የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ተዘጋ

(ሙሉቀን ተስፋው)

አዲስ በተቋቋመው የሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከእምነት ጋር በተያያዘ በተነሣ ጠብ ከትናንት ጀምሮ መዘጋቱንና የፓርኩ ኃላፊዎች አቶ ማሩ ቢያድግልኝና አቶ አበባው አዛናው በዞኑ አስተዳዳሪ መታሠራቸውንና የፓርኩ ኅልውናም አደጋ ላይ መውደቁን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል፡፡

የፓርኩ ሠራተኞች ነን በማለት የነገሩን የተፈጠረውን ችግር እንዲህ አብራርተዋል፡፡ በድብ ባሕር ቀበሌ ሊማሊሞ ጎጥ አንድ የሃይማኖት አባት ከወራት በፊት ማጥመቅ ይጀምራል፡፡ በዚህም ጸበሉን ተከትሎ በፓርኩ ውስጥ በርካታ ቤቶች በወራት ውስጥ ይገነባሉ፡፡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመነጋገር ቤቶቹ እንዲፈርሱ ከተደረገ በኋላ ከጸበሉ አካባቢ በዞኑ አስተዳዳሪ አቀናባሪነት የእሳት ቃጠሎ ተነሳ፡፡ በቃጠሎው የሕብረተሰቡን ሃማኖተኛነት ስሜት በመጠቀም ጽላትና ሥእል ተቃጥሏል የሚል ወሬ ይሰራጫል፡፡ በዚህም ሕብረተሰቡ የፓርኩን ኅልውና በሚጎዳ መልኩ እንደተንቀሳቀሱና በጠለምት፣ ደባርቅና ጃናሞራ ወረዳዎች ከብቶችን ወደ ፓርኩ በማስገባት የእንስሳቱ ኅልውና አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡ በዚህም ጋር ተያይዞ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አምሳሉ ደረጀ የነበረውን ፖለቲካዊ ኢቅቡልነት ለማስተካከል ይህን እኩይ ሥራ ፈጽሟል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ ለምን ይህን ሊያደርግ ይችላል ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ አምሳሉ አሁን ባለው የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ተቀባይነት ባለመኖሩ የሕዝብ ወገን ለመምሰል የተጠቀመበት እንደሆነና የፓርኩን መኪኖችም በግዴታ ለመጠቀም በመፈለጉ ከፓርኩ ኃላፊዎች ጋር እስጥ አገባ ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከ70 በላይ የሚሆኑ የፓርኩ ቋሚ ሠራተኞች ሥራ ማቆማቸውንና የፓርኩም ኅልውና አደጋ ላይ መውደቁን ሕብረተሰቡም ያለውን ችግር እንዲገነዘብ ሠራተኞቹ አሳስበዋል፡፡ ለፌደራልና ክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ አመልክተው መልስ ማግኘት አለመቻላቸውን ጭምር አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ፓርክ በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መስህቦች አንዱ ነው፡፡