ቀላል የማይባሉ የታክሲ ሾፌሮች አድማ ላይ መሆናቸውን ሰምተናል – ተሳፋሪዎች

የታክሲ ሹፌሮች አድማ በአዲስ አበባ ?

በያዝነው ሳምንት ከሰኞ ዕለት አንስቶ በአዲስ አበባ ከወትሮው ለየት ያለ የትራንስፖርት ፈላጊዎች ረጃጅም ሰልፍ መኖሩን አስተውለናል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ምልከታ ያደረገ ሲሆን ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ የትራንስፖርት እጥረት መኖሩን እና የተሳፋሪዎች እንግልት መኖሩን አረጋግጠናል።

በሳምንቱ ከወትሮው በተለየ የታክሲ እጥረትና ረጃጅም ሰልፎች እንደተስተዋሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

ዛሬ ጠዋት ግን በተለይ ከሀያትና ሰሚት ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ እልፍ እልፍ ከሚሉ ታክሲዎች በስተቀር የሚታይ ታክሲ ባለመኖሩ ኮንትራት ታክሲን ጨምሮ ተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው ወደ ስራ ገበታቸው እንደሄዱ ነዋሪዎቹ ነግረውናል፡፡

ምክንየቱ ደግሞ ቀላል የማይባሉ የታክሲ ሾፌሮች አድማ ላይ በመሆናቸው መሆኑን ሰምተናል ብለውናል፡፡

Image result for taxis in addis ababaከሀያት መገናኛ በድጋፍ ሰጪ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ ግለሰብ እንደነገረን ከሆነ እኔ ወጥቼ እየሰራሁ ነው ግን አብዛኞቹ ታክሲዎች ወደ ስራ አልወጡም ብሎናል፡፡ እየደወሉ መኪናህን አቁመህ ወደ ቤትህ ግባ ያሉት ሾፌሮች መኖራቸውንና ሊያስቆሙት የሞከሩ ተራ አስከባሪዎች እንደነበሩ ነግሮናል፡፡

ትናንት የካ ክፍለ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ሰብስቦን ሁሉንም ሮሯችንን ብናሰማም ደስተኞች አልነበርንም ብሏል፡፡

ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ እኔም ወደ ቤት መግባቴ አይቀርም ያለን ይህ ሾፌር 100 ብር የነበረው የመጀመርያው እርከን የትራፊክ ቅጣት ወደ 300 ብር መግባቱ ዋናው የታክሲዎቹ ስራቸውን ባለመስራት ቅሬታቸውን የመግለፃቸው ምክንያት ነው ሲል ነግሮናል፡፡

የቀበቶው መመርያ ተግባራዊ መሆኑም ብዙ ሾፌሮችን ከ ተሳፋሪ እያጋጨ ያለ ጉዳይ ነው ብሎናል፡፡

ብዙ ተሳፋሪዎች ልብሳቸው እንዳይቆሽሽና በሌላም ምክያት ቀበቶ ማሰር አይፈልጉም፣ በርካታ ቀበቶ የሌላቸው ታክሲዎችም አሉ ሲል ነግሮናል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዛሬ ጠዋት በተለየ ሁኔታ ከሀያት ወደ መገናኛ በሚመጣው መስመር ትራንስፖርት አለመኖሩ እውነት ነው ብሎናል፡፡

ሰልፎችም ከወትሮው በተለየ ረዣዥም እንደነበሩ ለኢትዮኤፍኤም የተናገሩት የአ.አ. ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ በድሉ ሌሊሳ ናቸው፡፡
ይሄን ካወቅን በኋላ ግን አውቶብሶችንና ፐብሊክ ባሶችን ወደ ቦታው በመላክ እግሩን አቃለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምን ያህል ታክሲዎች ለስራ ወጥተው ነበር የሚለውን በኋላ አቴንዳንስ ካየን በኋላ ነው ማወቅ የምንችለው ያሉት ምክትል ስራ አስኪያጁ ታክሲዎቹ አድማ ላይ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ያኔ ነው ማወቅ የምንችለው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ መንገድ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂሪኛ ሂርፓ በዋናነት ህግ አክብረው መስራት የማይፈልጉ ሾፌሮች እንጂ ህግ አክብረው የሚሰሩት ወጥተው በህጉ መሰረት እንደሚሰሩ አስተውለናል ብለዋል፡፡

በመስመራቸው መስራት የማይፈልጉት የሚያሰሙት ተቃባይነት የሌለው ቅሬታ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በህጉ መሰረት ቅጣቱም እንዲሁ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ቀበቶ እንዲታሰር ማስገደዳችንም ሆነ ለሁሉም የህግ መጣስ ቅጣት ማስቀመጣችን በአደገኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም