የመዓዛ ትሩፋት – ልጅነትን በስደት

የመዓዛ ትሩፋት
***

መብራቱ በላቸው
***

ልጅነትን በስደት
***

የየካቲት 66 ሕዝባዊ አብዮትና እሱን ተከትሎ የተከሰተው የመንግሥት ለውጥ ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት መመሰቃቀልና ስደት ምክንያት ነበር። የዘመኑ “አብዮተኞች” ትንቅንቅ፣ ደም አፋሳሽ ትግል፣ መቆራቀዝና የእርስ በርስ መናከስ ዜጎችንና አገሪቱን ለከፋ አካላዊና መንፈሳዊ ስቃይ ዳርጓል። የመዓዛ መንግሥቴ ቤተሰቦች የዚህ መከራ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ኢትዮጵያን ውስጥ ነበሩ። በነበረው መከራ ተማረው አገር ጥለው የተሰደዱት የመዓዛ ቤተሰቦች ኬንያና ናይጀሪያን ለጥቂት ጊዚያት መቆያ አድርገው መጨረሻ መዳረሻቸው አሜሪካ ሆኗል።

የልጅነት ጊዜዋን በስደት ለማሳለፍ የተገደደችው መዓዛ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከናወን የነበረውን የዘመኑን የፖለቲካ ትኩሳትና ውጣ ውረድ ስትሰማ ነው ያደገችው። “በልጅነቴ አሜሪካ የመገኘቴ ሚስጥር አቢዮቱ ባመጣው ጣጣ መሆኑን እየተረዳሁ ብመጣም፣ ስለነበረው እንቅስቃሴ ግን ብዙም የማውቀው ነገር አልነበረም” የምትለው መዓዛ “በውስጤ ስለ ምክንያቱ ሥረ መሠረት ለመረዳት ትልቅ ጉጉት ነበረኝ፤” ትላለች። በሌሎች አገሮች ስለተከሰቱ የጦርነት ወሬዎች ስትሰማ ከራሷ ጋር በማዛመድ ስለ አገሯ ፍንጭ ለማግኝትና ለማወቅ የነበራት ጉጉት እየጨመረ እንደመጣ ታስታውሳለች። የጋዳፊን አገዛዝ በመሸሽ ወደ አሜሪካ የመጡ ተማሪዎችን የማግኘት ዕድል ገጥሟት ነበር። የእነሱን የጭቆና፣ የመገፋትና የመገደል ታሪክ ስትሰማ በአገሯም ተመሳሳይ ጭቆናና በደል እየተተከናወነ እንደሆነ ማዛመድ ጀምራ ነበር።

በለጋ ዕድሜዋ ለዓመታት አሜሪካን አገር ያገኘቻቸው የሊቢያ ወጣቶች ታሪክ በአዕምሮዋ ውስጥ ተቀርፆ ትልቅ ታሪካዊ ዳራ እንደሆነላት ትናገራለች። የሚያስገርመው ግን ቤተሰቦቿ ስላለፉበትና ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረው ሁኔታ ከዚያ በፊት አንብባ እንደማታውቅና ማንበብና መመርመር ስትጀምር ግን ችግሩን እየተረዳችው እንደመጣችና ለችግሩም ሌላ መንገድ አለው ብላ ማሰብ እንደጀመረች ታስታውሳለች። በንባብ ፍቅር የወደቀችው ገና በልጅነቷ ነበር። አብዝታ ማንበብ መውደዷን እንጂ ደራሲ እንደምትሆን አታውቅም ነበር።

የሥነ ጽሑፍ ሕይወት
***

የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሚችጋን ዩኒቨርሲቲ አግኝታ እንደወጣች በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ነበር ተቀጥራ የመሥራት ዕድል ያገኝችው። ይህ ዕድል ለብዙዎች ትልቅ የሚባል ቢሆንም መዓዛ ግን ብዙም አልወደደችውም ነበር። በዋናነት የፈጠራ ሥራን የሚያኮስሱ ለገበያ ተብለው የሚገቡ ትዕይንቶች ያበሳጯት ነበር። በዚህም የተነሳ የፈጠራ ታሪክ (Creative writing) መማርና የምታስበውን ሥራ በራሷ መንገድ መጻፍ እንዳለባት ወሰነች።

የፈጠራ ታሪክ አጻጻፍ (Creative writing) በድኅረ ምረቃ መርሐ-ግብር ለመማር ኒውዮርክ የኒቨርሲቲ አመለከተች። ኒውዮርክ የኒቨርሲቲ አሜሪካን አገር ካሉ ቀደምት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱና በፈጠራ ታሪክ አጻጻፍ ትምህርት ዘርፍ አንቱ የተባለ ተቋም ነው። ወደ ተቋሙ መግባት ቀላል ባለመሆኑ መዓዛ ደጋግማ በማመልከት ልትገባ እንደምትችል በማሰብ ነበር ያመለከተችው። እስከዚያው እየጻፍኩ እጠብቃለሁ የሚል ሐሳብ ነበራት። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ሙከራ ተቀባይነት በማግኝቷ በተቋሙ የ‹ማስተር ኦፍ ፋይን አርትስ› (MFA) ተማሪ ለመሆን በቃች።

በተቋሙ ቆይታዋ ከደራሲዎች፣ ከሥነ ጽሑፍ ፌስተቫል፣ ከሒሳዊ ንባብና ታላላቅ ሌክቸሮች ጋር የተዋወቀችበት ጊዜ ነበር። “የክፍል ጓደኞቼን ጽሑፎች በማንበብ ሒሳዊ ንባብን ለማዳበር፣ ሥነ ጽሑፍን ለመረዳት፣ ሒስን ለመቀበልና ለማጥናት በብርቱ እጥር ነበር፤” የምትለው መዓዛ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የፈጠራ ድርሰት ለመሥራት የሚያስችላት ትልቅ ዕውቀት እንዳገኘች ትናገራለች። “አንዳንድ ሰዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማርና ዲግሪ መያዝ የልቦለድ ጸሐፊ አያደርግም በማለት ለመማር ያመነታሉ። እውነት ነው ዲግሪ መያዝ የፈጠራ ደራሲ ለመሆን ዋስትና አይደለም። ነገር ግን የሥነ ጽሑፍን ዓለም ማወቂያና ከጸሐፊያን ዓለም ጋር የመተዋወቂያ መንገድ ነው፤” በማለት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ለድርሰት ሥራዋ ያበረከተውን አስተዋፅዖ ታብራራለች።

በዚህ ሁኔታ ወደ ሙሉ ጊዜ ደራሲነት የገባችው መዓዛ የድርሰት ሥራዋን ስትሠራ ብሪይተን የተባለ ደቡብ አፍሪካዊ ገጣሚ ትልቅ ማበረታታትና ዕርዳታ እንዳደረገላት ታስታውሳለች። “በውስጤ ተቀምጦ የማብሰለስለውን ሐሳብ ለመጻፍ በማመነታበት ወቅት ነበር ብሪይተን “አንዳንድ ጊዜ ‹ታሪክ ሊነግረን ያልቻለውን እውነት የልቦለድ ድርሰት ይነግረናል› በሚል ወርቃማ አባባል ትልቅ ብርታትና የመጻፍ ወኔ ይሰጠኝ ነበር።” በማለት ውለታውን ታስታውሳለች። ይኼም ትልቅ የመጻፍ ወኔና ግፊት እንደሆነላት ታስታውሳለች። በዚህ አጋጣሚም ነበር ጦርነት በግለሰቦች ሕይወት ላይ ስላስከተለው ሰቆቃና መከራ እንጂ ባጠቃላይ ስለ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ለመጻፍ እንደማትፈልግ የወሰነችው። ተወዳጁንና ተደናቂውን ‹ቢኔዝ ዘ ላየንስ ጌዝ› (Beneath the Lion’s Gaze) የተባለውን የልቦለድ ሥራዋን መጻፍ የጀመረችው በዚህ ወቅት ነበር።

መዓዛ ስለ ድርሰቶቿ
***

መዓዛ ስለ ድርሰት ሥራዋ ስትናገር አስቀድሞ የሚመጣባት በልጅነቷ ወደ አሜሪካ ልትመጣ የቻለችበት ምክንያት፣ በዘመኑ የነበረው የጦርነትና የስደት ሕይወት ወሬ፣ የጋዳፊን አገዛዝ በመሸሽ ከሊቢያ የተሰደዱ ወጣቶች ታሪክና እሷም ራሷ ስለ አገሯ የምትሰማቸው ታሪኮች ውስጧን ይከነክኗት እንደነበር ነው። እነዚህንና መሰል የልጅነት ትረካዎች እና ትዝታዎች በአዕምሮዋ ይዛ ያደገችው መዓዛ ወደ ጸሐፊነት ዓለም ስትገባና የልቦለድ ድርሰት መጻፍ እንደምትችል ስትረዳ ይኼን ያገሯን ታሪክ መጻፍ እንዳለባት እንደተረዳች ትናገራለች። “ልቦለድ በዙሪያችን ያለን እውነት ለመረዳት የሚያስችል ዕድል ይሰጣል፤” የምትለው መዓዛ “ልቦለድን የማያምኑና ታሪክና ግለ ታሪክ ብቻ ማንበብ የሚወዱ ሰዎች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የትረካ ድርሰቶችም ቢሆኑ የራሳቸው ፈጠራ እንዳላቸው አይረዱም፤” ትላለች። “እኔም የጻፍኩት በዙሪያዬ የነበረን ታሪክ በልቦለድ መልኩ ለመተረክ ነው” ትላለች።

“ለራሴ የማያነቃቃኝን እና የማልመሰጥበትን ታሪክ ይዤ ለመጻፍ ለብዙ ዓመት አልንገታገትም” የምትለው መዓዛ “በትክክል ከጦርነት ባሻገር መመልከት ስችልና ስለ ሰው ልጆች በጦርነት ውስጥ ያለ መስተጋብር መረዳት ስጀምር ነው ወደ መጻፍ የገባሁት” ትላለች። “የእኔ ድርሰት ስለ አብዮት የሚያወራ ድርሰት ነው። በግርግር ዘመን አተኩሮ የተጻፈ ቢሆንም የፍቅር ታሪክም ነው፤ የአንድ ቤተሰብ የፍቅር ታሪክ” በማለት ስለ መጀመሪያ ድርሰቷ ‹ቢኔዝ ዘ ላንስ ጌዝ› መሠረታዊ ይዘት ትናገራለች። ድርሰቱ ጦርነትና አመፅ ዓላማው እንዳልሆነና ገፀ-ባሕርይዎቿ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሰውን ስለመውደድ የሚተርኩ እንደሆኑ አበክራ ታስረዳለች።

መዓዛ ‹ዘ ሻዶው ኪንግ› (The Shadow King) በሚል ርዕስ ሁለተኛ የልቦለድ ድርሰት ጽፋለች። ይህ መጽሐፍ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ስላደረገው ሙከራና ስለ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን አኩሪ ታሪክ የሚተርክ ነው። መዓዛ ስትናገር “ስለ እነዚህ ጀግኖች ስሰማ ነው ያደኩት። በልጅነት አዕምሮዬ የነዚህ ጀግኖች ታሪክ ተቀርፆብኝ በማደጌ ታሪክ ማገላበጥ ስጀምርና ልቦለድ መጻፍ ስጀምር ጉዳዩ ከጀግንነት የሚልቅ ትልቅ ቁም ነገር እንደሆነ ገባኝ። ብዙ መመርመርና በልቦለድ መልክ መጻፍ እንዳለብኝ ተረዳሁ” ትላለች። ጀግኖች አባቶቻችንን በዱር በገደሉ ሲያግዙ የነበሩ ጀግኖች እናቶቻችን እነማን ነበሩ? ታሪካቸውስ የታል? በሚሉና በሌሎችም ጥያቄዎች ውስጧ ይመሰጥና ይገረም እንደነበር የምትናገረው መዓዛ ከጦርነቱ ታሪክ በላይ በኢትዮጵያዊያን ሴቶችና ወንዶች፣ እንዲሁም በጣሊያንውያን ወንዶችና በኢትዮጵያዊያን ሴቶች መካከል የነበረው መስተጋብር በእጅጉ ይመስጣት ነበር። በመሆኑም ልቦለዱ ‹በጦርነት ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም የጦርነት ታሪክ ግን አይደለም› ትላለች።

የመዓዛ ትሩፋቶች
***

‹ቤኒዝ ዘ ላየንስ ጌዝ› በዘመኑ በአፍሪካ ታትመው ለንባብ ከበቁ ዐሥር ምርጥ መጻሕፍት አንዱ በሚል ‹ዘጋርድያን› የተሰኘው የብሪታኒያ ዕለታዊ ጋዜጣ ሽልማት አበርክቶላታል። ይህ ታሪካዊ ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመና በታላላቅ የዓለማችን የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ብዙ ሒሳዊ ግምገማ የተደረገበት ድርሰት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቿን በአሜሪካ በሚታተመው ‹ዘ ኒውዮርክ ታይምስ› ዕለታዊ ጋዜጣ እንዲሁም የአፍሪካ ዳያስፖራ ሥነ ጽሑፋዊ፣ ጥበባዊና ባህላዊ ወጥ ሥራዎቻቸውን አሳትሞ ለንባብ በሚያበቃው ‹ካላሉ› መጽሔት ለንባብ አቅርባለች።

‹ሌተር ኢንተርናሽናሊ› በተባለ መጽሔት፣ የተመረጡ የሥነ ጽሑፍና የጥበብ ሥራዎችን ለሕትመት በሚያበቃው ‹ግራንታ መጽሔት› ጨምሮ በቢቢሲ ሬዲዮ ቻናል አራት ላይ ሥራዎቿ ቀርበውላታል። እ.አ.አ. በ2011 በዩናይትድ ስቴትስ ‹ዳይቶን ሊትረሪ ፒስ ፕራይዝ› በሚል ሠላምን ለሚሰብኩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው ዓመታዊ የሽልማት ፕሮግራም ላይ ተሳትፋ የኹለተኛ ደረጃን አግኝታለች። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሴቶች ትምህርት ላይ ትኩረት ያደረገና ‹ገርል ራይዚንግ› (Girl Rising) የተሰኘ የዶክመንተሪ ፊልም የሠራች ሲሆን፣ በፊልሙ ላይ እንደ ሜሪል ስትሪፕ፣ አን ሀትዌይ፣ ሴሊና ጎሜዝ፣ አሊሺያ ኪስ እና ኬት ብላንኬትን የመሳሰሉ ታዋቂ የፊልም ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

በጥበብ ሥራዎቿ ስለ ሰብአዊ መብት የማስተዋወቅ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት የሚነገርላት ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ በዓለማችን እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች የሚፈፀሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ለሕዝብ ማድረስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ‹ዋር ስኬፕስ› የተሰኘ የድረ-ገጽ መጽሔት አማካሪ ሆና አገልግላለች። በአሜሪካ በስደተኛ መጠለያ በሚገኙ ሕፃናት መብት ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ ለሚሠራ አንድ ማዕከል በተለያዩ ፕሮግራሞች እና በሚሰጡ አገልግሎቶች የማማከር አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች።

የባለሙያ ዕይታ
***

ደረጀ ሙሉጌታ “A Thematic Analysis of Beneath the Lion’s Gaze and Held at a Distance: My Rediscovery of Ethiopia” በሚል ርዕስ በመዓዛና ርብቃ ሥራዎች ላይ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ዲፓርትመንት ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱን አድርጓል። ደረጀ በጥናቱ ለመጠቆም እንደሞከረው የመዓዛ ሥራ የሚያጠነጥነው የዐፄ ኀይለ ሥላሴን የሥልጣን ዘመን ማብቃት ተከትሎ በተከሰተው ደም አፋሳሽ ለውጥ ምክንያት በተፈጠረው አስፈሪ ሥርዓት ውስጥ አንድ ቤተሰብን ማዕከል በማድረግ ድንቅ በሆነ የትረካ ክሕሎት የቀረበ የፈጠራ ሥራ ነው። ድርሰቱ የርኀብን አስከፊነትና መዘዙን፣ የሰውን ልጅ ጭካኔ፣ ክህደትን፣ ፀፀትን፣ ዘር ማጥፋትን፣ ጭቆናንና መከራን የመሸከምና የዓላማ ፅናትን ከፍቅር ጋር አስተሳስሮ የያዘ ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አተራረክ የቀረበ ልቦለድ ነው ይለዋል።

በደረጀ ጥናት መሠረት የመዓዛ ድርሰት አራት ዐበይት ጉዳዮችን ይዳስሳል። ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን፣ ፅናትና ፅንፈኝነትን፣ ደም አፋሳሽ አብዮትና ብሔራዊ ጀግንነትን የሚዳስስ ነው። እነዚህ ሁነቶች ጉዱ በተባለ ሥርዓቱን በሚወክል ገፀ-ባሕርይና በዶ/ር ኀይሉና (በተለምዶ አጠራር ጋሽ ኀይሉ) በቤተሰባቸው ዙሪያ በማጠንጠን ይተርካል። ዶ/ር ኃይሉና ቤተሰባቸው የሚወክሉት በፅናትና ቆራጥነት የቆመ፣ ነጻ ኢትዮጵያን የሚናፍቅ ቤተሰብን ነው። የሚደርስባቸውን በደልና ሰቆቃ፣ ፅናታቸውን፣ ቆራጥነታቸውንና የሚከፍሉትን መስዋዕትነት በተባ ብዕሯ በድንቅ ቋንቋ ለዓለም አስነብባለች።

በ‹Wright state university› የተዘጋጀው “Reader’s Guide for Maaza Mengiste’s Beneath the Lion’s Gaze” መጣጥፍ የመዓዛን ድርሰት በሦስት ዐበይት ጉዳዮች ዙሪያ ያስቀምጠዋል። ቤተሰብን ባማከለ መልኩ የማኅበረሰብን ግጭት መግለጽ፣ የአመፅን አስደማሚና አስቀያሚ ገጽታ እንዲሁም በትውልዱ ለማኅበራዊ ጭቆና የተሰጠ ተመጣጣኝ ምላሽን የዳሰሰ ሥራ በማለት ያስቀምጣል። መዓዛ የኢትዮጵያን አብዮትና መዘዙን ሆን ብላ በአንድ ቤተሰብ መነፅር ልታሳየን ተግታለች። ይህ ቤተሰብ የብዙ ድምፆችና አመለካከቶች መገኛ ተደርጎም ተቀርጿል። በዚህም አንባቢ የአብዮቱን ገጽታ በአንድ ቤተሰብ መነፅር እንዲረዳውና እንዲያየው ከማድረግ ባሻገር የወቅቱ ምስቅልቅል ምን ያህል የቤተሰብን ግንኙነትና መስተጋብር እንዳናጋ ያሳያል።

ማሳረጊያ
***

መዓዛ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የዳያስፖራ ሥነ ጽሑፍ (Diasporic Literature) ተብለው ከሚመደቡት ጸሐፍት አንዷ ናት። ዶ/ር ታዬ አሰፋ “የስደት ጭብጦች በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ልቦለዶች” በሚል ርዕስ ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ኹለተኛው አገር ዐቀፍ የባህል ዐውደ ጥናት ላይ ባቀረቡት ጥናት “የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ሐሳባቸውንና ተሞክሯቸውን በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ላለው ወገናቸውና ለሌላው አንባቢ በተለያየ የጽሑፍ ዓይነት በስፋት ማቅረብ የጀመሩት በተለይ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ነው” ይሉና ስለ ምክንያቱ ሲያስረዱ “…የኢትዮጵያውያን ስደት በጣም እየተደጋገመና በስፋት እየተከሰተ በመሄዱ ቀደም ሲል ከአገር የተሰደዱትን ኢትዮጵያዊያን ተመክሮ ለማወቅ የሚፈልግ አንባቢ በስፋት በመኖሩና ደራሲዎቹም ሌሎች ከነሱ ልምድ ትምህርት እንዲቀስሙ ስለሚፈልጉ ወይም አገር ቤት ባለውም ሆነ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ መፍጠር ስለሚሹ ነው። የተወሰኑ ደራሲያን ደግሞ ያለፉበትን ሕይወትና ገጠመኝ ትርጉም ለመረዳት የሚያደርጉት ጥረት አካል ስለሆነም ነው” ይላሉ።

መዓዛ ስለድርሰት ሥራዋ ስትናገር በውስጧ ሲብላላ ስለነበረውና በዘመኑ በአገሯ ስለተከናወነው ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተት መጻፍ ትፈልግ እንደነበር ትናገራለች። በሕይወቷ ያለፈችበትንና የገጠማትን ለመረዳት ያደረገችው ጥረት ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በድንቅ የሥነ ጽሑፍ ችሎታዋ በኹለቱ ድረሰቶቿ ታሪክን፣ ቤተሰብን፣ ፍቅርን፣ ፖለቲካን፣ ጦርነትን፣ ርኀብንና ስለማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍትሕ የተደረገ ተጋድሎን ለዓለም አሳይታለች። ይኼን ችሎታዋን የዓለማችን ታላላቅ መገናኝ ብዙኃንና ባለሙያዎች አድናቆትን ችረውታል።

ታሪክ በበቂ ሊነግረን የማይችለውን ክስተት ልቦለድ መንገር እንደሚችል መዓዛ በድርሰቷ አስመስክራለች። መዓዛ መንግሥቴ ለታዋቂነት የበቃችበትን ድርሰት ከማቅረቧ በፊት በደርግ አነሳስና ያንንም ተከትሎ በመጣው አስከፊ ትዕይንት ዙሪያ ዲናው መንግሥቱ “The Beautiful things That Heaven Bears” እና ነጋ መዝለቂያ “Notes from the Hyena’s Belly” የሚለውን ድርሰታቸውን አበርክተዋል። እንደ ብዙዎቹ የሥነ ጽሑፍ ሐያስያን እምነት የመዓዛ ሥራ ከቀድሞዎቹ የአገሯ ልጆች ሥራዎች ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ቋንቋ ከተጻፉት የአሜሪካዊያኑም ድርሰቶች የላቀ ሥፍራ የሚሰጠው ነው ይላሉ።