የሕዳሴው ግድብ ስምምነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረምና ሕዝብ በመንግስት ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጥር የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) እና የህብር ኢትዮጵያ ጥምረት /ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)/ የሕዳሴውን ድርድር አስመልክቶ ጥር 30/5/2012 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ጠይቋል።
የህዳሴ ግድብ የመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻ መሆን የለበትም” ያለው አብሮነት የግብፅ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አሸማጋይ ለመሆን የፈለጉበትን የድርድር ጥያቄ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም መቀበል አልነበረባትም ሲል ወቅሷል።
በግድቡ ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድርም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጥቅም የሚወስን፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ከአስር የማያንሱ የአፍሪካ አገሮችን ጥቅም የሚመለከት ድርድር ነው ያለው ጥምረቱ፣ ከዚህ ድርድር ጀርባ ያሉ አገራት እና ተቋማት በሙሉ ከኢትዮጵያ ይልቅ የግብፅ ወዳጅ የሆኑና ይህንን ድርድር ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ መሆኑ ግልፅ ነው ብሏል።
እንደዚህ ዓይነት ሃይላት የአደራዳሪነቱን ሚና በወሰዱበት ሁኔታም የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የድርድር ውጤት ሊገኝ እንደማይችል አስቀድሞ የታወቀ መሆኑን የገለፀው የአብሮነት መግለጫ፣ ድርድሩ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ወጥቶ የሩቅ እና ገለልተኛ ያልሆኑ ሃይሎች አደራዳሪነት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው ብሎታል።
ድርድሩ ከአገር ብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በጥድፊያ እና ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ መወሰን እንደሌለበት የጠየቀው አብሮነት፣ የድርድሩን ሰነድ በስምምነት ለመቋጨት የተያዘው ግዜ ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘም ጠይቋል። በሚራዘመው ግዜም በቂ መድረክ ተፈጥሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ እና ከአፍሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ግልፅ ውይይትና ምክክር እንዲካሄድ፤ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተልና ይህ ስምምነት ከእሱ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረም በመንግስት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንዲፈጥር አጥብቀን እንጠይቃለን ብሏል።
Source : አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) መግለጫ
ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የሕዳሴውን ድርድር አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ቀን 30/5/2012 ዓ.ም
ቁጥር አብሮነት/005/12
የህዳሴ ግድብ የመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻ መሆን የለበትም!
በቅርቡ በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ አደራዳሪነት በዋሽንግተን ዲሲ የህዳሴውን ግድብ አጠቃቀም አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር በከፍተኛ ፍጥነት እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ድርድር በቅርብ ግዜ ስምምነት ላይ ሊደርስ እና በፊርማ ሊቋጭ እንደሚችል በተደራዳሪ አካላቱ በኩል እየተገለፀ ይገኛል፡፡
ይህ የህዳሴ ግድብ ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ያለው በዋጋ ሊተመን የማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ፕሮጀክት ስለመሆኑ አብሮነት ይገነዘባል፡፡ በዚህ ግድብ ላይ የሚደረገው ይህ የሶስትዮሽ ድርድርም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጥቅም የሚወስን፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ከአስር የማያንሱ የአፍሪካ አገሮችን ጥቅም የሚመለከት ድርድር እንደሆነ አብሮነት ይገነዘባል፡፡
በህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄድ ድርድር ይህንን ያህል ከፍተኛ የሆነ አገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ፣ የግብፅ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አሸማጋይ ለመሆን የፈለጉበትን የድርድር ጥያቄ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም መቀበል አልነበረባትም፡፡ ከዚህ ድርድር ጀርባ ያሉ አገራት እና ተቋማት በሙሉ ከኢትዮጵያ ይልቅ የግብፅ ወዳጅ የሆኑና ይህንን ድርድር ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሃይላት የአደራዳሪነቱን ሚና በወሰዱበት ሁኔታም የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የድርድር ውጤት ሊገኝ እንደማይችል አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡
ይህ ድርድር መጀመሪያውኑ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ወጥቶ በእነዚህ የሩቅ እና ገለልተኛ ያልሆኑ ሃይሎች አደራዳሪነት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው ብሎ አብሮነት ያምናል፡፡
ስለሆነም ይህ ከአገር ብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በጥድፊያ እና ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ መወሰን ስለሌለበት-
የድርድሩን ሰነድ በስምምነት ለመቋጨት የተያዘው ግዜ ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘም፤
በዚህ በሚራዘመው ግዜም በቂ መድረክ ተፈጥሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ እና ከአፍሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ግልፅ ውይይትና ምክክር እንዲካሄድ፤
የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተልና ይህ ስምምነት ከእሱ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረም በመንግስት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንዲፈጥር አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ጥር 30/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