የአገር አቋራጭ አውቶብሶች እንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን ተከትሎ መናኸሪያዎች በተጓዦች ተጨናንቀዋል ተባለ

[addtoany]
DW : በአዲስ አበባ የላም በረት መናኸሪያ ወደተለያየ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ለመሄድ ባሰቡ ተጓዦች ተጨናንቆ ተስተውሏል። መገናኛ አካባቢ ያለው የላም በረት መናኸሪያ ተሽከርካሪዎቹ በግማሽ እንዲጭኑ የሚል መረጃ ደርሶናል ያሉ ተሳፋሪዎች የመናኸሪያውን ዙሪያ ከበው ሲጠይቁ እና እቃዎቻቸውን ይዘው ተቀምጠው ተስተውለዋል።
ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተሳፋሪዎች ለቀናት በዚያው እንደቆዩ እና ለችግር መዳረጋቸውንም ተናግረዋል።
ይህንን ሁነት ለመዘገብ በቦታው የተገኘ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀረጻ ሲያደርግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የደነገገውን ርቀትን የመጠበቅ ጉዳይ በዘነጋ አኳኋን ለኮሮና ተኅዋሲ በሚያጋልጥ መልኩ ፣ ተጠያቂው ሰው ሲናገር የበለጠ ህዝብን አሰባስበው ተመልክተናል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች መሰባሰቡ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ፣ በድምጽ ማጉያ ህዝብን በተሳሳተ መረጃ የሚያደናግሩ ደላላዎችን ሲያስጠነቅቅ ነበር። ተሳፋሪዎቹ ትራንስፖርት ባለስልጣን ከሚሰጠው መረጃ ውጪ ሌላውን እንዳይቀበሉ ሲጠይቁ አርፍደዋል ። መጭው የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ይመስላል ዛሬ በርከት ያለ ተሳፋሪ በዚሁ መናኸሪያ ዙሪያ ለኮሮና ተህዋሲ አጋላጭ በሆነ ሁኔታ ተሰባስቦ ነበር።