“ከነአቶ በቀለ ገርባ ኮረዳ የቀረበልን የፍታት ጥሪ” በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

በነአቶ በቀለ ገርባ ኮረዳ ለኢትዮጵያ ህዝብ የቀረበ የፍታት ጥሪ የቆየ ትዝታየን አስታወሰኝ። “ከራሳችሁ ባህል ወጥታችሁ ከኛ ከእንግሊዞች የተወረሰውን ፍታት አደነቃችሁ። አስተርአየ ግን የኢትዮጵያን ባህላዊ ፍታት እንደያዘ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ወደ ሰውነት የሚጠጋው ኢትዮጵያዊው የፍታት ባህል ነው። እናንተ ግን ከራሳችሁ  ባህላዊ ስርአተ ፍታት ርቃችኌል” ብለው እንግሊዛዊው መምህሬ ዶ/ር ስሚዝ የተናገሩት  ትዝ አለኝ።  ሲፈቱና ሲያፋቱ የኖሩት ወያኔወች ከቤተ መንግሥት ከራቁ በኌላ፤  ምንም እንኴ  ቤተ ክርስቲያችን የገጠማትን ችግር  በማትገልጽበትና  በማይመጥናት ጫጫታ የሚካሄደውን ብዙወቹ መናገር ቢሞክሩም  ያፍ መፍቻ ንግግር ጫጫታ መስሎ ስለታየኝ፤ የ ጫጫታ አዳማቂ ላለመሆን ብየ  ብዕሬን አስሬ አፌን ዲዳ ለማድረግ ወስኘ ነበር። ለሚያግበሰብሰው ትርፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ ወያኔ ያስረኛል፤ ድርጅቴ ይዘጋብኛል ብሎ አፉን ዘግቶ የኖረው ሸፍጠኛ የወንጀል ሰባኪ ሁሉ አፉ ቢፈታም፦”ትዳር ፍቱ እኔን አግቡ“ ያለች በሽህ ለሚቆጠር ወንድ ያለምንም ሀፍረት ራሷን ያቀረበችውን ኮረዳ ሳይ ዝምታየ ተሰበረ።

ስለፍትሀት ከመንደሬ ሳድግ ካየሁት ከኢትዮጵያውያንና ከፈረንጆች መምህሮቼ ከተማርኩት ጥቂት ላካፍላችሁ። ካብነቱ መምህራን የተማርኩትን ላስቀድም። በሰባት ነገሮች ተጣምሮና ተጠናቅሮ የተሰራው ሰው በዚህ ዓለም የሚኖረው ዘመን ሲያበቃ ጥንቅርነቱ ይፋታል ይበታተናል። በመፋታት ይሞታል። በፍታት ወደ መቃብር  ይሸኛል። አትናቴወስ “ኢንክል አብጽሆተ አዕምሮቱ ዘከመ ኀብሩ አርባእቱ ጠባዕያት ከሃሊ እግዚአብሔር ገብረ ሰብአ አስተናቢሮ በውስቴቱ መንፈሰ ሕይወት እንዘ ኢይኀብር እሳት ምስለ ማይ ወመሬት ምስለ ነፋስ ” (ሃይ 28፡31) እንዳለው፦ ማለትም፦ ልንተረጉመው በማንችለው ጥበቡ እግዚአብሔር ተቃራኒ የሆኑትን ነፋስንና መሬትን ውሀንና እሳትን አስማምቶና አጣምሮ  ሰውን ሰራ፤ ከሶስት ነገር የተጠናቀረችውን መንፈሰ ሕይወት በውስጡ አስቀምጦ ሰውን ነፍስ ያለው ሰው  ካደረገው በኌላ በለስን ቀጥፎ እንዳይበላ፤ ቢበላ በበላበት ቀን ነፍሱና ሥጋው እንደሚፋቱ ማለትም እንደሚሞቱ ነገረው።

