“ቤተ መቅደሱን ማን በዘጋልኝ” (ሚል 1፡10) በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

      ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

               “ቤተ መቅደሱን ማን በዘጋልኝ” (ሚል 1፡10)

በዚህ ፈታኝ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ህንጻ ውስጥ በህብረት የሚደረገውን ጸሎት አቁመን በየቤታችን መደረጉን ክህደት እንደሆነ የምታወሩ፤ የወሬኞችን ልፍለፋ ሰምታችሁ ቅር የተሰኛችሁ፤ ስለ ካሮናቫይረስ ተረድታችሁ ሳትሰለቹ ህዝባችሁን ለማስተማር በትግል ያላችሁ የስነ ፍጥረት ተማሪወች፤ የራሳችሁን ሰውነት ሰውታችሁ የወገናችሁን ህይወት ለማትረፍ በትግል ያላችሁ ሀኪሞች ይህች ጦማር ትድረሳችሁ!

በደቂቀ አዳም ላይ የሞት ጥላዋን ከዘረጋቸው ኃያሏ ኢምንት ህዋስ እንድንጠነቀቅ የስነፍጥረት ተማሪወች የሚነግሩን ነብያት ክርስቶስ ሀዋርያት ከተናገሩት ጋራ ተመሳሳይ እንጅ የሚቃረን አይደለም።
በቤተ ክርስቲያን ህንጻ ውስጥ በህብረት የሚደረገው ጸሎት መቅረቱንና፤ በየቤታችሁ ጸልዩ መባሉን አንዳንድ ሰወች እየተቃወሙ በሚነግሯችሁ ከመቆጣትና እንደ ክህደትም ከመቁጠር ይልቅ፤ ማዘንና እንደ ክህደትም ልንቆጥረው የሚገባን ምን እንደሆነ ልንረዳ ይገባል።

አምላካችን የምናየውን የምንዳስስውን አቅማችን የሚያሸንፈውን ጠላት ታግለን እንድናሸነፍ ጥበቡን ኃይሉን ብርታቱን ይሰጠናል፤ ከማናየው፡ ከማንሰማው፡ ባቅማችን ታግለን ከማናሸነፍው ከረቂቅ ጠላት እንዲሰውረን ቆመንም ተቀምጠንም ተኝተንም ቢሆን ከያለንበት የምናቀርብለትን የምህላ ድምጽ ይሰማናል።
በህንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን በማህበር የምናቀረበው ምህላ ለጥያቄ የሚቀርብ ባይሆንም፤ ይህን በመሰለ ወቅት በየቤታችን ተወስነን በምናቀርበው ጸሎት ላይ መጠራጠር ደግሞ አምላካችንን በህንጻ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ ማድረግ ትልቅ ክህደት ነው። በቤተ ክርስቲያን ብቻ መጸለይም አማራጭ እንደሌለው አድርጎ መቃወም አይገባም። ልንቃወም የሚገባን፤ ራሳቸውን ነብያት አድርገው “ መአቱ እስኪያልፍ ድረስ ” ገለል በሉ የሚለውን የነብያትን ቃል በድፍረት የሚቃወሙትን ነው።

ይህን የመሳሰሉ ቸነፈሮች ሲከሰቱ ደጅ መዝጋት በሀገራችን የተለመደ ነው። በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ክልል በመቃብር ውስጥ ከሚኖሩ አባቶች በቀር ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰው እንዳይመጣ ይናገራሉ። የወረርሽኝ በሽታ በምህረቱ እስኪበርድ ድረስ የጉባዔ መምህሮቻችን የቤተ ጉባያቸውን ደጅ ይዘጋሉ። ሰውነቴ የዳሰሰውን ሲፈጸምም በዓይኔ ያየሁትን ያለንበት ወቅት ጠቅሶታልና ላካፍላችሁ። በነበርኩበት ቅኔ ቤት ወረርሽኝ የሚባል በሽታ ተከሰተ። ጮለሚት በምትባለው ገዳም ይኖሩ የነበሩ አባ ዘሩ የሚባሉ መነኩሴ ከዘጉበት ወጥተው “የየመንደሩ አጥር በራፍ፤ የየቤቱ ደጃፍ ይዘጉ፤ መውጫ መግቢያ በሮች ይቀየሩ’ ብለው ለደብሩ ተናገሩ።

