አዎ! ታላቁ የህዳሴ ግድብ የእኔ ነው!
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሦስትዮሽ ስብሰባ ዙሪያ ከአንድ የውጭ ሃገር ጋዜጠኛ “ግብጽ ካልተስማማች ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ መሙላት ታዘገያለችን” ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄ “ምን ነካህ ግድቡ እኮ የእኔ ነው” ሲሉ የመላ ኢትዮጵያውን ምላሽ የሆነውን መልስ ሰጥተዋል።
አውነት ነው አሁንም በኩራት እንደግመዋለን አዎ ግድቡ የእኔ የኢትዮጵያዊው ነው!
ለማንም ግልጽ እንደሆነው የአባይ ወንዝ ከሚያመነጨው ውሃ 85 በመቶውን የምታበረክተው ሃገራችን ኢትዮጵያ ናት። ይኸን ውሃ እያበረከተች ለዝንተ ዓለም ግን ውሃውን ሳትጠቀም የበይ ተመልካች ሆና ኖራለች።
የአባይ ወንዝ በደጃፋቸው እያለፈ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት በማገዶ ጪስ ዓይናቸው የሚለበለብ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውም እኛ ኢትጵውያንን የሚያንገበግበን የአደባባይ ሐቅ ነው።በወንዙ ዙሪያ ሃገራችንን ያገለሉ እና ዓይን አውጣነት የተስተዋለባቸው ሁለት ኢፍትሐዊ ስምምነቶች ተደርገዋል።
ይኸ በየትኛውም ዓለም ያልታየና ስግብግብነትና እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል እሳቤን ያዘለ ውል ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ እንደተደረገ ተደጋግሞ የተገለጸ ጉዳይ ነው።
“በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” እንደሚለው ብሂል ኢትዮጵያውያን በገዛ ሀብታቸው የበይ ተመልካች ሆነው ዘመናትን በቁጭት አሳልፈዋል። አባይን በግጥምና በዜማ በማወደስና በመንቀፍም አንድ ቀን ታሪክ እንደሚቀየርም ተንብየዋል። ትንቢቱ መሬት ላይ ሳይወድቅም መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም የታላቁ ህዳሴ ግድብን በአባይ ወንዝ ላይ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በመጣል የአባይ ወንዝ ላይ የነበረው የቁጭት ታሪክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለወጠ!
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከጉድለታቸው በመቆጠብ በጥረታቸውና በላባቸው ዕውን ያደረጉትና አንድ የሃይማኖት አባት በግድቡ መጀመር ሰሞን እንደተናገሩትም “በማህጸን ካለ ሕፃንና በመቃብር ካለ አስክሬን ውጪ” ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቆሙለትና የደገፉት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
ይህ ግድብ በኢትዮጵያዊያን ሲወጠንም የሃገራችንን በሀብቷ የመጠቀም የማይገሰስ መብትና ሉዓላዊነቷን ታሳቢ ከማድረግ በዘለለ የታችኛውና የተፋሰስ እንዲሁም የጎረቤት ሃገራትን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ነው። ግድቡ ንጹሕና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት በማምረት እስከአሁን በጨለማ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ከመታደጉ በተጨማሪ ለታችኛው የተፋሰስ ሃገራትና ለጎረቤቶቻችንም ጭምር በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፋይዳ ብዙ ግድባችን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ግድቡ ግብፅ ላይ አላግባብ በትነት የሚባክነውን የዓባይ ወንዝ ውሃ መጠን የሚያስቀር፣ በተለይም ሱዳንን ከጎርፍ ስጋት የሚታደግና ከዓመት እስከ ዓመት የወንዙ የውሃ ፍሰት ሳይቆራረጥ እንዲፈስ የሚያደርግ ድንበር ተሻጋሪ ጥቅም ያለው ለኢትዮጵያና አፍሪካ ህዳሴ መሰረት የሆነ ታላቅ ግድብ ነው።
ገና ከግድቡ ጅማሬ አንስቶ ብቻቸውን የመጠቀም ስግብግብነት መለያቸው የሆኑ ኃይሎች የግድቡን ግንባታ ቢቃወሙም እንደ ሱዳን ያሉ ፍትሐዊና እውነተኛ ሀገሮችን ጨምሮ በርካቶች የግድቡን ፋይዳ ቀድመው በመረዳት ድጋፋቸውን ችረውታል። ከግድቡ መበሰር አንስቶ ኢትዮጵያም ማንንም ሳትጎዳ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን እንደምታረጋግጥ በተደጋጋሚ አስታውቃለች።
ሉዓላዊነቷን በማንም እንዳማታስደፍርም አበክራ አስረድታለች። አሁንም ቢሆን በዚህ መርህ መሰረት ለትብብርና ውይይት በሯን ክፍት አድርጋ የግድቡን ፍጻሜ ለማቃረብ ሌት ተቀን በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ይሁንና አሁንም በተለይም ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ከዘመኑ ጋር የማይሄድ የስግብግብነት ፖሊሲን የሚከተሉ ኃይሎች የትብብርና ውይይት መንገዶችን የሚዘጉ አደናቃፊ ሃሳቦችን በማቅረብ በግድቡ ዙሪያ በጋራ ለመሥራትና ለመጠቀም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ እየሞከሩ ይገኛሉ።
ይሁንና ለማንም ግልጽ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ በአባይ ወንዝ መጠቀምና ታላቁ የህዳሴ ግድብን የማስተዳደር ጉዳይ የማይገሰስ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መብት መሆኑ ነው። ግድቡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውን አንጡራ ሀብት የተገነባ እንደመሆኑ ግድቡ የማንም ሌላ አካል ሳይሆን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ብቻ ነውና! ለዚህም ነው ደጋግመን አዎ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ የእኔ ነው” የምንለው!
አዲስ ዘመን