ለዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚል በ10 ዓመታት ዉስጥ 12 መሰረተ ድንጋዮች ተጥለዋል። የተሰራ ነገር ግን የለም

DW : የዓድዋን ድል በታሪክ ለማቆየት ሲባል በዓድዋ እና አካባቢዋ ይገነባሉ ተብለዉ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸዉ ፕሮጀክቶች አስታዋሻ ማጣታቸው ተመለከተ፤ በከተማዋ ነዋሪዎችም ቅሬታቸዉን እየገለፁ ነዉ። የዓድዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚለዉ ከሆነ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ 12 መሰረተ ድንጋዮች የዓድዋን ድል ለማሰብ ይሰራሉ ለተባሉ ፕሮጀክቶች ቢቀመጡም አሁን ድረስ የተሰራ ወይ የተጀመረ አንድም ፕሮጀክት የለም፡፡

የዓድዋን ድል ለማስታወስ ተብሎ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ የጀግኖች መታሰቢያ ሐወልቶች፣ ፓርክ፣ ቤተ-መዘክር እና ሌሎች በተለያየ ግዜ ይሰራሉ ተብሎ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሟቹ የቀድሞ ፕሬዝደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩውሬ ሙሴቬኒ፣ የአፍሪካ ሕብረት የአንድ ወቅት ሊቀ መንበር ፓትሪክ ማዚማካ እና ሌሎች ባለስልጣናት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዉ እንደነበር ከመቀሌ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡ 124ኛ የዓድዋ ድል መታሰብያ ሰኞ ይከበራል፡፡