( ኢፕድ) “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው የአቋም መግለጫ ከድሮ የባለይነቴ ለምን ለቀቅኩ የሚል እንድምታ ያለው፤ የመገለልና ባዕድ ስሜት እንደተሰማው የሚያሳይና ለጦርነት እንደተዘጋጀ የሚያመለክት ነው” ሲሉ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደውን አስቸኳይ ጉባኤ ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ ውህደቱን አልቀበልም፣ ከኢህአዴግ የጋራ ሀብት እካፈላለሁ ማለቱንና በውስጥ እንቅስቃሴዎች እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን እንደሰሙ ጠቁመው፤ ሁኔታው ወደግጭት የሚያስገባ ይመስላል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የህወሓት መሪዎች ኢህአዴግ በመፍረሱ ከፍተኛ ቁጭት እንደተሰማቸው ያሳያል፡፡ ያስተላለፉት መልዕክትም የመገለል እና ባዕድ ስሜት እንደተሰማቸው የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ወደ ግጭት ሊያድግ እንደሚችልና እነርሱም ለጦርነት እንደተዘጋጁ የሚያመለክት አንድምታ አዝሏል ብለዋል አቶ አምዶም፡፡
እንደሃላፊው ማብራሪያ፤ መልእክቱ ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ዜና አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ ከችግሩ መውጣት አለበት፣ ካለበት ችግርም የሚያወጣው ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ የጦርነት ፕሮፖጋንዳ መንዛቱም ለህብረተሰቡ ጥሩ ነገር እንደሌለው ያመለክታል ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹ሁልጊዜም ምክንያትና ሰበብ የሚያደርጉት እኛን ነው፡፡ ዛቻ ይደርስብናል፣ ጉዳትም እያደረሱብን ይገኛሉ ሰላማዊ ታጋዮች በመሆናችንም ይጎዱናል ይህ ግን ጥሩ አይደለም›› ያሉት አቶ አምዶም፤ ህግም ህገ መንግስቱም መከበር አለበት ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው አረና ዘንድሮ ለሚደረገው ምርጫ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ የህወሓት አቋምም መስተካከል እንዳለበት መክረዋል፡፡
የህወሓትን መግለጫ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን የሰጡት የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ ህወሓት ከብልጽግና ተነጥሎ ራሱን የቻለ ፓርቲ ሆኖ መንቀሳቀስ መብቱ ቢሆንም ድርጅቱ ከዚህ በላይ አስተሳሰብ መያዙን ይጠቅሳሉ፡፡
ድርጅቱ የብልጽግና ፓርቲን እየወነጀለና እየከሰሰ መሆኑን በመጠቆም ውንጀላው የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ድርጅት አድርጎ እስከመክሰስ የደረሰ ነው ባይ ናቸው፡፡
ሂደቱ ግጭትን የሚፈልግ አይነት ነው፡፡ መግለጫውን ህወሓት የትግራይ ህዝብ ተከብበሃል፣ ጠላት አለህ፣ ታጠቅና ክተት በማለት ከሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ጋር አይይዘን ብናየው ከድሮ የበላይነቴ ለምን ለቀቅኩ፣ የሚያስለቅቀኝም ብልጽግና ነው የሚል እንድምታ አለው፡፡ ከዚህም ባለፈ የጸብ አጫሪነት፣ ወደ ግጭት የመግባትና ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት ያለው ድርጅት መሆኑንም ያመለክታል፡፡
ህወሓት ትግራይ ውስጥ የበላይ ሆኖ ያንሰራራ፣ ባለፉት 27 ዓመታትም የኢህአዴግ መሪ ሆኖ ኢትዮጵያን በግጭት፣ በድህነትና በኋላቀርነት ጠፍንጎ የያዘ መሆኑ ይታወቃል የሚሉት ዶክተር አረጋዊ፤ አሁን ያንን የበላይነቱን ሲያጣ ነው ትግራይ ውስጥ ነው የመሸገው ብለዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ ከለላ እንዲሆንለት በማሰብም ተከብበሃል ስለዚህም ለጦርነት ክተት በማለት ሌት ተቀን እየጮኸ ነው። ሌሎች ድርጅቶች ሁኔታው ትክክል እንዳልሆነ ለህዝቡ ለማስረዳት ሲሞክሩ ባንዳ፣ ከሃዲ በማለት እያሰረና እየደበደበ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ህወሓት ያወጣው መግለጫ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለሚያደርጉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትልቅ ጫና ይፈጥራል የሚሉት ዶክተር አረጋዊ፤ የለውጥ አየር እንዳናስተጋባ፣ ህዝቡ በሚፈልገው ድርጅት ተሰባስቦና ተደራጅቶ የሚፈልገውን እንዲደግፍ፤ የማይፈልገውን እንዲተው የሚችልበትን ሁኔታ እንዳያገኝ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በእኛ በተፎካካሪዎች ላይ ትልቅ ችግርና ጫና እያሳደረብን ነው፡፡ ተጽእኖው ከእኛ አልፎ በህዝብ ላይ ነው፡፡ በሚቃወሙት ላይ የሚሰነዝራቸው ስሞች አሳፋሪና ዘግናኝ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተጽዕኖው ቀላል አይደለም፡፡
ምንም ቢሆን የጀመርነውን እንቅስቃሴ አናቆምም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪመሰረት፣ የኢትዮጵያም ሆነ የትግራይም ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ ወሳኝ እንዲሆን፣ ድምጹን በነጻነት በካርድ እንዲወስን ያለው ያለመገሰስ መብቱ ተግባራዊ እንዲሆን ትግላችን ይቀጥላል፡፡
ለተነሳንለት የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት አላማ ወደ ኃላ አንልም፡፡ ህወሓት ኢህአዴግ ሆኖ ሲያካሂደው እንደነበረው አይነት ምርጫ ተብዬ እንዲደረግ አንፈቅድም፡፡ ሁኔታው መለወጥ አለበት፡፡
በመላው ኢትዮጵያ የለውጥ አየር ሊተነፍስ የቻለው ህዝቡ ጠንክሮ ስለታገለ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን መታገል ይኖርበታል፡፡
ትግራይ ሁለት አይነት ተፎካካሪ ድርጅቶች አሉ፡፡ ግማሾቹ የህወሓት ተቀጽላዎች ናቸው፡፡ በህወሓት ላይ የሚሰነዝሩት ስሞታ የለም። ይህንን የትግራይ ህዝብ ለይቶ ሊያውቅና ድጋፍና ዕድልም ሊነሳቸው ይገባል ሲሉም ዶክተር አረጋዊ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን