ዜጎች ወደ ቅያቸው ሊመለሱ መሆኑ ተገቢ ነው- ግን ዘላቂ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል #ግርማ_ካሳ

አቶ ለማ መገርሳ በአማርኛ ፣በተለይም ከኦሮሞ ክልል በተፈናቀሉ ወገኖች ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለጻ ሰጥተዋል። በገለጻው ተደስቻለሁ። ዶር ነጋሪ ሌንጮ የኦሮሞ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ኦሮምኛ በማይናገሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለመደባበስ ነበር የሞከሩት። እንደውም አይናቸውን በጨው አጥበው፣ ተፈናቃዮች በፍቃዳቸው ለቀው የሄዱ እንጂ ማንም እንዳላፈናቀላቸው ነበር የገለጹት።

ከኦሮሞ ክልል በተፈናቀሉ ወገኖች ምክንያት፣  አቶ ለማ መገርሳ ከሁሉም አቅጣጫዎች ከፍተኛ ተቃዉሞ ደርሶባቸዋል።ጠንካራ ትችት ሲሰነዝሩ ከነበሩት ወገኖች መካከል አንዱ እኔው ነኝ። ባህር ዳር ሄደው በነበረበት ጊዜ ያገኙት ትልቅ ተቀባነይት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሽቆለቆለበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። እዉነት ለመናገር ከሆነ በጥቂት ጊዜ በአንዴ ጣራ ደርሶ ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ መሬት የተፈጠፈጠ እንደ አቶ ለማ ይኖራል ብዬ አላስብም። አቶ ለማ ከጥቂት ወራት በፊት እንደ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ጃካም ኬሎ … የኢትዮጵያ ጀግና ተደርገው ነበር የሚቆጠሩት። በኋላ ግን ከነሌንጮዎች፣ ከነ ዳዎድ ኢብሳ ምድብ ወረዱ። በተለይም ከባህር ዳር በኋላ፣ ሰው ብዙ ነገር ሲጠብቅ፣ በአቶ ለማ ክልል ውስጥ መጤ ናችሁ እየተባሉ ዜጎችን ማፈናቀሉ መብዛቱ፣  ብዙዎችን ማስገረም ብቻ ሳይሆን አስደንግጧል።

በተፈናቃዮች ዙሪያ በአማራ ክልል መንግስትም ላይ ብዙ ተቃዉሞ ተጽፏል። በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለውን ቁጭትና  ንዴት የተረዱት የአማራ ክልል ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ከኦሮሞ ክልል መንግስት ጋር እንደተነጋገሩበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ራሳቸው በቀጥታ ከአቶ ለማ መገርሳ ጋር ተወያይተዋል። የኦሮሞ ክልል መንግስት ነገሮችን ከመደባበስ አስፈላጊውንና አስቸኳይ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ የጠየቁት የአማራ ክልል አመራሮች፣ ባለኝ መረጃ፣  ያ ካልሆነ ግን የብአዴን እና የኦህዴድ መቀራረብ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ነው ለኦህዴዶች የነገሯቸው። ብአዴን ድጋፉን ካነሳ በማናቸውም ጊዜ ኦህዴድ በፌዴራል ደረጃ ያገኛቸውን ስልጣኖች በቀላሉ ሊያጣ እንደሚችል የሚታወቅ ነው። ከብአዴን ጋር አብሮ መስራት ካልቻለ፣ ኦህዴድ በፌዴራል መንግስት ውስጥ ማይኖሪቲ ነው። ያንንም እነ ለማ መገርሳ ጠንቅቀው ስለሚያወቁ፣ የብአዴንን ጥያቄ ከማስተናገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም።

አቶ ለማ መገርሳ ከአቶ ገዱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ  በአማርኛ መግለጫ የሰጡት። ወሳኝ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ነው የነገሩን። ዜጎችን ያፈናቀሉ ፣ እንዲፈናቀሉ የረዱ፣ ሲፈናቀሉ ዝም ያሉ፣ ዜጎችን ያልጠበቁና በሃላፊነት ላይ ያሉ ብዙ የኦህዴድ አመራሮች ላይ፣ መንግስታቸው እርምጃ እንደወሰደ የገለጹት አቶ ለማ፣ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባትን ሕዝቦቻችን ናቸው ብለዋቸዋል።የተፈናቀሉ ሁሉ በአንድ ጊዜ ውስጥ ወደ ቅያቸው እንዲመለሱ አስፈላጊዉን ዝግጅት እንዳደረጉም ነው ያሳወቁት።

ወገኖች፣ ግፍ ሲፈጽም፣ አድልዎ ሲደረግ ዝም ማለት ትልቅ ስህተት ነው። አቶ ለማ እንዲህ አይነት መግለጫ እንዲሰጡ ያስገደዳቸው ዜጎች በመጮሃቸው፣ ድምጻቸውን በማሰማታቸው ነው።

“አቶ ለማ ይሄን ተናገሩ” ማለት ነገሮች ተስተካከሉ ማለት አይደለም። የተፈናቀሉት ወደ ቅያቸው ቢመለሱም፣ ነገ እንደገና እንደማይፈናቀሉ ዋስትና የላቸውም። ዛሬ የተወሰኑ የኦህዴድ አመራር አባላት ቢባረሩም፣ እነዚህ የኦህዴድ አባላት ሲያራመዱት የነበረውን ዘረኛ አስተሳሰብ መጀመሪያዉኑ እንዲኖራቸው ያደረገው የዘር ስርአቱና ሲስተሙ ካልተስተካከለ፣ የተባረሩትን የሚተኩት ያው ነው የሚሆኑት። ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ነው የሚሆነው። በመሆኑም የኦሮሞ ክልል መንግስት፣ ላይ ላዩ ከሚደረጉ ተግባራት ባለፈ፣ ብዙ በአስቸኳይ ማስተካከል ያለበትና ማስተካከል የሚችላቸው ጉዳዮች አሉ።

አንደኛ – በኦሮሞ ክልል ኦሮምኛ የማይናገሩ ፣ በብዛት አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ፣ ከ50፣ ከ60፣ ከ80 ..በመቶ በላይ የሆኑባቸው ወረዳዎች፣ ዞኖች፣ ቀበሌዎች አሉ፡ በነዚህ አካባቢዎች ሕዝቡ በአማርኛ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት መቻል አለበት። ለምሳሌ በአዳማ 75% አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ ኦሮምኛ ብቻ የከተማው የስራ ቋንቋ የሚሆንበት ምክንያት የለም። በአጠቃላይ አማርኛ ከኦሮሞኛ ጋር የስራ ቋንቋ መሆን አለበት።

ሁለተኛ – ለምሳሌ በአማራ ክልል ኦሮሞዎች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች በኦሮምኛ ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ። በኦሮሞ ክልል አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መደረግ አለበት።

ሶስተኛ – የኦሮሞ ክልል ሕግ መንግስት አፋኝና ዘረኛ ሕገ መንግስት ነው። የኦሮሞ ክልል ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ያ ማለት ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች በአገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ናቸው። እንደ እንግዳ ነው የሚታዩት። ማንም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የአገሪቷ ግዛት በነጻነት እንደ አገሩ ነው መኖር ያለበት።መጤ የሚባልበት ምንም ምክንያት መኖር የለበትም።

 

 

https://www.facebook.com/118697174971952/videos/718678284973835/


► መረጃ ፎረም - JOIN US