በምዕራብ ኦሮሚያ እየተከናወነ ስላለው ጉዳይ የኦነግ ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) ማብራሪያ ሰጠ

BBC Amharic : በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በአራቱም የወለጋ ዞኖች ማለትም፤ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን፤ የስልክ አገልግሎት የሌለባቸው ደግሞ ምዕራብ ወለጋና የቄለም ወለጋ ዞኖች ናቸው።

የቴሌኮም አገልግሎቶች መቋረጥን አስመልክቶ ከኢትዮ ቴሌኮምም ይሁን ከመንግሥት የተሰጠ በቂ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የቴሌኮም አገልግሎቶቹ እንዲቋረጡ የተደረጉት መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ላይ ኦፕሬሽን እያካሄደ ነው የሚሉ መላ ምቶች በስፋት ሲነገሩ ቆይቷል። ቢቢሲ ይህን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት የቴሌኮም አገልግሎት ባለመኖሩ አልተሳካም።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የቀድሞ የኦነግ ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ በትግል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ጃል መሮ በምዕራብ ኦሮሚያ እየተከናወነ ስላለው ጉዳይ ጠይቀናል።

ጃል መሮ ለጥቂት ደቂቃዎች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።

መሮ የሚገኘው የት ነው?

የጃል መሮ እንቀስቃሴን የሚነቅፉ ፖለቲከኞች በአሁኑ ሰዓት መሮ ከወለጋ ውጪ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ። የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በሌለበት ወለጋ በስልክ አግኝተን ነው ያናገርነው። የት ነው የምትገኘው? ወለጋ ውስጥ ከሆንክስ ስልክ እንዴት ሊሰራ ቻለ? የሚለው የመጀመሪያው ጥያቄ ነበር።

የስልክና የሞባይል ዳታ ግንኙነት መቋረጡን የሚናገረው ጃል መሮ፤ “እንዳሰቡት በኦሮሞ ነጻነት ጦር ሊገኝ የታሰበው የበላይነት መሳካት ስላልቻለ በተለየ መንገድ ሊሄዱበት የወሰኑት ውሳኔ ነው እየተካሄደ ያለው” ይላል።

“መንግሥት ሲፈልግ አግልግሎቱን ለአንድ ዓመት ይዝጋው። ጦራችን በየዕለቱ በተሟላ መልኩ ግንኙነት ማድረጉን እንደቀጠለ ነው። ኪሳራው ለመንግሥት እንጂ በእኛ ግነኙነት ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም” በማለት የተሟላ አገልግሎት እንዳለው ጠቁሟል።

ጃል መሮ ከሌሎች አካላት ጋር አብሮ እየሰራ ነው ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ሲሰጥ፤ “ስትፈልጉ መሮ ሞቷል ስትፈልጉ. . . ስትፈልጉ መሮ መቀሌ ነው ያለው… ከዚህ ቀደም ኮሎኔል ገመቹ አያና እና ዳውድ ኢብሳ ሲናገሩት እንደነበረው፤ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ከሚደግፉ ማናቸውም አካላት ጋር አብረን ልንሰራ እንችላለን። ይህ መብታችን ነው። ለምን ሰይጣን አይሆንም። ኦሮሞን ነጻ የሚያወጣ ከሆነ አብረነው [ሰይጣን] ልንሰራ እንችላለን።

ይሁን እንጂ እንደሚባለው ከህወሃት ጋር አብረን ልንሰራ አንችልም። ብዙ ጠባሳ አለብን ከህወሃት ጋር ፈጽሞ ልንሰራ አንችልም” ብሏል።

“እኔ የምገኘው ኦሮሚያ ጫካ ውስጥ በወለጋ የቡና ዛፍ ሥር ነው” በማለት መሮ ምላሹን ሰጥቷል።

የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ

17 የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት መታገታቸው ይታወሳል። ቢቢሲ ያነጋገራት ከአጋቾቹ ያመለጠች ተማሪ እገታው እንዴት እንደተፈጸም፣ ከአጋቾቹ እንዴት እንዳመለጠች እና የአጋቾቹ ጥያቄ ምን እንደነበረ ተናግራለች።

ምንም እንኳ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው፤ ታግተው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ እንዲለቀቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ኃለፊው ይህን ይበሉ እንጂ፤ የተማሪዎቹ ወላጆች ”ማን ይለቀቅ ፤ ማን አይለቀቅ እስካሁን አላወቅንም” እያሉ ይገኛሉ።

ተማሪዎቹን ያገታቸው የትኛው አካል እንደሆነ በይፋ ባይነገርም፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው እና በድሪባ ኩምሳ የሚመራው ኃይል ስለመሆኑ ብዙዎች ግምታቸው አስቀምጠዋል።

ጃል መሮ ግን “ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ እየሰማሁ ያለሁት ከእናንተ ነው። የትግል ዓላማችን ከተማሪዎች ጋር አይገናኝም። በተማሪዎቹ ላይም ይህን የተባለውን አይነት ተግባር አልፈጸምንም። እንደተለመደው የእኛን ስም ለማጉደፍ የተወራ ነው እንጂ በፍጽም እንዲህ አይነት ተግባር አሁንም ወደፊትም እንፈጽምም።”

መሮ ተማሪዎቹ ታግተውበታል በሚባለው ሥፍራ በኮንትሮባንድ ንግድ ሥራ ላይ ታጥቀው የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን ተናግሮ፤ የእሱ ጦር ግን በአካባቢው እንደሌለ ይናገራል።

በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች ዜናን መስማት የተለመደ ሆኗል። የጥቃት ዒላማዎቹ የሚያነጣጥሩት በአካባቢው ባለሥልጣናት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ለሥራ ወደ ወለጋ ዞኖች የሚንቀሳቀሱ ኃላፊዎችንም ይጨምራል።

ለእነዚህም ባለሥልጣናት ግድያ ተጠያቂ የሚደረገው በጃል መሮ የሚመራው የታጣቂ ቡድን ነው።

ጃል መሮ ግን መንግሥት የእርሱን ጦር ለማዳከም እየተጠቀመበት ያለው ስትራቴጂ መሆኑን እንጂ የእርሱ ጦር ይህን መሰል ተግባር እንደማይፈጽም ይናገራል።

“በምስራቅ በኩል ኦሮሞን እና ሱማሌን እንዳጫረሱት ሁሉ አሁንም በዚህ በኩል የኦሮሞ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለማጋጨት ነው” ይላል።

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዚህ ቀደም ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ጦር እንደሌላቸው መናገራቸው ይታወሳል።