ሰው የፈጣሪውን ትእዛዝ ከመስማት ይልቅ፤ የሰይጣንን ምክር ተቀብሎ  ቀጥፎ በላ። ሀሉንተናው ከሁለንተናው ተፋታ። ነፍሱ ከሥጋው፤ ትስብእቱ (እሱነቱ)ከቤተ ሰቡና ከኑሮው ከቦታው ተለያየ (ተፋታ)።  ጸጋው ሁሉ ተገፈፈ። ተራቆተ። ማፈሩን አወቀና  በቀጠፋት  ቅጠል ዓለምአፈርነቱን ሊደብቅ ሞከረ። የፈጠረው አምላክ ግን፤ የቀጠፍካት ቅጥፈት ርቃንህን መደበቅና መሰወር አትመጥንም። ይህ ሁሉ በቅጥፈትህ ዓለማፈርህ ነውና ወደ አፈርነትህ ግባ አለው። ቀጣፊ ማለት የነበረውን የሚያዛባ፤ አስመስሎ የሚያቀርብ ዋሾ አታላይ ማለት ነው። በኢትዮጵያችን ቀጣፊ ስንል ሰይጣን ወይም እባብ ማለት ነው።

ሰው  በቅጥፈቱ ምክንያት ትስብእቱ ሲፈረሰ   “ግብኢ ነፍስየ ውስተ እረፍትኪ” ማለትም “የማትሞችው ረቂቋ ነፍስ ወደ ፈጣሪሽ፤ በስባሿ ሰውነት ወደ አፈርነትሽ ተመለሽ” እያሉ ቄሶች በሞት የተቀጠፈውን ሬሳ ይፈታሉ። ዘመድ አዝማድ እንደየቀረቤታው “ወንድሜ አጎቴ ጋሻየ መከታየ” እያለ በመፍታት በሞት የተቀጠፈውን ትስብእቱን እንዲሸፈንበት ፈጣሪ ባዘዘው አፈር ይሸፍነዋል።  ኅብረተ ሰቤ የሳለብኝን ይህን ስርአተ ፍታት በትዝታየ ሰንቄ  ድንበር ተሻግሬ ለትምህርት ኬንያ ገባሁ። በቆየሁበት ኮሌጅ ከዚህ በታች የምጠቅሰው ፍታት ገጠመኝ።

በትምህርት ላይ ሳለሁ፦“ማኦማኦ” በሚባለው የኬንያ ነጻ አውጭ ድርጅት ከነ ጆሞ ኬንያታ ጋራ ተሰልፈው ለአገራቸው ለነጻነታቸው የተዋጉ አርበኛ ሞቱ። አርበኛው በህወት እያሉ ኮሌጁ የተመሰረተበትን ሰፊ መሬት ለግሰዋል። በለገሱት መሬት ላይ ከኮሌጁ ህንጻ ጋራ የተጎራበተ በቅዱስ እንድርያስ ስም የተሰየመ ካቴድራልም ተመስርቷል። እንግሊዝ በቅኝ ግዛት ከገዛቻቸው commonwealth  በሚባል ህብረት ከተሳሰሩ አገሮች ከዩጋንዳ ከታዝንያ፤ ከህንድ እና ከእግሊዝ አገር  ታዋቂና የተማሩ ሰወች በአርበኛው ስርአተ ፍታት ላይ እንዲገሚኙ በጋዜጣና በራድዮ ተነገረ። ከሶስት ኢትዮጵያውያን በቀር የቀረው ተማሪ እንግሊዝ በቅኝ ግዛት ከገዛቻቸው commonwealth  በሚባል ከተሳሰሩ አገሮች የመጣ ነው። ስርአተ ፍታቱ በቅዱስ እንድርያስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና በኮሌጁ ክበብ  እየተመራ እንደሚከናወን ተገለጸ።

ወቅቱ በSociology እና በcultural anthropology መካከል cultural theology ተብሎ የተቀየሰውን ክፍለ ትምህርት የምንቃኝበት therm ነበር። ከምንጠቀምባቸው መጻሕፍት አንዱ  African Religions and Philosophy  በሚል ርእስ John Mbiti የሚባሉት ያዘጋጁት መጽሐፍ ነበር። በዚህ ክፍለ ትምህርት እንደምሳሌ ተደጋግማ  African Indigenous Church እየተባለች ምትጠቀሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ፕሮፌሰሩ “በቀብሩ ስርአት ተገኝተን ከሟቹ ቤተስብ ጀምረን ያየነውንና የሰማነውን ከየራሳችን ባህላዊ የቀብር ስርአት ጋራ በማነጻጸር እንድንጽፍ አዘዙን። በዚህ ጽሑፍ ያልተሳተፈ ተማሪ ከጠቅላላ ማርክ 50 እንደሚያጣ አስጠንቅቀውን ወደ ስርአተ ፍታቱ ሄድን። እንደራሴ ባህል በፍትሀቱ የተገኘው ቤተ ሰብ ዘመድ አዝማድ እንደየቀረቤታው “ወንድሜ ጋሻየ አጎቴ መከታየ” እያለ ከል ለብሶ የሚያልቅስ ጠብቄ ሄድኩ።  አንድም አላየሁም። ይልቁንም እንደሰርገኛ ነጫጭ የለበሱ  ውሀ እየጠጡ ከፍታቱ ጋራ ያልተገናዘበ ነግር በፈገግታ ይነጋገራሉ። እኔም ሁላችንም የተሰማንን ጻፍን። ወደ ክፍላችን ተመልሰንና የጻፍነውን ለፕሮፌሰር ስሚዝ አስረከብን።

በሳምንቱ የተማሪው ሁሉ ወረቀት ታርሞ  ተመለሰ። የኔ ብቻ ዘገየ። መዘግየቱ አሳሰበኝና ዶ/ር ስሚዝን የዘገየበትን ምክንያት ጠየኳቸው። የአካዳሚክ ዳይሬክተሩ ሚስተር በንሰንን ጥይቅ አሉኝ። ሚስተር በንሰንን ጠየኳቸው። ከትምህርት ቤቱ Principal  ከ Gedion Erere ታገኘዋለህ አሉኝ።ከተለያዩ አገሮች ቋንቋዎችና ባህሎች የመጡ መምህራን፤ ከተለያዩ አገሮች በመጣነው ተማሪዎቻቸው አማካይነት በተለያዩ አገሮቻችን የሚካሄደውን የቀብር ስርአት  ለመማር የተዘጋጁ ሆነው፤ ወረቀቶቻችን ይቀባበሉ ኖሯል። እኔ ያዘጋጀሁት ከተማሪዎች ሁሉ የተለየ ሆኖባቸዋል። በመገረም ያዘጋጀሁትን እየተቀባበሉ የየራሳቸውን ስሜት ሲያሰፍሩበት ስንብተው በመጨረሻ ባሰፈሩበት ሀሳባቸው  ድሪቶ ሆኖ ወረቀቴ ደረሰኝ። ፕሮፌሰሩ የጠቅላላውን ተማሪ ሀሳብ ጠቅለል አርገው ባቀረቡት ሀተታቸው (lecture) “ሰው መነሻውና መድረሻው ልደትና ሞት ነው።  ሰፊና ጥልቅ ይዘት ያለው ስለሆነ በ cultural theology  እና በ cultural anthropology መጠናት ካለባቸው ሰበነክ (anthropoid) ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሞት ነው።

