ከደምቢ ዶሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የታገቱት ተማሪዎች እንዲለቀቁ እና መንግስት በጉዳዩ ላይ ያሳየውን ቸልተኝነት ለማውገዝ በአዲስ አበባ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነቂስ እንዲሳተፉ ባልደራስ ጥሪ አቀረበ። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በሰጠው አስቸኳይ መግለጫ ሰልፉን እንደሚደግፈው ገልፆ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉት መልዕክቶች ከፖለቲካ ድርጅቶች ነፃ የሆኑና ሰብአዊ መብትን የሚመለከቱ ናቸው ብሏል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ታጋቾች የሚፈቱበትን ሁኔታ የሚጠይቅበት ነው ብሏል።
የሰልፉ አስተባባሪዎች ከፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት የሌላቸውና ተቆርቋሪ ዜጎች መሆናቸውን የገለፀው ባልደራስ የድርጅቱ አባላት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአመለካከትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድባቸው በነቂስ ወጥተው ለታገቱት ተማሪዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት ለጉዳዩ አነስተኛ ትኩረት የሰጠ ከመሆኑ ባሻገር መፍትሔ እንዳይገኝ እንቅፋት ሆኗል ያለው መግለጫው የሰልፉ አላማም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ታጋቾቹ በሰላም እንዲለቀቁና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ በሕግ እንዲጠየቁ ግፊት የሚያርግ እንደሆነ ጠቁሟል።