ከመካላችን አንዱ ውጥንቅጥ (የእለት ምግብ)ለማግኝት ተስቦ ከገባበት መንደር ገብቶ በሽታውን ይዞ መጣ። ከሱ ጋራ ሌሎች ስድስት ተማሪወች ታመሙ። መምህራችን ጉባዔውን ዘጉ። ሽንብራና ባቄላ በኮፌዳችን እየሞሉ ከማንም ሰው አትገናኙ እያሉ በየደብሩ መቃብር ቤት እንዲበተን አደረጉ።ብዙ አመታት የቆየ በራዳት ዘራፊነት መምህሩን የሚረዳ ወልቃባ የሚባል ከጎሀ ጽዮን የመጣ ተማሪ ነበረ። ወልቃባ እና እኔ ከጔደኞቻችን ጋር እንሞታለን ብለን ከመምህሩ ጋራ ቀረን። መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ “ሞታችኌልና ህይወታችሁ በእግዚአብሔር ተሰውሯል”(ቆላ 3፡2)የሚለውን እየጠቀሱ እኛን ማጽናናት ቀጠሉ። ሶስት ተማሪወችና ረዳታቸው ወልቃባም በበሽታው ሞቱ።

በመቃብር ዘግተው የሚኖሩ ሌሊት እየመጡ ሬሳውን ከመምህራችን ጋራ እየተሸከሙ ወስደው ቀብረው እስኪመለሱ ድረስ በበሽታው ተረፍርፈው የሚያቃስቱትን ፈዝዠ ብቻየን እመለከት ነበር። እኔ ግን አልታመምኩም ነበር። የተያዘው ሁሉ ካገገመ በኋላ በመጨረሻ እራሳቸው መምህራችን ታመሙ።
“ከመ ሰዶም እምኮነ፤ ወከመ ገሞራ መሰልነ።
እስራኤል አስቱ ለእመ ኢተርፈ ለነ” ብለው ጉባኤ ቃና ዘረፉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን አእምሮው ጤነኛ ያልሆነ አንድ ታምሩ ቅርቀብ የሚባል እብድ፤ ”ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዳችሁ ጸበል ጠጡ ምንም አትሆኑም“ እያለ በየመንደሩ እየዞረ ይናገር ነበር። እራሱ ታመመና በመንገድ ላይ ወደቀ። ታሞ በመንገድ ላይ መውደቁን መምህራችን ሰሙ። ተሽክመው አምጥተው ከኛ ጋራ ቀላቀሉት። ታምሩ ቅርቀብ ብዙ ተሰቃይቶ ከዳነ በኌላ በየመንደሩ እየዞረ፦
መምህር ማለት እንደፈረደ፤
ዘራፊ ማለት እንደ ራደ”
የቀረው መምህር ከኔ የባሰ ለፍላፊ፤
ተማሪወቹም እንደ ጆቢራ ቀፋፊ“
እያለ ተሸክመው ወደ ትምህርት ቤታችን ያመጡትን መምህራችንን በግጥም እያመሰገነ፤ ሌሎችን መምህራን እየነቀፈ መናገር ጀመረ። ራደ የሚባለውም ታሞ ካገገመ በኋላ፤ ታምሩ ቅርቀብ በታመመ ጊዜ በቅርብ ይረዳው የነበረ ተማሪ ነው። ታምሩ ቅርቀብ ስለረዳው ራደንም ያደንቀዋል።

ይህን የመሰለ መቅሰፍት ሲከሰት መምህሮቻችን እንኳን ሰው እንስሳትም ከየመሰማሪያቸው እንዲገቱ ያደርጋሉ። በማቅ ይከደናሉ(ዮናስ 3፡8 )እያሉ ግስ ገሰውበታል። ቅኔ ተቀኝተውበታል። የህዝቡ ንግግር ግጥሙ ሁሉ በልቅሶው በዋይታው ላይ ይመሰረታል። የበሽታው ወራት አልፈና አዳሙ እጅጉ የሚባሉ አንድ አዛውንት በሌላ ህመም ሞቱ፤ ከቆላ ከደጋ ዘመድ አዝማድ ተሰበሰበና ህዝብ እያረገደ ከበላይ ዘለቀ ጋራ የፈጸሙት ጀብዱ እየተነገረ በምሾ ግጥም ተቀበሩ። ቀባሪ የጠፋበትን ክፉ ዘመን፤ ከደህናው ዘመን ጋራ ያነጻጸረች ምሾ አውራጅ፦
የሰው ልጅ ሲደላው ለካን ልቡን ያጣል
ሰው እያስታመመው ለሞተ ያለቃሳል።
አታምርሩ ልቅሶ ፈጣሪ ይቆጣል
ያምናው ተመልሶ ተስቦ ይመጣል
ብላ ምሾ አወረደች። ይህን የመሰለ ያልተጠበቀ ቸነፈር በህብረተ ሰብ ላይ ሲከሰት እንደነ አባ ዘሩ ያሉ አስጠንቃቂወች እንደ የኔታ ፈረደ ያሉ አስተዋዮች እንደ ታምሩ ቅርቀብ ያሉ ”ምንም አይነካችሁም“ የሚሉ እብዶች ይከሰታሉ።

በዘመናችንም በሸፍጥና በስግብግብነት የሰከሩ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ተደጋጋሚ ቀውስ ቤታቸው የፈረሰባቸው፤ ኑሯቸው የተናጋባቸው ሕይወት የተቃወሰባቸው ሰወች፤ የሰይጣን መጠናወት እየመሰላቸው በስንቱ አታላይ እጅ እንደወደቁ እየተመለከትን ነው። “ማንም ክርስቶስ ከዚህ ወይም ከዚያ ቢላችሁ አትመኑ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ነብያቶች ይነሳሉ፤ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኴ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና አስደናቂ ነገር ያደርጋሉ፤ አስቀድሜ ነገርኴችሁ”(ማቴ 24፡24) ተብሎ የተነገረውን ማስጠንቀቂያ ያነበቡ ሁሉ በሸፍጠኞችና በእብዶች እየተታለሉ ገደል እየገቡ ናቸው።

ያላነበበ ያልተረዳ ቀርቶ ተረድቻለሁ አውቄአለሁ የሚለው በዚህ አይነት ቀውስ ላይ ካለ፤ በኃያላን መንግሥታት ላይ የሞት ጥላ የዘረጋች ኃያሊቷ ህዋስ መጣች የሚባለው የወሬ ውሽንፍር ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ የህብረተ ሰቡን የማሰብ ኃይል እንደሚያናጋበት መገመት የሚከብድ አይመስለኝም። እንደተለመደው በቤተ ክርስቲያን ህዝብ ተሰብስቦ የሚደረገው ስርአተጸሎት መአቱ እስኪያልፍ ድረስ ታግሰን በየቤታችን እንጸልይ ማለት፤ ”ኃጢአት ነው የእምነት ጉድለት ነው“ እያሉ እንደ ታምሩ ቅርቀብ የመሰሉት ቢቃዡ አያስደንቅም።

የነታምሩ ቅርቀብ ቢጤወችን ቅዠት ከመስማት ይልቅ፤ ለምህረቱ መግቢያ በር ካፋች እንደሆነ ራሱ ክርስቶስ የተናገረውን “እርስ በርሳችሁ ይቅር ካልተባባላችሁ ይቅር አልላችሁም” “ንስሀ ባትገቡ ትጠፋላችሁ” የሚለውን ተግባራዊ በማድረግ ህሊናን መንፈስን ከኃጢአት ቁስል ማጽዳት ይረዳል። ያረጋጋል። ያጽናናል። ምህረትም ያወርዳል።ሊያሳስበንና ሊያስጨንቀን የሚገባንም ለምህረቱና ለይቅርታው እንቅፋቶች ናቸው ከሚባሉት የህሊና ብክለት ከሚያስከተሉት የኃጢአት አይነቶች መላቀቅ አለመቻላችንና፤ ነብያትም ክርስቶስም ሀዋርያትም መንፈሳውያን ሊቃውንትና ስለ ካሮናቫይረስ የተረዱ የስነ ፍጥረት ተማሪወች የነገሩንን ፈጥነን አለመስማታችን ነው። የሁሉንም ምክር እንዳንሰማ በጫጫታቸው ጆሯችንን አፍነው ከገደል ጫፍ አቁመው ”ብትዘሉ ሚካኤል ይቀልባችኋል ገብርኤል ይታደጋችኌል“ እያሉ እምነታችንን ከሚፈታተኑን ሰወች መራቅ አለመቻላችን ነው።

ሰው ወድቆ ከማይተርፍበት በመቅደስና በረጀም ተራራ ጫፍ ላይ ሰይጣን ክርስቶስን አቁሞ ሲፈትነው፤ ክርስቶስ ሰይጣንን ”አንተ ሰይጣን“ ወግድ ያለው፤ እኛም አምላክ ያድናችኌልና መሰብሰባችሁን አታቁሙ እያሉ ሰውነታችን ሊቆቋመው ከማይችላቸው ካሮናቫይረስ ከመሳሰሉት ወጥመዶች እንድንገባ ከሚፈታተኑን እንድንርቅ ለምሳሌነት ነው። ከያንዳንዳችን የሚፈልገው ኢስይያስ “መአቱ እስኪያልፍ ሽሹ በያላችሁበት ተወስናችሁ ቆዩ” (ኢሳይያስ 26፡ 20) እያለ ባንድ ወቅት፤ “እናንት እቃ የምትሸከሙ እልፍ እልፍ በሉ። ርኩስ ነገር አትንኩ። እግዚአብሔር በፊታችሁም በኌላችሁም ሆኖ ይታደጋችኌል”(ኢሳ 52፡11)። እያለ በሌላ ወቅት ለተናገረው መታዘዝ ነው።