ሁላችሁም የትላንቱን ስርአተ ፍታት በየባህላችሁ መነጽር አትታችሁታል። ብዙ ልዩነት ግን አይታይም” በማለት የኔን ለብቻ  ለይተው በማዘግየት የጠቅላላውን ተማሪ  ሀሳብ አጠቃለው አቀረቡት።ንግግራቸውን በመቀጠል “ከተማሪው ሁሉ ልዩ ሆኖ የአስተርአየን በማግኝታችን ተደንቀናል። ይልቁንም ይበልጥ ያስደነቀን” ብለው፦ ወደነ እነ ዮሐንስ ሁንቄ እየተመለከቱ “ከኢትዮጵያ ከመጣችሁት ከናንተም  ልዩ መሆኑ ነው” አሉ። ቀጠሉና “ካንዲት አገር መጥታችሁ  የተለያየ ግንዛቤ እንዴት ኖራችሁ?  ብለው ፕሮፌሰሩ ጠየቁን። ልዩነታችንን በተማሪው መካከል እንድንገልጽ ገፋፉን።  እነዮሐንስ ሁንቄ “እኛ  ፕሮቴስታንቶች ነን። “ወንድም ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “ተስፋ እንደሌላቸው እንዳታዝኑ”(1ኛ ተሰሎ 4፡13) ያለውን ትምህርት ተረድተን ኋላ ቀር ከሆነው ከኢትጵያ ኦርቶዶክስ ባህል ወጥተናል።  ኬንያ ያየነው ፍትሀት  ትክክል ነው“ ብለው ሀሳባቸውን ገለጹ።

ፕሮፌሰሩ ወደኔ እያዩ  “ሀሳብ ካለህ እድሉን ልስጥህ” አሉኝ። እኔም “የጻፍኩት ጽፌአለሁ። ተጨማሪ ካስፈለገ ባህላችንን የሚያንጸባርቁ ፕሮቴስታንቱ የማይጠቅሳቸው የኔ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቅሳቸው መጽሐፈ ጦቢትና፤  መጽሐፈ ሲራክ የሚባሉ apocrypha መጻሕፍት አሉን። ሲራክ “ለሞተ ሰው አልቅስለት እዘንለት ራስህንም አሳዝን እንደ አገሩ ባህልም ተዝካር አውጣለት። ያገለገለህን ሰው ሞት ቸል አትበል” (ሲራክ 38፡ 16)። ይላል። በመጽሐፈ ጦቢያ ላይም “የሰው ሬሳ ወድቆ አገኘሁ። ወደ አንዱ ቤት አስገባሁት፤  ጸሐይ እስኪገባ ድረስ እህል ሳልቀምስ ቆየሁ ። ወደ ቤቴ ተመልሽ ታጥቤ እያዘንኩ እህል ቀመስኩ”(መ. ጦቢት 2፡3᎗4)።  የሚል አለ። በነዚህና በመሳሰሉ መጻሕፍት  ባህላችን የተደገፈ ስለሆነ የሞተ ሰው እዚህ እንዳየሁት በሳቅ በፈገግታ ፍታት ወደ መቃብር አይሸኝም። ሳይቀበርም እህል አይቀመስም።ፈጽሞ ነውርና ዘግናኝ ነው” አልኩ። ስሙን የረሳሁት ሌላው ኢትዮጵያዊ ቀበል አደረገና በዚያ ሁሉ ተማሪ ፊት “እናንት ኦርቶዶክሶች ነፍስ እናጸድቃን እያላችሁ የተዝካር ድግስ ለመብላት ያዘጋጃችሁት ዘዴ ነው” አለኝ።

