በአወዳይ በመንግሥት እና በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተከሰተ

በአወዳይ ከተማ በመንግሥት እና በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል ግጭት መከሰቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

BBC Amharic : ዛሬ ጠዋት የጠቅላይ ሚንስርት ዐብይ መንግሥት እና ፓርቲን ለመደገፍ የከተማዋ ነዋሪዎች አደባባይ የወጡ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩን መንግሥት በመቃወም መፈክር እየሰሙ የወጡ ሰዎች እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የፖሊስ ባልደረባ ለቢቢሲ እንደተናገረው “ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ለመደገፍ ሰዎች ሰልፍ ወጡ። ከዛ ለምን ለድጋፍ ወጣችሁ የሚሉ ሌሎች ሰዎችም መውጣት ጀመሩ። ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያወግዝ መፈክር በማሰማት ድንጋይ መወርወር ጀመሩ” በማለት የግጭቱን አጀማመር ያስረዳል።

በደንጋይ ተመተው እና በዱላ ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸውን የፖሊስ አባሉ ተናግረዋል።

ይህ የፖሊስ ባልደረባ እንደሚለው ከሆነ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተከሰተውን ግጭት ለመበትን ፖሊስ በርካታ ጥይት ወደ ሰማይ መተኮሱን ተናግረው፤ በፖሊስ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ጉዳት የደረሰበት ሰው ስለመኖሩ የማውቀው የለም ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ “ባለፉት ቀናት የአከባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት ‘ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፋችሁን ለመግለጽ ሰልፍ ውጡ’ እያሉ ነዋሪዎችን ሲያስጨንቁ ነበር” ይላል።

ይህ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ እንደሚለው ከሆነ ዛሬ ጠዋት ላይ ሰዎች ለድጋፍ ሲወጡ እነሱን የሚቃወሙ ሌሎች ሰዎችም አደባባይ መውጣት ጀመሩ።

“በዚህ መካከል ከየት መጡ ሳይባል በርካታ የጸጥታ ኃይል አባላት ከተማዋን ወረው ግርግር ተፈጠረ ከዚያም ወደ ግጭት ተገባ” በማለት ይናገራል።

ይህ የከተማዋ ነዋሪ እንደሚለው ከሆነ ድጋፍ ለመስጠት አደባባይ ወጡ የተባሉት ሰዎች ወደው እና ፍቅደው ሳይሆን በደረሰባቸው ጫና ነው ይላል።

ቢቢሲ በስልፉ ከተካፈሉ ሰዎች ነበረ ስለተባለው ጫና ለማረጋገጥ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም::

በዚህም ‘ለምን ያለ ፍላጎታችሁ ድጋፍ መስጠት አስፈለጋችሁ’ ከሚሉ ሰዎች ጋር መጋጨታቸውን ያስረዳል።

ይህ ነዋሪ እንደሚለው ከሆነ የጸጥታ ኃይሎች በሰዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።

ሌላው የአከባቢ ነዋሪ ግጭቱ የተከሰተው ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመደገፍ በወጡ እና እነሱን በተቃወሙ መካከል መሆኑን ያረጋግጣል። “መንገድ ዝግ ነበር። አሁን ላይ መኪኖች በመከላከያ እየታጀቡ ነው እያለፉ ያሉት” ሲል ያለውን ሁኔታ ያስረዳል።

በዛሬው ዕለት በከተማዋ ስለተከስተው ነገር ከአካባቢው ባለስልጣናትና ከፖሊስ ለማጣራት ቢቢሲ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል::

በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ቢነገርም በትክክል ለማረጋገጥ አልተቻለም።