ዶክተር አብይ አሕመድ ግጭት ወደባሰበት ደቡብ ክልል ሕዝቡን ለማነጋገር ሊያቀኑ ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት ቀጣይ ሳምንት ወደ ደቡብ ክልል ያቀናሉ

በአገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች በተለይም ደግሞ በሀዋሳና ወላይታ ሶዶ የተነሱትን ግጭቶች ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ገለጹ፡፡

እስከዚያ ድረስ ግን በሰላምና ፍቅር የምትታወቀው የትንሿ ኢትዮጵያ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች፣ የአከባቢው ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ለአካባቢያቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ የጸጥታ አካላትም ህብረተሰቡን ባሳተፈና እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የየአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልል እንሁን በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ስርዓት ያስቀመጠ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በሰላም መጠየቅና ማስተናገድ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

ከወሰን ጋር በተያያዘ በተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት መመለስ ይቻል ዘንድ ይህንን የሚከታተል ኮሚሽን ለማቋቋም መንግስት እያሰበ መሆኑንም ዶ/ር አብይ ገልጸዋል፡፡

ይህ ኮሚሽን ከየአከባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በመቀበል ስር ነቀል መፍትሔ እንደሚሰጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ Ebc