ከዚህ ትእዛዝ በራቀ መንገድ፤ በየትኛውም ቦታ የሚቀርበውን ምህላና አቅራቢውን እግዚአብሔር አይቀበለውም። የሚቀርብበትንም ቤተ መቅደስ “ይዘጋ” ብሏል። እኛ በህዝብ ፊት የምንቆም መንፈሳውያን መምህራን ምድራዊ ጥቅማችን ያስቀሩብናል ብለን እንዳናስቀይማቸው ለምድራውያን አለቆች የተጠነቀቅንላቸውን ያህል፤ በፈጣሪያችን ፊት ስንቆም ለመለኮታዊ ክብሩ አልተጠነቀቅንም።  ለደሀው ህዝብ አልተጨነቅንም። አንደበታችንን ከህዝብ ሰርቀነዋል። እግዚአብሄርንም ሸፍጠነዋል። በሸፍጥ የሚቀርበውን ጸሎትና አቅራቢወችንም አይቀበልም። “ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ” (ሚል 1፡10)ሲል እግዚአብሔር በነቢዩ ሚልክያስ በኩል የተናገረው ቃል የተጻበትን መጽሀፍ ልናጥፈው አይገባም።

“በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፌ አዝዟልና፤ መንፈሱም ሰብስቧቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም። ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም”(ኢሳ 34፡16) የሚለውን መንፈሳዊ መጽሐፍ ከመምህራን ሀተታ ባለመረዳታቸው አቅማቸው ከነሱ በታች የሆኑትን ወገኖች ግራ በማጋባት ላይ ያሉትን አቁሙ ልንላቸው ይገባል። በእግዚአብሄር የተፈጠሩትን፤ በአየረ ዓየራት፤ በእመቀ እመቃት ያሉትን ፍጥረት ለማወቅ በመታገል ላይ ያሉት፤ የስነ ፍጥረቱ ተማሪወች የነገሩንን እንዳንሰማ፤ በተረታቸው እየታገዙ ቅዠት የሚያሰራጩትን እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ልንሰማቸው አይገባም። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በማወቅም ባለማወቅም በፈጣሪና በስነፍጥረት ላይ በጠላትነት ራሳቸውን ማሰለፋቸውን የሚረዱ አይደሉምና በሙሉ ኃይላችን ልንገስጻቸው ሀላፊነታችን ያስገድደናል።

“ወብርሃንሰ ዘውስተ ጽልመት ያበርህ ወያርኢ፤ ወጽልመትኒ ኢይረክቦ ወኢይቀርቦ” (ዮሐ 1፡5)። የሚለውን ምንባብ ”በስነፍጥረት ተመራምረው ያወቁት እውቀት በስዋሬ ያለውን ምሥጢር ይገልጻል“ ብለው ሊቃውንት አበው በሚያስተምሩበት ጉባዔ ስነ ፍጥረትን ለማወቅ በመታገል ላይ ያሉትን የስነ ፍጥረት ተማሪወችን ( scientists ) ለመስማት እንድንጓጔ አስተምረውናል። ይህም ብቻ አይደለም።

ቴወዶስዮስ የሚባለው ሊቅ “ወአነ አአምር ርቱዐ ከመ ኢይደሉ ህዝባዊ ይምሀር መምህራነ ።ወእመ አኮሰ ይመስል ከመ ነዳይ ዘይጸውእ ባዕለ ከመ ይብላእ ሀቤሁ ከማሁ ሕጹጸ አዕምሮ አነ” (ሃይ ም 83፡26) እያለ በተናገረው ይህም ማለት፦ ሊቃውንት ስረ ነገሩን ጠልቀውና ርቀው ስለሚያውቁት ነገር፤ በነሱ ፊት ቆሞ ለመናገር መድፈር ምንም የሌለው መናጢ ድሀ ባለጸጋውን ልጋብዝህ የሚል ግብዝ መምሰል ነው“ ብለው ባልደከምንበት ነገር በደከሙበት ሊቃውንት ፊት እንዳንናገር በሰፊው አስጠንቅቀውናል።

