DW : በአዳማ ከተማ ብቻ ለሦስተኛ ጊዜ ከአባላት እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ትናንትናም ሳይሳካ መቅረቱን ነው አቶ በቀለ ገርባ የተናገሩት። በከተማዋ የሚገነውን ስቴዲየም ጨምሮ የመንግሥት የመሰብሰቢያ አዳራሾች በአጠቃላይ ፓርቲው እንዳይጠቀምበት በመከልከሉ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ወደ መጡበት ለመመለስ መገደዳቸውንም አቶ በቀለ ጨምረው ገልጸዋል።
ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ጨምሮ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብትን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የተደረሰውን ስምምነት የሚጣረሱ ተግባራት በመንግሥት ወገን እየተፈጸመ ነው ሲሉ አቶ በቀለ ይከሳሉ። የመንግሥት ኃይሎች የመንግሥት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ከመከልከል ባሻገር ግለሰቦች የመሰብሰቢያ አዳራሾቻቸውን እንዳያከራዩዋቸው ጭምር አስፈራርተዋቸዋልም ይላሉ።
በአዳማ ከተማ ከተደረገው ክልከላ ባሻገር አስቀድሞ በኦሮሚያ ክልል ሌሎች አካባቢዎችም ጠንከር ያለ ክልከላ ገጥሞናል ያሉት አቶ በቀለ እንቅስቃሴያቸውን ለመገደብ መንግሥት የሚያደርገው ተጽዕኖ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ተስፋ ማድረግ እንደሚቸግራቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአዳማ ከተማ ኦፌኮ የመሰብሰብ መብቴ አልተከበረልኝም ለሚለው አቤቱታ፤ «የኦፌኮንም ሆነ የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ለመገደብም ሆነ ለመከልከል መንግሥት መብቱ የለውም፤ የከተማው አስተዳደርም ክልከላ አላደረገም» የሚሉት ደግሞ የከንቲባው ከፍተኛ አማካሪ አቶ ናስር ሁሴን ናቸው። እንደ አቶ ናስር ችግሩ የተፈጠረው ኦፌኮ አዳራሽ ለመከራየት ከግለሰቦች ጋር በፈጠረው አለመግባባት ነው።
ከትናንትናው የፓርቲው ስብሰባ መስተጓጎል በፊት ሁለት ጊዜ ተፈጠረ የተባለውን ክልከላም እንደማይቀበሉት አቶ ናስር ይናገራሉ። የከተማዋን ስቴዲየም ጨምኦፌኮ ከአባላትና ደጋፊዎቼ ጋር መገናኘት አልቻልኩም አለሮ ያሉትን አዳራሾች አስቀድመው በማሳወቅ መጠቀም ካለመቻል የሚፈጠሩ ክፍተቶች ለስሞታው መነሻ እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይም የትኛውም ፓርቲ አስቀድሞ በማሳወቅ ሊገለገልባቸው እንደሚችል አስረድተዋል።
ኦፌኮ ትናንት በአዳማ ከተማ ሊያደርገው የነበረው ስብሰባ ናፍያድ በተባለ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ መሆኑን ዶይቸ ቬለ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። የከንቲባው ከፍተኛ አማካሪ በሰጡት ምላሽ ኦፌኮ ከትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ጋር ባለመስማማት የተፈጠረ ችግር ነው ለሚለው ምላሻቸው የትምህርት ቤቱን ባለቤት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።