የነ ዶ/ር አብይ የለውጥ ጎዳናና የትኛውን አቅጣጫ ሊከተል ይገባዋል? (በይታገሱ ዘውዱ )

  1. በለውጥ ዋዜማ

ዛሬ ካለንበት ድንግዝግዝ ሁኔታ አንፃር የመዘነው እንደሆነ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ መጥቷል ወይስ በለውጥ ሂደት ውስጥ ነን?” ለሚለው ጥያቄ ጥርት ያለ መልስ ያለን አይመስለኝም ።  ባለፉት አራት አስርት አመታት በተለይም ደግሞ ለ27 ዓመታት የተዘረጋው ረዥሙ የፖለቲካ ክረምት ቆፈን ለቆ ተስፋ ሰጭ የፀደይ ጊዜ እየመጣ እንደሆነ የሚጠቁሙ ክስተቶች ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት አስተውለናል። ተደጋግሞ  እንደተነገረው እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ የመጣው በማያባራ የህዝብ አመፅና ቁጣ አስገዳጅነት እንጂ በገዢዎቻችን መልካም ይሁንታ እንዳልሆነ ለአፍታ እንኳን የማይጠረጠር እውነታ ነው። ለዚህም ይመስላል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው የህብረተሰብ አባል የሚፈልገውን የለውጥ አይነት፣ ጥልቀት፣ ጥራትና ብዛት እንደ አመለካከቱ እየዘረዘረ ለውጡ ይፋጠን በሚል ውትወታውን የቀጠለው።

እንደምሰማውና እንደምንታዘበው ለውጡን እውን ያደርጋሉ የተባሉ ጥያቄዎች ከተለያየ አቅጣጫ በተለያየ መጠን እየቀረቡ ይገኛል። የሽግግር መንግስት ይቋቋም ከሚሉ ወገኖች አንስቶ፣ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ  እውን እንዲሆን የሚያስችሉ የህግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ይደረጉ የሚሉ ሞጋቾች በርክተዋል። እንዲሰረዙ የተጠየቁ አዋጆች፣ እንዲሻሻሉ የሚፈለጉ የህግ ድንጋጌዎች ዝርዝራቸው ጥቂት የሚባል አይደለም። ከፖለቲካው ተሻግሮ የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያዎች እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይደረግ የሚለው ጥያቄም በተመሳሳይ አቅጣጫ ወደ ፊት እየተገፋ ይገኛል። ጥያቄው ማቆሚያ አይኖረውም። ቁምነገሩ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በምን ያህል ፍጥነት ተራምዶ የት ያደርሰናል የሚለው ጉዳይ ነው።

ከየአቅጣጫው ከሚነሱ ውትወታዎች ረገድ የምንገነዘበው የለውጡ ጥያቄዎች የጋራ ባህርያት እንዳሉት ሁሉ የሚጋጩ ፍላጎቶችንም አዝሏል። ለማስታረቅ የሚከብድ ዋልተኝነት በለውጡ ሂደት ላይ ጥላ አጥልቶበታል። አንዱ ወገን ሃገራዊ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠንከር አለበት ሲል፣ ሊላኛው በዘውግ ማንነቴ ጥቃት እየደረሰብኝ ሀገር ብሎ ነገር የለምና በመጣንበት መንገድ መጓዝ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስላደላ ከኢትይጵያ በፊት የዘውግ ማንነቴ የሚል ፅንፍ የወጣ አቋም ያቀነቅናል።

የሆነው ሆኖ የመካከለኛውን መስመር አስበን ለውጡ ወደ ፊት እንዲራመድ በመፍቀድ እንነሳ። የሀገራችን ፖለቲካዊ ሽግግር ይህን መምሰል አለበት፣ በዚህ አቅጣጫ ይጓዝ፣ ይሄኛው ይጣል፣ ያኛው ይተከል የሚለው ጥልቅ የለውጥ ሂደት ሃሳብ ውስጥ ከመስመጣችን አስቀድመን ልናጤናቸው የሚገቡ በርካታ ነባራዊ ሁነቶች እንዳሉን ልብ ሊባል ይገባል። አስቀድመን ልናስበው የሚገባን የለውጡ ጥያቄ  ከየት መጣ የሚለውን ነው። በመቀጠል ዛሬ ላይ ሀገራችን የደረሰችበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ የእድገት ደረጃ ምንድን ነው የሚለው ጉዳይም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። መሬት ላይ ያሉት ሃገራዊ፣ አከባቢያዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ምንምን ይፈቅዳሉ፣ ምንምን አይፈቅዱም ከሚለው ጥያቄ ጋር ተሰናስነው በተገቢው መንገድ መጠናት እና መተንተን አለባቸው። ከስሜታዊ እና ከተምኔታዊ ንድፈ ሃሳብ ግንዛቤ ተላቀን ከእውነታዎች ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ አለብን። የሁኔታ ግምገማው ከታሪካዊ ልምዳችን ጋር ተዛምዶ፣ የከፈትነው የለውጥ ምዕራፍ ያለበት ጥንካሬና ድክመት፣ የሚፈጥረው እድልና ስጋት ሚዛን ላይ ተቀምጦ ሊናፀርና ሊተነተን ይገባዋል።

