ዓድዋ የአንድነታችን ድርና ማግ፤ ከዓድዋ ድልድይ እስከ ሶሎዳ ተራራ፡፡
(አብመድ) ‹‹ዓድዋ ምንም ዓይነት የተጣመመ ታሪክ የለውም፤ እኛው ካላጣመምነው በስተቀር፡፡›› ተጓዥ ጋዜጠኞች
ዘመን በዘመን ይተካል፤ ትውልድ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አሻራውን እያስቀመጠ ያልፋል፡፡ ማንም ሆነ ምንም በዚች ምድር ላይ ዘለዓለማዊ ይሆን ዘንድ አልተፈቀደለትም፤ ሁሉም የዚች ዓለም ተራ መንገደኛ ነውና፡፡ በዚህ የትውልድ እና የዘመን አሻራ ውስጥ ግን እልፎችን ሸኝተው፣ እልፎችን ተቀብለው እና እልፍ አስተናግደው ታሪካዊ ዳራቸው የማይደበዝዙ፣ ትውልድን እና ሀገርን በአንድ የሚገምዱ የታሪክ አውራዎች አይጠፉም፤ ልክ እንደ ዓድዋ፡፡
ዓድዋ የአንድ ጀንበር ጦርነት እና የሁለት ሀገራት ውጊያ ብቻ አይደለም፡፡ ዓድዋ የወራሪ ተወራሪ ሥሪትን ከመሠረቱ ሰብሯል፤ የነጮችን ፍፁማዊ የበላይነት ጥርጣሬ ውስጥ ከትቷል፤ የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ቀንዲል፣ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት ቀንበር ሰባሪ እና የጭቁን ሕዝቦች ትምክህት ነው፤ ዓድዋ፡፡ 124 ዓመታትን ባስቆጠረው የዓድዋ ድል ጉዞ ውስጥ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን ለሀገር ነፃነት የሚከፈልን መሰዋዕትነት ለዓለም ሕዝብ አሳይተውበታል፡፡
የዘንድሮው 124ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ የበዓሉ አከባበር አንዱ አካል የሆነው እና ከአዲስ አበባ ዓድዋ ድልድይ እስከ ሶሎዳ ተራራ የሚደረገው ጉዞም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተከናወነ ነው፡፡
የካቲት 17/2012 ዓ.ም ከ300 በላይ የሚደርሱ ከሁሉም ክልሎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ከተለያዩ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የተውጣጡ ጋዜጠኞችን የያዘ የልዑክ ጉዞ ጀምሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዓድዋ ድልድይ አካባቢ በመገኘት ተጓዦችን ‹‹መልካም ጉዞ›› ብለው የሸኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ናቸው፡፡ ሚኒስትሯ ‹‹የዓድዋ ጦርነት ውሳኔ ከተላለፈባት አዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ድል ችቦ ብስራት ሶሎዳ ተራራ የምታደርጉት ጉዞ የአሁኗን ኢትዮጵያ የለውጥ ምዕራፍ ያመላክታል›› ነው ያሉት፡፡
ከእንጦጦ ተራራ ስር አዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ተራሮች፣ ከዓድዋ ድልድይ እስከ ሶሎዳ ተራራ፣ ከአንጎለላ እስከ አንኮበር፣ ከመርሆ ግቢ እስከ አይጠየፍ፣ ከወረኢሉ እስከ ውጫሌ፣ ከይስማ ንጉሥ እስከ ማይጨው ተጓዦቹ ታሪክን እየዘከሩ ትናንትን በዛሬ መነፅር ይመረምራሉ፡፡
‹‹ዓድዋ ምንም ዓይነት የተጣመመ ታሪክ የለውም፤ እኛው ካላጣመምነው በስተቀር›› የሚለውን አስተያዬት የሰጠን የንጋት ሚዲያው ጋዜጠኛው ምኒልክ ፋንታሁን ነው፡፡ ‹‹ዓድዋ ዛሬ ቀና ብለን እንድንሄድ ያደረገ ታሪክ በመሆኑ ያለምንም መሸራረፍ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል›› ብሏል ጋዜጠኛው፡፡ ከኤል ቲቪ የመጣችው ተጓዥ ጋዜጠኛ ብርቱካን መንገሻም የጋዜጠኞች ዘገባ የታሪክ ሰነድ በመሆኑ ዓድዋን እና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ መርምሮ እና አንብቦ መረዳት መዘግብ እንዳለባቸው ትመክራለች፡፡
ከተራ ንትርክ እና አሉባልታ ወጥቶ ቅደመ አባቶቻችን ለሀገር አንድነት እና ነፃነት የከፈሉትን መስዋዕትነት በመዘከር ትውልዱ ማንነቱን እንዲያውቅ ለማድረግ እንደሚሠሩም ነው ተጓዥ ጋዜጠኞቹ በተለይም ለአብመድ የተናገሩት፡፡
ሰኞ የካቲት 23/2012 ዓ.ም አባት አርበኞች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና የእግር ተጓዦች በተገኙበት በዓድዋ ተራሮች ራስጌ በሶሎዳ ተራራ ጫፍ ላይ የ2012 ዓ.ም 124ኛው ዓመት የዓድዋ ድል በዓል እንደሚከበር በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ እንደገና ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