በተጨማደደ ግንዛቤው እኔን ለመሞገት ያቀረበውን ሀሳብ በዚያው ቅጽበት ሳላስተካክለው ብቀር፤ የሰሙት ተማሪወች  ይዘው ወደያገራቸው እንደሚገቡ ተሰማኝ። የተጠቃሁም መሰለኝና በቁጣ “መኑ ውእቱ ዘኢይትአመኖ ለእግዚ እምዐላውያን በውስተ ሲኦል በእንተ ዕልወታ ለነፍሱ። ወአልቦ ህየ መኑሂ አላ ወጽአ ኩነኔሁ ለእግዚአብሔር ለዕለ ኩሉ ዘይመውት እንዘ ህልው በሕይወቱ”(ሃ. አ. ም . 52፡32)። ይልብሀል” ብየ ቁጭ አልኩ።  በዚያች ቅጽበት አስብ የነበረው፤ መከላከሌን ብቻ  እንጅ የት እንዳለሁ፤  ለማን እና በምን ቋንቋ እንደምናገር አላሰብኩም ነበርና የተናገርኩትን እንኳን ከሌላ አገር የመጡት ለራሳቸው ለነ ዮሐንስም ግልጽ አልነበርም። ፕሮፌሰሩም  አስተርአየ በቋንቋችሁ የተናገረውን ከመካከላችሁ አንዳችሁ በእንግሊዘኛ ንገሩን” አሉ።

እነ ዮሐንስም “የተናገረው ግዕዝ ስለሆነ እኛም አናውቀውም” አሉ። መምህሩ የበለጠ ግርሟቸው የተናገርኩትን ማወቅ ፈለጉና፤ ራሴ ወደ እንግሊዘኛ መልሸ እንድገልጸው ተጫኑኝ። በተሰበረ እንግሊዘኛየ “Haw deceived  is a person who is hpping that he could inherite the king dom of God without believing in God and confessing his sin while he still  is alive” አልኩ ። የደረስንበት ዘመን እንዳፈራቸው ደፋሮች የሰው ሀሳብ እየዘረፉ በመምህራንና  በተማሪ ፊት መናገር ጸያፍ ነው። የራስ ሀሳብ ከሆነ የራሴ እየተባለ፤ ውሰት ከሆነና ወይም ከመጽሐፍ የተወሰደ ከሆነ የደራሲው ስምና የመጽሐፉ ርእስ እየተጠቀሰ ማናገር ግድ ነውና፤ ፕሮፌሰሩ “የራስህ ሀሳብ ነው? ወይስ  አፈ ታሪክ ነው?” ብለው ጠየቁኝ። “ከመጽሐፍ ነው” አልኴቸው። “የመጽሐፉን ስም መጥቀስ ትችላለህ?” አሉ። “ሃይማኖተ አበው” ይባላል አልኴቸው። “ምን ማለት ነው” አሉኝ።  “the faith of the fathers ማለት ነው“ አልኳቸው።  “የገለጽብከት የራስህ ሰዎች የማይሰሙት ቋንቌ ምንድነው? አሉኝ። ”ግእዝ ይባላል“ አልኳቸው። የምትጨምረው ሀሳብ አለህ?አሉኝ።

ንግግሬን በመቀጥል፦ “ከሞትን በኌላ ትንሳዔ እንዳለ እናምናለን። ከሞት ተነስተን  የምንገናኝበትን ቀን ወደ ማናውቅበት ወገን በሞት ተለይቶ በፍታት ሲቀበር ይቅርና  የክረምቱ ወቅት አልፎ ወንዞች ጎለው እስክንገናኝ ድረስ ወገንና  ወገን ስንለያይ በልቅሶ ነው። ከብቶቻችንም ከመካለቻው አንዱ ታርዶ ፈርሱና ደሙ ሳይጠረግ  ማታ ወደ በረታቸው ከተመለሱ በታረደበት ዙሪያ እየጮሁ ወደ በረታቸው በቀላሉ አይገቡም። ከሜዳ ከመመለሳቸው በፊት ደሙና ፈርሱ መታጥብ አለበት”  አልኩ። ዮሐንስ ሁንቄ ቀለብ አደረጋና “እንስሳቱም እንደናንተ ክርስቶስን ስላልተቀበሉ ነዋ! የሚያለቅሱት” አለ። መምህሩም ተማሪውም አንድ ላይ ሳቃቸውን ለቀቁት። በኔ የተሳቀብኝ መስሎኝ ለደቂቃ ግር  አለኝ። ፕሮፌሰሩ “እውነት እሱ እንዳለው እናጸድቃለን ብላችሁ ነው?“ ብለው በፈግታ ጠየቁኝ። ከላይ የጠቀስኩትን ደግሜ ጠቀስኩት።

