እነ በረከት ቶሎ ጡረታ ካለወጡ ወይም አርፈው ካልተቀመጡ ያልጠበቁት ነገር ሁሉ ሊገጥማቸው ይችላል::

ጋዜጠኛ ፋሴል የኔዓለም
ምናልባት አንዳንዶቻችን በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የውስጥ ትግል የተጠናቀቀ ሊመስለን ይችላል ፣ ግን አይደለም:: ልክ ነው ህወሃት እጅግ ተዳክሟል፥ በፌደራል ደረጃ ብዙ ስልጣኖችንም አጥቷል:: ነባር ታጋዮቹም ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሸሽተዋል፥ ቢሸሹም ግን መዶለታቸውን አላቆሙም:: የዱለታው ማእከል ደግሞ በረከት ስምኦን ነው:: በረከት ባለፉት ሳምንታት በተከታታይ ወደ መቀሌ ሲጓዝ ከቆየ በሁዋላ በመሃል አቋርጦ ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ነበር:: ትናንት ህክምናውን ጨርሶ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰ ከሰአታት በሁዋላ ወዲያውኑ ወደ መቀሌ በሯል:: ወደ ቦሌ ሲሄድ መኪናውን እራሱ እያሽከረከረ፣ ያለ አጃቢ፣ መሄዱን ከሁነኛ ምንጭ ሰምቻለሁ:: “ለምን? ”ብዬ ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ “ጥላውን ሁሉ ማመን አቁሟል” የሚል ነው:: በረከት ለውጡን ለመቀልበስ ቀዳዳ እየፈለገ ያለው ብአዴን ውስጥ ነው፥ ብአዴን ደግሞ ቀዳዳውን ሁሉ እየደፈነ “አናስገባም ሰርገኛ” ብሎአል፥ የበረከትና የህወሃት ደጋፊዎችን ሁሉ ከአመራር ቦታዎች ላይ ጠራርጎ እያስወጣ ነው:: የሃምሌው የብአዴን ጉባኤ የተበላ እቁብ እየሆነ ነው፣አንዳች ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር የእነ በረከት ቡድን ሃምሌ ላይ አሸንፎ ሊወጣ አይችልም:: እነ በረከት ቶሎ ጡረታ ካለወጡ ወይም አርፈው ካልተቀመጡ ያልጠበቁት ነገር ሁሉ ሊገጥማቸው ይችላል:: ምናልባት ትግራይ ስለመሸጉ ሴራቸው የማይታወቅ መስሎአቸው ከሆነ፣ የተሳሳቱ ይመስለኛል:: በዚህ አጋጣሚ ትግሉ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ የሚመስላችሁም ሰዎች እንደገና አስቡበት:: እነዚህ ሰዎች እጅ እስኪሰጡ ድረስ እጅን ሰብስቦ መቀመጥ አይገባም:: የታጠፈ እጅ ካገኙ ዜሮ እድልም ይዘው ሊነሱ ይችላሉ::
ቅዳሜ ለእነበረከት ግልጽ መልእክት የሚተላለፍበት ቀን እንደሚሆን እጠብቃለሁ ::