ስለሀገራችን የለውጥ ጉዞ ስናስብ ወንዝ ተሻግረን ባህር አቋርጠን የትኞቹ ሃገራት ምን አይነት ለውጥ በምን አይነት መንገድ አካሄደው ምን አተረፉ፣ ምንስ ደግሞ አጡ የሚሉ ንፅፅራዊ ትንተና (comparative analysis) መደረግ ይኖርበታል። ከአንባገነነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር እኛ የመጀመሪያዎቹና የመጫረሻዎቹ እንዳልሆንን ግልፅ ነው።  ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ፣ ስኬትና ውድቀት ተገቢውን ትምህርት ወስደን በራሳችን አውድ በስራ ልንተረጉመው የሚገባ አስተምሮትን በአለም ታሪክ ላይ በነጭና ጥቁር ቀለም ተፅህፎ እናገኘዋለን።

ሌላኛውና ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ የለውጡ ባለ ድርሻ አካላት ጉዳይ ነው። እነኚህ አካላት የየድርሻቸውን ሃላፊነት ከመውሰድ አልፈው የተገኘውን እድል ላለማባከን ሊወስዱት የሚገባን ጥንቃቄ ታሳቢ ማድረጉ ተበቢ ይሆናል። እነኚህ የለውጥ ሃይሎች በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የመብት ተሟጋቾች እና ሌሎችም ልዩ ልዩ  አደረጃጀቶች የለውጥ ሂደቱ ደጋፊ እንጂ አደናቃፊ ላለመሆን፣ በህዝበኝነት መንፈስ ለሃገራቸውና ለወገናቸው ቅድሚያ ሰጥተው፣ ከግልና ከቡድን ጥቅም ወይም ክብር ተሻግረው ሊመለከቱት የሚችሉት ትልቅ ስዕል ሊኖራቸው ይገባል። እሱም ኢትዮጵያና ህዝቦቻ ናቸው።

ለውጥን መፈለግ ብቻ ለውጥ ሊሆን አይችልም። የምንፈልገውን ለውጥ የምንታገለው መንግስት ይሰጠናል ብሎም ማሰብ የዋህነት ይሆናል። እንደ አንድ የፖለቲካ ሃይል መንግስትን የሚመራው የፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ግንባር ( ኢህአዴግ ) ያለውን ሁኔታ አስጠባቂ እንደመሆኑ መጠን የያዘውን አቋምና ስፍራ ለመልቀቅ አይፈቅድም። ዋና ዋና የህዝብ ጥያቄ ለሆኑ ጉዳዮች መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥቃቅን ምልክቶችን በማከም የመጣበትን  መንገድ ለማስቀጠል አጥሩን መከላከሉ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። አልያም እንደ “ጡት አባቱ” የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ፖለቲካውን “ሊብራላይዝ” አድርጎ ዴሞክራሲን ሊያፍን፣ “political liberalization without democratization” የሚሉትን የተሃድሶ ሞዴል ሊከተል ይችል ይሆናል። በመሆኑም ኤህዴግ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ ይሰጠናል ብለን ልንጠብቅ አይገባም። ይልቁንስ ኢህአዴግ ውስጥ ከበቀሉ የለውጥ ፋና ወጊዎች ጋር በምን መልኩ ተጋግዘን የህዝባችንን ጥያቄ እውን እናደርጋለን የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ ለመመለስ የፖለቲካ ሃይሎች በፅኑ ሊያስቡበት ይገባል።  በዚህ ሂደት ምን አይነት ለውጥ ነው የምንፈልገው ለሚለው ቀላል መሰል ነገር ግን ተግባራዊነቱ እጅግ ከባድና ውስብስብ ለሆነ ጥያቄ መልስ ልንሰጠው የሚገባው።