ፕሮፌሰሩ የሁላችንንም ሀሳብ ካስጨረሱ በኌላ፤ ”ኢትዮጵያዊው ስርአተ ፍታት የተፈጥሮ ነጸብራቅ እንጅ በክርስቶስ የማመንና ያለማመን አይደለም። እኛ እንግሊዞች  በቅኝ ግዛት በቆየንባቸው አገሮች ያረመናቸው ብዙ ባህሎች እንዳሉ ያጠፋናቸውም አሉ” ብለው፦ ንግግራቸው በመቀጠል “ሰው ሲታመም  ከቤት እንዳለ ነፍሱ ብትወጣ በቤተ ሰቡ ላይ ተደራራቢ ሞት ያስከትላል  ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ ነበረ። ቤተሰቦቹ ሳይሞት እግሩን በረዥም ገመድ አስረው ጫካ ይጥሉታል። ገመዱ ብቻውን እስኪመጣ ድረስ ጧት ጧት እየተነሱ የገመዱን ጫፍ ይስቡታል። ገመዱን መጎተት ከከበዳቸውና ብቻውን ካልመጣ አልሞተም  ብለው ምርር ያለ ልቅሶ ያለቅሳሉ። ገመዱ ተስቦ ብቻውን ከመጣ ሞቶ አውሬ በልቶታል ብለው ይደሰታሉ ከብት ያርዳሉ ይበላሉ ይጠጣሉ ይዘፍናሉ። እኛ እንግሊዞች  በቅኝ የገዛናቸውን አፍሪካውያንን አሁን ባያችሁት ስርአት ነጭ ልብስ ለብሰው እየተዝናኑና ውሀ እየጠጡ ቤተ ሰቦቻቸው ሲሞቱ  በዚህ ስርአት እንዲሸኙና እንዲቀብሩ አደረግናቸው“ አሉና፦ ፊታቸውን ወደነ እነ ዮሐንስ ሁንቄ አዙረው፤ “እናንተ  ከራሳችሁ ከኢትዮጵያ ስርአተ ፍታት ወጥታችሁ ከኛ ከእንግሊዞች ተወርሶ ያያችሁትን አደነቃችሁ።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሞተ ሰው የሚሸኝበት ፍትሀት እንደኛ እንደ እንግሊዞች በመዝናናት ሳይሆን፤ ከነ ነፍሱ እግሩን አስሮ ለጫካ አውሬ በመወርወርም ሳይሆን አስተርአየ ያቀረበው የኢትዮጵያው ባህል ይመረጣል። እናንተ ግን ከራሳችሁ ሰባዊ ባህል ስርአተ ፍታት ርቃችኌል”  ብለው ዘጉት። ወደራሴ ትዝብት ልመለስና፦Lewis የተባሉ ደራሲ Mere Christianity በሚል ርእስ “Our experience is colored through and through by books and plays and the cinema, and it takes patience and skill  to disentangle  the things we have really learned from life for ourselves.”(page 110) እንዳሉት፦ ከመንደሬ እያየሁ ባደኩት፤ ካብነቱ መምህራንና ከውጭ በተማርኩት ትዝታየ፤  አሁን በነ አቶ በቀለ ገርባ ኮረዳ የታወጀውን ፍታት እንድቃኘው አስገደደኝ።

