የታከለ ኡማና የእስክንድር ነጋ ትንቅንቅ እና የባልደርሱ ቁማርተኞች በፈረንሳይ ለጋሲዮን አከባቢ

የታከለ ኡማና የእስክንድር ነጋ ትንቅንቅ እና የባልደርሱ ቁማርተኞች በፈረንሳይ ለጋሲዮን አከባቢ – ምንሊክ ሳልሳዊ

ታከለ ኡማ እስክንድር ነጋ ተወልዶ ባደገበት ፈረንሳይ አከባቢ በመዝመት ቆሞ የቀረውን የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ማስጀመሩ ከተሰማ በኋላ የፖለቲካው ቁማሩ ጦፏል።

በእርግጥ ሕዝቡ በመጭው ምርጫ ድምፁን ለማን እንደሚሰጥ ቢያውቀውም ታከለ ኡማ የፈረንሳይ ለጋሲዮንን ድምፅ ለብልጽግና ፓርቲ ለማግኘት የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱን ተመላልሶ እያስተገበረው ነው።

የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱን ማስጀመሩ ቀና የልማት ስራ ቢሆንም ታከለ ፈረንሳይ አከባቢ የዘመተው የእስክንድር ነጋን ተቀባይነት ለማሳጣት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በእስክንድር ነጋ ጉያ ስር ሆነው ፖለቲካን መደራደሪያና መጠቀሚያ ያደረጉት ቡድኖች እንዳሉ አከባቢው ላይ የሚኖሩ ሰዎች ይናገራሉ።በባልደርሱ ውስጥ እውነተኛ ታጋዮች እንዳሉ ሁሉ ባልደርሱን ጠልፎ ለመጣል ከታከለ ኡማ ጋር በምስጢር የሚደራደሩ ቁማርተኞችም እንዳሉ የፈረንሳይ ወጣቶች ይናገራሉ። ድርድራቸው ቦታና ብድር ማግኘትን ይጨምራል።

ለረዥም አመታት የመንገድ ስራው ፕሮጀክት እንዲቀጥል ጥያቄ ሲያቀርቡ ሰሚ አጥተው እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የእስክንድር ነጋ የአከባቢው ተወላጅ ሆኖ ወደ ተቃዋሚነት መግባቱና አዲስ አበባ ፖለቲካ ላይ ተፅእኖ መፍጠሩ እንደጠቀማቸው ያብራራሉ። እስክንድር ነጋ ባልደርሱን መስርቶ ባይንቀሳቀስ ኖር የሚያስታውሰን አልነበረም ሲሉ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ነዋሪዎች ይገረማሉ።

እንደእኔ እስክንድርም ታከለም ፖለቲካቸውን የማራመድ መብት ቢኖራቸውም ሕዝብን ከለላ አድርጎ የፖለቲካ ቁማር መጫወት ግን አፀያፊ ተግባር ነው። #MinilikSalsawi