በአሜሪካ የተዘጋጀው የኅዳሴ ግድብ ሥምምነት ለሌላ ጂኦፖለቲካል ዓላማ ማስፈጸሚያ ገጸ-በረከት እና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል ኢትዮጵያ መጠንቀቅ አለባት – ዶ/ር ደብረጺዮን

Image may contain: 1 personDW : ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ እንዲፈርሙት በአሜሪካ የተዘጋጀው ሥምምነት «ለሌላ ጂኦፖለቲካል ዓላማ ማስፈጸሚያ ገጸ-በረከት እና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል» ኢትዮጵያ መጠንቀቅ እንደሚገባት የትግራይ ክልል ምክትል-ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) አስጠነቀቁ። ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ የአድዋ ድል 124ኛ ዓመት መታሰቢያ በትግራይ ክልል ሲከበር ባደረጉት ንግግር «በውሉ የሰፈሩ ሐሳቦች እና ቃላቶች» ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሜሪካ «ስምምነት ሳይፈረም የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጨረሻ ሙከራ እና የውኃ ሙሌት ሊከናወን አይገባም» የሚል መግለጫ ካወጣች በኋላ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ላለፉት ወራት በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ «ታዛቢነት» ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ከፍሬ ሳይደርስ ሳንካ ገጥሞታል። ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተዘጋጀው ስምምነት «የሦስቱ ሃገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም» ስትል እንደማትቀበለው አስታውቃለች። ግብፅ በበኩሏ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ የተዘጋጀው «ፍትኃዊ እና ሚዛናዊ» ስምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ ተሳትፎ ያደረገችበት ነው ብላለች።

የትግራይ ምክትል-ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን «የኅዳሴ ግድብን አስመልክቶ የቀረበውን የውል ሰነድ ቆም ብለን ከውጫሌ ውል በመማር፤ በውሉ የሰፈሩ ሐሳቦች እና ቃላቶች በሉዓላዊነታችን ላይ የመጡ ከዚያም አልፈው ለሌላ ጂኦፖለቲካል ዓላማ ማስፈጸሚያ ገጸ-በረከት እና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት መፈጸም ይገባዋል።» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ደብረ ፅዮን በንግግራቸው «በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና በኅዳሴ ግድብ ዙሪያ በታላላቅ አገሮች ብቻ ሳይሆን በአላፊ አግዳሚው እየታዩ ያሉ ጣልቃ-ገብነቶች ከነ መነሻ ምክንያታቸው ታውቀው ተገቢ ጥንቃቄ በመውሰድ ወቅታዊ፣ በሳል እና የማያዳግም ምላሽ መስጠት ይገባል» ብለዋል።
የኢትዮጵያ ርዕሠ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተከበረው የአድዋ መታሰቢያ ደብረ ፅዮን «አሁን በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት እና በብሔራዊ ማንነታችን፤ ብሔራዊ ክብራችን እና ሉዓላዊነታችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስተካከል የአድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነው የውጫሌን ውል በአስተማሪነቱ ወስደን ልንጠቀምበት ይገባል» ሲሉ ተደምጠዋል።

«የድሮ ቅኝ ገዢዎች የሚፈልጉትን አገር ወረው በጉልበት በመሣሪያ ይገዙ ነበር» ያሉት ደብረ ፅዮን «የአሁኑ ቅኝ ገዢዎች ግን አገሮች የፖሊሲ ነፃነት እንዳይኖራቸው በማሻሻያ (ሪፎርም)፣ በብድር እና እርዳታ ስም ለእነሱ የሚጠቅም ለውጥ እንዲደረግ በመጫን፤ በቁጥጥራቸው ሥር በማስገባት ዜጋው በመሰለው አገሩን እንዳያስተዳድር የሚያደርጉ መሆኑን» ኢትዮጵያውያን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።