“እመሰ ይርህቅ ለሕሊናነ አዕምሮተ ምግባራት ዘንኔጽሮሙ ወኢንክል ተናግሮ ዘከመ ድልወቶሙ እፎኑመ ንትሀበል ለተናግሮ ዘኢነአምር” (ሃይ ም 33፡ ቁ 4) ማለትም፦ካቅማችን በላይ የሆነውን እኛ ያልተረዳነውን የፍጥረታትን ባህርይ የተረዱ ምሁራን የነገሩንን ለመረዳትና ለማወቅ ካቃተን የስነ ፍጥረት ባለቤት ስለሆነው ፈጣሪ እንዴት ማወቅ እንችላለን? ብሎ የስነፍጥረትና የነገረ መለኮት ምሁር ባስልዮስ ያስተማረውን መሰረት በማድረግ አባቶችችን በሀተታቸው ደግመው ደግመው ነግረውናል። ይህን ሁሉ በጉባያችን የተማርነውን ማስጠንቀቂያ እየሰበሩ፤ የራሳቸውን ግምት በሊቃውንት ፊት በድፍረት የሚናገሩ ሁሉ ሰርገው የገቡ እንጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረቻቸው አይደሉም።

የስነፍጥረት ተማሪወች ሀኪሞች ሆይ!ትግላችሁ ከካሮናቫይረስ ጋራ ብቻ ሳይሆን ካልተማሩት ከኔ ቢጤወች ጋርም እንደሆነ ስገነዘብ እጅግ አዘንኩላችሁ። ወዳችሁ ፈቅዳችሁ የመራጣችሁት ተልእኮ የተቀደሰ ክርስቶሳዊ ነውና ታገሉ። እንደዘመኑ ፖለቲካና ክህነት በግል ጥቅም እንዳታረክሱት ግን ተጠንቀቁ። ልረዳችሁ ባልችልም፦ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እሳት ያድነናል። ባያድነንም አንሰግድም እንዳሉት (ዳንኤል 3፡17)፤ እናንተም ከካሮናቫይረስ ይሰውረናል ፤ ባይሰውረንም ለተልእኳችን እንሙት በሚለው ተጋድሏዊ እምነት አምላካችሁ አጽንቶ ይህን ፈታኝ ዘመን እንዲያሻግራችሁ እጸልያለሁ።

ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ወገኖቼ ሆይ!ነብያትም፤ ክርስቶስም፤ ሐዋርያትም፤ ሊቃውንት እና ዘመናውያን የስነ ፍጥረት ተማሪወች የገሩንን አስተባብረን ለነፍሳችንና ለሰውነታችን የሚበጀውን ሁሉ እናደርግ፤ ከመንፈሳዊውም ከሥነፍጥረትም ግንዛቤ የራቀ አዕምሮ ባላቸው ሰወች ቅዠት ግራ አትጋቡ። በደቂቀ አዳም ላይ የሞት ጥላዋን ስለ ዘረጋቸው ኢምንት ህዋስ እንድንጠነቀቅ የስነፍጥረት ተማሪወች የሚነግሩን ነብያት ክርስቶስ ሀዋርያት ከተናገሩት ጋራ ተመሳሳይ የተቀደሰ እንጅ የሚቃረን አይደለም።

ክርስቶስ “ወዝክተኒ ኢትህድጉ” ማለትም ይህንም ሳትተው ያንንም ልታደርጉ ይገባችኌል (ማቴ 23፡23)ያለውን፤ ሐዋርያትም ሊቃውንትም የስነፍጥረት ተማሪወችም (ሳይንቲስቶች)የመሰከሩትን ተግባራዊ ለማድረግ እየታገልን፤ ባልተገነዘብነው ባላሰብነው መንገድ ከሚገጥመን ካሮናን ከመሳሰሉት ረቂቃን ህዋሳት እንዲሰውረን ማዳን የባህርዩ የሆነውን እግዚአብሄርን እንማጸነው።

በተረፈ የመከራው ወቅት እስኪያልፍ በየቤታችሁ ጸልዩ መባሉን እየተቃወሙ የሚናገሩትን፤ እንደ ክርስቶስ ሂድ ሰይጣን እንድትሏቸው እንደ ሀዋርያትም “ስለ ክፋትህ ንስሀ ግባ ምናልባት የልብህን ሀሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚ ለምን” እንድትሏቸው አደራ እያልኩ በነቢዩ ሚልክያስ በኩል “ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ” ሲል እግዚአብሔር በተናገረው ቃል እሰናበታችኌለሁ።

የሞት ጥላዋን ከዘረጋችብን ኃያሊቷ ህዋስ እግዚአብሔር ይሰውረን!

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ  [email protected]