ወያኔ ሲገድል ሲያስር ሲያሳድድ አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዲዳ ሆነው የኖሩ ሁሉ አፋችንን  ፈታን ቢሉም፤ የታፈኑትን ወጣቶች ፍቱ ለማለት አሁንም አንደበታቸው እንደታሰረ አፋቸውም እንደታፈነ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ “ሚስቶቻችሁን ፈታችሁ እኔን አግቡኝ” የምትል አፍረት ቢስ ኮረዳ ብቅ ማለቷ የዘመኑን ክፋት እንድረዳው አደረገኝ። የቅኔ ትምህርት ቤቴንም አስታወሰኘ። በቅኔ ትምህርት ባህል መምህራኑ ተማሪወቻቸው ለሚቀምሩት ቅኔ መሰረትና መነሻ የሚሆን ቅኔ ይዘርፋሉ። በመምህራችን የተዘረፈውን ቅኔ ምስጢሩን አሰካኩን ቀመሩን እናጠናል። በዚያ ልክ በመምህሩ እና በብዙ አድማጭ ፊት የየራሳችንን ቅኔ እየቀመርን ተራ በተራ እናቀርባለን።

የምንቀምረው ቅኔ  ጸያፍ ፍርቅ ከሆነ፤   ሁሉ ይማርበት ዘንድ እዚያው ላይ ባድማጩ ፊት መምህሩ ያርማሉ። የሰው ቅኔ ሰርቀን (Plagiarism ) ካቀረብን እንደክብደቱ እንጨት ለቅመን እንድናቀርብ እንቀጣለን።  መምህሩ በዘረፉት ቅኔ ልክ ያላንዳች ፍርቅ ጸያፍ ከቀረበ ወደሚቀጥለው እርከን እንድንቀጥል እንታዘዛለን። ይህች አውታታ የነ ዶክተር መራራ ተማሪ፤ አማራ ወንዶች  አግብተው ወልደው የልጅልጅ አይተው የኖሩትን የኦሮሞ እናቶች የልጆቻቸው አባቶች እየፈቱ እሷን እንዲያገቡ  መምህሮቿ በዘረፉላት ልክ የቀመረችውን የፍች ቅኔ ባደባባይ አቀረበች። ከላይ እንዳልኩት፤ ግጥሙ ተፋልሶ  ዜማው ተሰብሮ የቀረበ ቅኔ ይበል ተብሎ አይታለፍም። ሁሉም ይማርበት ዘንድ የተፋለሰው ግጥም የተሰበረው ዜማ እዜው በመምህሩ ይታረማል።  በተነገረበት ቅጽበት መምህሩ ሳያርሙት ካለፉት ለተማሪውም ለራሳቸው ለመምህሩም እንደ እፍረት መቁጠር የተለመደ ስርአት ነው።

ከእለታት አንድ ቅን የቅኔ ስጦታ የሌለው ተማሪ እጅ እግር የሌለው ቅኔ ቀምሮ ከመምህሩ ቀረበ።  ሳያርሙ ዝም ብለው አሳለፉት። የገባው የቅኔ ሰው መምህሩ ሳያርሙ ተማሪውን መልቀቃቸው ከሞራል ውጭ መሆናቸውን በቅኔ አሳፈራቸው። መምህሩም ሸፍጠኛ ስለነበሩ፤ “የሚታረም እኮ በውስጡ ንጹህ ቡቃያ ሲኖር ነው። ሁሉም አርም ሲሆን ከመተው በቀል ምኑ ይታረማል? ብለው በተማሪው ሁሉ ፊት ተማሪያቸውን አሳፈሩ።

አንድ ታዛቢ፦

“የልጅ አገረድ አውታታ

በመንታ መንገድ  እራቍቷን ተኝታ

ተነሽ የማይሏት ምነው፦

ይህ ሁሉ ዓለም አፈር ነው”  ብሎ የቆየ ግጥም በመጥቀስ፤ ተማሪው እጅ እግር የሌለው ቅኔ በማቅረቡ፤ መምህሩም ሳያርሙ በማለፋቸው ሁሉም ማፈር የሚገባቸው መሆናቸውን ነገራቸው።

