የ“አድገናል አላደግንም፤ ለምተናል አለማን፤” ስሜታዊ ትርጉም (ጌታቸው አስፋው)

[addtoany]

የ“አድገናል አላደግንም፤ ለምተናል አለማን፤” ስሜታዊ ትርጉም

ጌታቸው አስፋው
(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)
ስለ አብዛኛው ሰው የኑሮ ዓይነትና ደረጃ አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ ኑሮ ተሻሽሏል ብለው ይናገራሉ፤ ይጽፋሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ይሰማሉ፤ አይናገሩም፡፡ ያነባሉ፤ አይጽፉም፡፡ የማይናገሩ የማይሰሙ፤ የማይጽፉና የማያነቡም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ቁጥራቸውም ቀላል አይደለም፡፡ ከሚናገሩት ከሚሰሙት፤ ከሚጽፉትና ከሚያነቡትም በእጅጉ ይበልጣል፡፡ ሐሳብ ለሐሳብ ከሚለዋወጡት ውስጥ የተማሩት ከልተማሩት፤ ያልተማሩት ካልተማሩት፤ የተማሩት ከተማሩት ይጨቃጨቃሉ፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል አላደገም፤ ለምቷል አለማም፤ አድጓል ግን አለማም፤ ለምቷል ግን አላደገም፤ የንትርኩ ጭብጦች ሆነዋል፡፡ ሁሉም የራሱን ሐሳብ እንጂ የሌላውን ሊቀበል አይፈልግም፡፡ የማንኛቸውም ማስረጃ ውኃ አይቋጥርም፤ ለሌላውም አይዋጥም፡፡ ውይይቱና ክርክሩ በእውነት ስለ እውነት ሳይሆን ኢሕአዴግንና ኢሕአዴግ መራሹን መንግሥት ከመውደድና ከመጥላት የተነሳ ነው፡፡

በጽንሰ-ሐሳብ ላይ ያልተመሠረተ አመለካከት የግል ወይም የቡድን ብቻ ነው፡፡ ሙግቱም በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ፍሬ ከርሲኪ ሊሆን ስለሚችል፣ ስህተትን ለማስረዳት የሚችል ብቃት አይኖረውም፡፡ ለዚህም ነው፣ ኢኮኖሚው አድጓል የሚሉም፣ አላደገም የሚሉም፣ ለማደጉም ላለማደጉም፣ ለመልማቱም፣ ላለመልማቱም፣ ለመሻሉም፣ ላለመሻሉም ማረጋገጫ የሌላቸው፡፡ ሙግታቸውም ከመውደድና ከጥላቻ፣ ከማመንና ከመጠራጠር የመነጨ ብቻ የሚመስለው፡፡ ለማደጉም ላለማደጉም፣ ለመልማቱም ላለመልማቱም፣ አድጎ ላለመልማቱም፣ ለምቶ ላለማደጉም የሚቀርቡት ማስረጃዎች ምንጫቸው ሁለት ነው፡፡ አንዱ ለመንግሥት የኢኮኖሚ ባለሟሎች በቀር ለሌሎች ሰዎች የማይታይ ቢታይም የማይቀበሉት በባለሟሎቹ የሚዘጋጅ ስታቲስቲካዊ መረጃ ሲሆን፣ ሌላው ለመንግሥት ባለሟሎችና ባለሥልጣናት የማይታይ ቢታይም የማይቀበሉት ለአብዛኛው ሕዝብ በገበያ ውስጥ የሚታይ የኑሮ ሁኔታ ነው፡፡

በፖለቲካ እምነት ልዩነት ላይ ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ተደርቦ መጠላላቱና መናናቁ ስለ ኢኮኖሚው ጉዳይ አንዱ ሌላውን እንዳያሳምን ከልክሏቸዋል፡፡ ለባለሙያው ሙያውን የማያውቀው ሊነግረው ይፈልጋል ጋዜጠኛው ለኢኮኖሚስቱ ላስረዳህ ይላል፡፡ አርቲስቱ ለኢኮኖሚስቱ ልንገርህ ይላል፡፡ የቱ በኢኮኖሚ ሙያ ተምሮ እንደሰለጠነና የቱ የሌላ ሙያ ባለቤት እንደሆነ መለየት አቅቷል፡፡ የፖለቲካ እምነት ልዩነቱ መጠላላቱንና መናናቁን ፖለቲካው ራሱ ይፍታው፤ የጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ልዩነቱን የኢኮኖሚው ጥበብ እንዲፈታው ዕውቀቱ ለብዙዎች እንዲዳረስ ጥበቡን የሚያውቀው ለማያውቀው ማጋራት የሙያም የዜግነትም ግዴታ አለበት፡፡

ዜጎች ሙያውን የሚያካፍላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ አጥተው በሆነ ባልሆነው ይጨቃጨቃሉ፡፡ ባለመግባባቱ ምክንያት አንደኛው የሌላውን መረጃ ከመቀበልና ከመተማመን ይልቅ፣ በግትርነት የራስን ሐሳብ አንዱ በሌላው ላይ ለመጫን ምስክር ይፈልጋሉ፡፡ የማይግባቡ ሰዎች አይመካከሩም፤ ካልተመካከሩም፤ አይማማሩም፡፡ ካልተማማሩም አያውቁም፡፡ ጉዳቱ በተናጠል ለግለሰብም በጋራም ለሕዝብና ለአገር ነው፡፡ በስሜታዊነት በሙያ ጉዳይ የሚጻፉ ነገሮች ሁሉ ግማሽ ሕዝብ ሲቀበላቸው ግማሽ ሕዝብ አይቀበላቸውም፡፡ በፖለቲካ ኩርፍያ ምክንያት ዕውቀታቸው ጣሪያ የነካ ብዙ የኢኮኖሚ ምሁራንም ሳይጽፉ ሳያስነብቡ ሳይናገሩ ሳያሰሙ አገራቸውን ሳያገለግሉ ከሙያቸው ጋር ተቀበሩ፣ ለአዲሱ ትውልድ የምርምር መነሻ የሚሆን ተጨባጭ መረጃ ሳይተው አለፉ፡፡

በተከላለሰና በተበራረዘ መረጃ የሚለካ ኢኮኖሚ እና በዓይን ምስክርነት የሚረጋገጥ ኢኮኖሚ እኩል አይሆኑም፡፡ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ዓለም ዐቀፍ ንጽጽር ለማድረግ ለዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተብሎ ከእነርሱ በወረደ የመረጃ አሰባሰብ ማዕቀፍና ዘዴ ለእነርሱ በሚያመቻቸው መንገድ በግምት ስለሚዘጋጅ ለአዘጋጁ ባለሙያ እንከን የማይወጣለት ሐቅ ነው፡፡ ገበያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በዓይኑ አይቶ፣ እውነቱን ለሚያውቀው ሕዝብ ግን አይዋጥለትም፡፡ ሁለቱን ሊያስታርቃቸው የሚችለው ስታቲስቲክሱንም ገበያውንም በአንክሮ ተመልክቶ የልዩነታቸውን ምክንያት መረዳትና ማብራራት የሚችል ሰው ብቻ ነው፡፡

ኢኮኖሚክስ በዩኒቨርሲቲዎቻችን መሰጠት ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ውጭ አገር ሄደው ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የያዙ በርካታ አንቱ የተባሉ ምሁራን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም አሉ፡፡ ስለ ሰው አገር ኢኮኖሚ ለመናገርና ለመመስከር ቢያቅታቸው ስለ እኛው ኢኮኖሚ መናገርና መመስከር አያቅታቸውም፡፡ ሆኖም ለማይሰማና ለማይስማማ መንግሥት በባዶ ሜዳ ላይ ሐሳባቸውን ማፍሰስ ጥቅም እንደሌለው ስለሚያስቡ ዝምታን መርጠዋል፡፡ መንግሥትም በዐሥር ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያሉ የውጭ ሰዎችና ድርጅቶች ስለ እኛ ሳያውቁ ራሱ በሚሰጣቸው መረጃ ምስክርነታቸውን ሰጥተው ሕዝብን እንዲያሳምኑለት ይሻል፡፡

መንግሥት በሰበካና በባዕዳን ምስክርነት ለማሳመን ቢሞክርም፣ ሕዝቡ የሙያ ዕውቀት ባይኖረውም በዐይኑ ከሚያየው በላይ በጆሮው የሚሰማውንና በጽሑፍ የሚያነበውን ሊያምን አልቻለም፡፡ ከምስክሩ ይልቅ ተጨባጭ እውነቱን የሚያውቀው ኑሮውን የሚኖረውና የራሱንም የጎረቤቱንም የሸቀጥ ፍላጎት መርካት ሥነ-ልቦና የሚያውቅ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ ዛሬና ከዛሬ ዐሥር ሃያ ሠላሳ አርባ ሐምሳ ዓመታት በፊት አንድ ኩንታል ጤፍ በስንት ብር ይገዛ እንደነበር፣ የኩንታል ጤፍ መግዣ ዋጋ ሌሎች ምን ዓይነት ሸቀጦችን ይገዛ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በተከላለሰ የአከላክ ዘዴ በተከላለሰ የመሸጫ ዋጋ ለክተው በወረቀት ላይ የሰፈረውን አርተፊሻል የቁጥር ኢኮኖሚ ከሚያውቁት ባለሙያዎች እና ስታቲስቲክሱ ከቀረበላቸው የውጭ አገር ሰዎችና ድርጅቶች በላይ የድሮው ምን ያህል እንደነበር የዛሬው ምን ያህል እንደሆነ የድሮውንም የዛሬውንም በገሃዱ ዓለም አይቶ እርግጠኛውን ሕዝብ ያውቃል፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በሁለት ብር ዋጋ ታናሽ ታላቅ ሽንጥ ስጋ ሙሉውን ይገዛ እንደነበርና ዛሬ የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ ሁለት መቶ ብር እንደሆነ የውጭ ምስክሮች ሊያውቁም ሊነግሩትም አይችሉም፡፡ ስታቲስቲክሱም የድሮውንና የዛሬውን አነጻጽሮ የሚያቀርበው ለመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ይጠቅማል ያለውን ብቻ ነው፡፡ ከሕይወት ተሞክሮው የቀድሞውንም የዛሬውንም የሚያውቀው ሕዝብ ግን ዛሬም በሕይወት አለ፡፡ ዛሬ በየመንገዱ አምስትና ዐሥር ብር ተከፍሎ የሚጠጣው ቡና ድሮ ጎረቤት ለጎረቤት ተጠራርቶ በነጻ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የሚጠጣው ቡና እንደሆነ የሚያውቀው ሕዝብ ዛሬም በሕይወት አለ፡፡ ድሮ ስለማይሸጥ በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ውስጥ ተካቶ አይደመርም፤ ዛሬ ግን ስለሚሸጥ በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ቆጠራ ውስጥ ይካተታል፤ ኢኮኖሚው ያደገ ያስመስላል፡፡ ጎረቤት ለጎረቤት ተጠራርቶ ደጋግሞ ይጠጣ የነበረ የጀበና ቡና በገንዘብ በመሸጡ ተጠቃሚው ተጎዳ እንጂ አልተጠቀመም፤ በባለሙያ አለካክ ግን የአገር ውስጥ ምርት መጠን አድጎ የኑሮ ደረጃም ተሻሽሏል፡፡ የቤት ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ወደ ገበያ መውጣት ሥልጣኔ ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ምርትና የኑሮ ደረጃ አደገ ለሚሉ በቁጥር የሚያምኑ ባለሙያዎች እና በዓይን ገበያውን አይተው ለሚመዝኑ ሰዎች ያለመተማመን ምክንያት ሆኗል፡፡

ባለሙያዎች የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ዋጋን በመከለስ ብቻ መሽቶ እስከሚነጋ በሚኖሩት ሰዓታት ውስጥ ቁጥሩ ተለውጦ ኢትዮጵያ ከኬንያ በለጠች ወይም ኬንያ ከኢትዮጵያ በለጠች ይላሉ፡፡ ለሕዝብ ግን በአንድ ቀን አዳር የሚለወጥ የኑሮ ሁኔታ የለም ትናንትም ዛሬም ያው ነው፡፡ የዛሬ መቶ ዓመትም ዛሬም ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ የኩርማን መሬት አራሽ ገበሬ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ምርት መጠን ግን ከሚልዮኖች ተነስቶ ቢልዮኖችን ዘሎ ትሪልዮኖች ውስጥ ገብቷል፡፡ ኢኮኖሚስት ሆኜ በስታቲስቲካዊ መረጃ አላምንም አልልም፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ ስታቲስቲካዊ መረጃዎቹን ያዘጋጁት እነማን ናቸው? ያዘጋጁት በምን ቀመር ነው? ምንን ታሳቢ አድርገው ነው? ከፖለቲካው ትዕዛዝ ነጻ ናቸውን? እና መረጃዎቹ ከእውነቱ ምን ያህል የራቁ ናቸው? ለምንድነው የራቁት? የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ካሳተሙት “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” ከተሰኘው መጽሐፍ አንድ ስንኝ ወስዶ በባለሟሎች የሚቀርቡ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ምን ያህል ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል፡- “አገሮች በራሳቸው መለኪያ በአገራቸው ያለውን የድሆች መጠን የሚያስታውቁበትን አሃዝ በመውሰድ በተቀመጠ የደረጃ ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ ከህዝቧ 29.2 በመቶ ብቻ ድሃ በመሆን ከ157 አገሮች ውስጥ 73ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ በዚህም በአውሮፓ እንደነ መሴዶንያ፣ ኮሶቮ፣ ዩክሬን፣ አርሜንያ፣ ከላቲን አሜሪካ እነ አርጀንቲና፣ ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ፔሩ፣ ጓተማላ፣ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን፣ ቦትስዋናን፣ ቶጎን፣ ናይጄሪያን፣ ኮት ዲቯርን ሁሉ አልፈን በልጠን እንገኛለን፡፡ ይህንን በመንግሥት የሚቀርብ አሃዝ በመጠቀም ነው እንግዲህ ኢትዮጵያ ድህነትን በመቀነስ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቷን የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ለጋሽ አገሮች የሚመሰክሩት”፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ የተናገሩት ትክክል መሆኑን አንድ ማስረጃ ወስደን እናረጋግጥ፡፡ “የዓለም ‹ኢኮኖሚክ ፎረም› ኢትዮጵያ የተከተለችውን የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜና የገቢ ስሌት ውድቅ አደረገ፤” በሚል የሪፖርተር ጋዜጣ (ጥር 24 2010) እንደዘገበው፤ በ2010 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ መንግሥት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ1.8 ቢልዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ይህን መረጃ ተቀብለው የዓለም ባንክና የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅትም አስተጋብተው ይሆናል፡፡ ይሁንና የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ትንታኔ ይህ ገቢ የተሰላበትን መንገድ ውድቅ አድርጎ ገቢውን ወደ 444 ሚልዮን ዶላር ዝቅ የሚያደርግ ትንታኔ አቅርቧል፡፡ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸው በአማካይ አንድ ሳምንት ወይም ሰባት ቀናት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በአንጻሩ ኢኮኖሚክ ፎረሙ ኢትዮጵያን ከሚጎበኘው ቱሪስት ውስጥ 87 በመቶው የቢዝነስ ወይም ኮንፈረንስ ቱሪስት በመሆኑ አማካይ የቆይታ ጊዜ ከሁለትቀን እንደማይዘል አስቀምጧል፡፡ በዚህ የቆይታ ጊዜያቸው ቱሪስቶች ለሚያስፈልጋቸው አገልግሎት በቀን በአማካይ ያወጣሉ ተብሎ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች የሚታሰበው 250 ዶላር ነው፡፡ በ2010 መጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ኢትዮጵን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር 465 ሺሕ ሲሆን በሚኒስቴሩ ግምት በቀን 250 ዶላር ወጪ የሚያደርጉና ሰባት ቀናት የሚቆዩ ከሆነ የእነዚህ አኃዞች ብዜት የሚያስገኘው 814 ሚልዮን ዶላር ነው፡፡ 1.86 ቢልዮን ዶላር ገቢ የሚገኘው በ16 ቀናት ቆይታ ነው፡፡

የዓለም ‹ኢኮኖሚክ ፎረም› ባስቀመጠው ስሌት መሠረት፣ ከ465 ሺሕ ቱሪስቶች ውስጥ 87 በመቶው ወይም 404 ሺሕ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ጎብኚዎች በመሆናቸው የቆይታ ጊዜያቸው በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት እንደሚገመት አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት የዓለም ‹ኢኮኖሚክ ፎረም› አንድ ቱሪስት በአንድ ቀን የኢትዮጵያ ቆይታው 450 ዶላር ወጪ ያደርጋል የሚል ስሌት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም በሁለት ቀናት አማካይ ቆይታ ከተሰላ 465 ሺሕ ቱሪስት ታሳቢ ተደርጎ ከ420 እስከ 440 ሚልዮን ዶላር ገቢ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ መገኘቱን ይጠቅሳል፡፡ በሦስት ቀናት ቆይታ ከታየም 628 ሚልዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ አስቀምጧል፡፡ የዚህ ዓይነት የመረጃዎች ስህተት ከእያንዳንዱ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሚደርሱት በተለምዶ ‹ጂዲፒ› ተብሎ የሚታወቀውን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ወይም የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ አጠናቃሪ በድምር ውጤት ምን ያህል ስህተት እንደሚሠራ መገመት ይቻላል፡፡ የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችም ስህተቱን በማስተጋባት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት አሳብጠው ያቀርባሉ፡፡