አንዱ ትዝታ ሌላውን ትዝታ ይጎትታልና፤ ሌላ አንዲት ኮረዳ ትዝ አለችኝ። አቻዋ የሆነ ፍቅረኛ ገጠማት። ተዋደዱና መጋባት ፈለጉ። የኮረዳዋ ቤተሰቦች ጋብቻውን አልተቀበሉትም። ኮረዳዋ የሚያማልዱ ቄስ  ፈልጎ ወደ ቤተ ሰቧ እንዲልክ ፍቅረኛዋን መከረችውና አንድ ቂስ ላከ።  ቄሱ ሀላፊነታቸው በተገቢው መንገድ ባለመወጣታቸው ወላጆቿ ጋብቻውን አልተቀበሉት። ፍቅረኛዋ ተስፋ መቁረጡን ነገራት። እሷም ተስፋ ሳይቆርጥ በፍቅሩ እንዲቀጥል፦

“ጠንክር በርታ ፍቅሬ ቢሆንም ባይሆንም 

ሰው ቢማር ቄስ እንጅ፤  ሰው መላክ አይሆንም” ብላ ተቀኘች።

ይህች ኮረዳ ሴት፤  ተልእኮውን የረሳ ሰው ቢማርና ቢቀስስ ፋይዳ እንደማይኖረው ተረድታለች።  “ክፉ ነገርን የሚያስተምር ሰው ጥበብ የለውም። ለኃጢአተኞች ሰዎች ምክር ጥበብ የላትም”(ሲራክ 19፡19)። የሚለው የሲራክ ምክር የገባት ትመስላለች። ቅኔዋ ቄስም ሆነ ተማርኩ የሚል  ለራሱ ለሆዱ እንጅ ለህዝብ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን እንደማይጠቅም በዚህ ወቅት ላለ ሰው የሚያስገነዝብ ነው።

አንባብያን የማትሰለቹኝ ከሆነ፤ ይጠቅማል ብየ ያስብኳትን ሌላዋ  ኢትዮጵያዊት ብልህ ሴት የተናገረችውን ላክልላችሁ።   ”ፍታት ፍታት“ እያሉ በሚያስተምሩ ከፋፋይ መምህራን ጭንቅላቱ ዞሮ ባሏ ሊፈታት አሰበና ተቸገረች።  ”እባከዎ ይምከሩልኝ“ ብላ ወደ ቄሱ ሄደች። ቄሱ በድግስ የታጀበ ፍታት ልባቸውን ሰርቆት ኖሮ ፤ ማስታረቁን ትተው “ፍታት! ፍታት!” ብለው ወደ ተዝካሩ ሄዱ፦ እሷም ታዘበችና፦

“ምን ያሉ ቄስ ናቸው፤ ተዝካር የለመዱ፤

ያስታርቁኝ ብላቸው ፍታት ብለው ሄዱ” ብላ ተቀኘች ።

እነ አቶ በነቀለ ገርባ ሆይ!በሸፍጣችሁና በቅጥፈታችሁ በካናችኋቸው ቄሶች የደቆነች ፍቱ የምትለው ይህች ኮረዳ፤ ሸፍጣችሁን ተረድታ ከላይ የተጠቀሰውን እየጠቀሰች የምትሳለቅባችሁ ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም። እንግሊዛዊው መምህሬ “ከራሳችሁ ባህላዊ ፍታት ወጥታችሁ ከኛ የተወረሰውን ፍታት አደነቃችሁ።  ወደ ተፈጥሮ ሰባዊነት የሚጠጋው ግን የራሳችሁ ኢትዮጵያዊው የፍታት ባህል ነው“ እንዳሉት የወገናችሁን እግር እያሰራችሁ ከነነፍሱ ለጫካ አውሬ መወርወራችሁንና ባውሬ በመበላቱ የሚሰማችሁን ደስታና ፈንጠዝያ አቁማችሁ፤ በወገናቸው ደምና ፈርስ ዙሪያ እየጮሁ በማልቀስ ወገናቸውን ከሚፈቱ እንስሳት ተማሩ  እያልኩ እሰናበታችኌለሁ።

ጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም.

[email protected]