የምንፈልገውን ለውጥ ስናስብ ለውጡ የመጣበትን መንገድ ማጤን ተገቢ ነው። ለውጡ የመጣበትን መንገድ በቅጡ ካልተረዳን የምንሄድበትን አቅጣጫ ማገናዘብ ሊከብደን ይችላል። አንድ አንድ ወገኖች ዛሬ ላይ ገርበብ ያለውን የለውጥ ደጃፍ ያንኳኩት ቄሮ፣ ፋኖና የመሳሰሉት ዘውግ ተኮር የወጣቶች ንቅናቄዎች ናቸው ብለው ስለሚያምኑ አኮቴቱን ሁሉ ለእነሱ ብቻ ሲሰጡ ይስተዋላል። በእርግጥ እነኚህ ንቅናቄዎች ጉልበታቸው ብርቱ በመሆኑ የማይናድ የሚመስለውን የትዕቢትን እና የፅንፈኝነት ተራራን ንደውታል። የማይበገር ይመስል የነበረውን አንባገነናዊ አገዛዝንም ለጊዜውም ቢሆን እጅ አሰጥተውታል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ትውልድና ታሪክ የማይዘነጉትን መስዋእትነት በህይወትና በአካል ከፍለዋል። ይሁን እና ኢትዮጵያ ላይ የተጫነውን አገዛዝ የሦስት አመት ተጋድሎ  ብቻ አወላልቆታል ብሎ መደምደም ከባድ ብያኔ ይሆናል። ጉዳዩን በሦስት አመታት ትግል ብቻ የምንሸብበው ከሆነ የለውጡን ጥያቄ ጥልቀትና ስፋት አሳንሰን እንዲሁ በአከባቢያዊ ጥያቄዎች ለጉመን ሃገራዊ ትርጉሙን እንዲያጣ እናስገድደዋለን የሚል ስጋት አለኝ። የኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የብልጽግና፣ የመሳሰሉ የመሰረታዊ መብት ጥያቄዎች ትላንት የተጀመረ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ ነው።

የራቀውን ትተን፣ የቅርብ ዘመኑን በተለይም ዛሬም ድረስ የዚያ ትውልድ የመብት ታጋዮች ከፖለቲካው መድረክ ያራቁበትን እና የዚህን ዘመን ትውልድ ጥያቄ ብቻ አቀራርበን ስንመረምር ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ሲደመር አመታት በልተቋረጠ የለውጥ ጥያቄ ንቅናቄች ውስጥ አልፋለች። ለዚህ መሰሉ ትግል ምዕራፍ ከፋች የሆነው የዝመና ነቢብ (ትወራ) ካነቃው የ1953ቱ “የንዋይ ቤተሰቦች” መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተነስተን ወደ እዚህ ዘመን ብንቆጥር በአመዛኙ የተነሱት የለውጥ ጥያቄዎች፣  ሃገሪቱን ከነበረችበት ጨለማ በማውጣት፣ በኢኮኖሚ የበለፀገች፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፣ በዴሞክራሲ የዳበረ ፖለቲካ ሥርዓት እውን እንዲገነባባት ትውልድ እየተቀባበለ የለውጥ አላማን አራምዷል። በሁሉም ባይባል እንኳን በአመዛኙ የተከፈለውን መስዋእትነት የሚመጥን ስኬት ተገኝቷል ለማለት ፍፁም አያስደፍርም። ተከብሯል የተባለው የዘውግ መብት እንኳን አንዱን ጌታ ሌላውን ሰለባ የሚያደርግ ሆኖ ነው የቀጠለው ተብሎ በፅኑ ይተቻል።

በሀገራችን ተደጋጋሚ የለውጥ መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረው የባከኑ እድሎች ሆነው አልፈዋል። ለዚህ መሰሉ ከባድ ኪሳራ የተዳረግነው የለውጥ ሃይሎቹ የተሳፈሩበት ባቡር የተሳሳተና መስመሩን እየሳተ በየጥሻው የሚወተፍ በመሆኑ፣ አልያም “የኔ” ያለውን አሳፍሮ  “ሌሎች” ያላቸውን ከኋላ ጥሎ በጓዙ ነው። ጨለማ ያሉትን ዘመን የተሻገሩት አንባ ገነኖች ሃገሩን በደም አበላ ሲያጥቡት፣ ፋሽስት ያሉትን አገዛዝ ጣልን ያሉቱ በዘረኝነት ታውረው ሀገር ምድሩን በአጥንትና በጉልጥምት ከፋፍለው ሃገራችንን ገፍተው ገደል አፋፍ ላይ አደረሷት።  የኢትዮጵያ ህዝብ የመለወጥ እድሎች አልፈውኛል ብሎ ተስፋ አልቆረጠም። ትግሉን አላቆመም። ሌላውን ትተን ከ1983 ወዲህ ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንኳን የነበሩትን ትግሎች ስናጤን እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን ለሃገራዊ አንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ለነፃነት እና ለመሳሰሉት መብቶች ያልተቋረጠ ተጋድሎ  አድርገዋል። ሺዎች ሞተዋል፣ ሚሊዮኖች ከቀዬቸው ተፈናቅለዋል፣ ሚሊዮኖች ሃገራቸውን ትተው ተሰደዋል። ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበቁ በደንብ እየጠበቁ መተው መተንፈሻ ሲታጣ ዳግም አዲስ ዙር ነውጥ እና እንቢኝ ባይነት የተወለደው።

ለበርካታ አመታት የተደረገው ትግል የፈጠረው ንቃተ ኅሊና ዳግም ዛሬ ትውልዱ ለመብቶቹ ቀናይ፣ ለነፃነቱ ተጋዳይ መሆን በመጀመሩ እንደገና የለውጡ ባቡር ሞተሩን ማሞቅ ጀምሯል። የባቡሩ በር ተከፍቷል ማለት  እነማንን አሳፍሮ በየት አቅጣጫ እንደሚጓዝና የመጨረሻው ግቡ ታውቋል ማለት ግን አይደለም። ከዚህ ቀደም እንዳመለጡን እድሎች ሁሉ ይሄኛውም ከእጃችን ወጥቶ ባልተፈለገ መስመር እንዳይጓዝ ነቅተን ልንከታተለው ይገባል።

የዛሬ ስድስት አመት ግድም የቀደሙት የኢህዴጉ ቁንጮ የበሩት ሰው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ  ያን ያህል መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ባይታሰብም መለስተኛ ማሻሻያዎች ይኖራሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሥርአቱ የቆመበትን መሰረት ሊያናጋ የሚችል አደጋ ጋር ቢጋፈጥም ተቋማዊ ቁመናውን ጠብቆ እያነከሰም ቢሆን ለመቀጠል ቢያንስ የሦስት ዓመታት እድል አግኝቷል። የሰውየው ከዙፋኑ ገለል ማለት በተለየ መንገድ የጠቀመው ለጥቂት ጉልበተኛዎች ብቻ ነው። ለውጥን የሚያቀነቅን ሳይሆን ነባሩን ሥርዓት በምልሰት እየተወነ የሚመራ ጠቅላይ ሚንስቴር አስቀምጠው ከላይ እስከ ታች በተዘረጉት መንግስታዊና ፓርታዊ መዋቅሮች ተጠቅመው የሀገርና የህዝብን ሃብት የሚበዘብዙ፣ የዜጎችን መብት እንደአሻቸው የሚረግጡ ሲቪልና ወታደራዊ “ኦሊጋርኪስ” ሃገሪቱን ፈነጩባት። ለውጥን ትላንትም ዛሬም አጥብቀው ይቃወሙታል። ለዚህም ነው ለተነሳው የመብት ጥያቄ ሁሉ መልሳቸው ጥይት፣ እስራት እና ማሳደድ ሆኖ የዘለቀው።

የህዝቡ እንቢተኝነትና አልገዛም ባይነት ወደ ፊት በገፋ መጠን የለውጡ ደጋፊ ሃይሎች ከስርአቱ ውስጥ በቅለውና ጉልበት አግኝተው የለውጥ ሃዋርያ ሆነው ለመውጣት ችለዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ካለ ለውጡ እየተመራ ያለው ከስርአቱ ውስጥ ባጎነቀሉና ሰብረው በወጡ የለውጥ አራማጅ ቡድኖችና ግለሰቦች ነው። በነዚህ የለውጥ አራማጆች እየተገፋ ያለው ሽግግር ለሀገራችን በአይነቱ የተለየ ነው። ለውጡ የሚመራው የስርዓቱ ፈጥሮ ባሳደጋቸው ግለሰቦች በመሆኑ፣ እነኚህ ሃይሎች የነበረውን ሁሉ አፈራርሰው አዲስ ህግና ሥርዓት ተክለው ሳይሆን፣ በነባሩ ህግና መስመር ተጠቅመው ደረጃ በደረጃ የህግና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረጉ ወደ ተፈለገው የሥርዓት ሽግግር ግብ ማዳረስን ተልኳቸው ያደረጉ ይመስላል። በነ አቶ ለማ መገርሳና በነ አቶ  ደጉ አንድ አርጋቸው የሚመራው የለውጥ መስመር ዶ/ር አብይን ከፊት አስቀድሞ ለውጡን መምራት ቢጀምርም ከፊቱ ሁለት ብርቱ አደጋዎች ተጋርጠውበታል።

እነ ጠቅላይ ሜኒስቴር ዶ/ር አብይ የጀመሩት የለውጥ ጉዞ ከፍተኛ ተቃውሞና ተግዳሮት የሚገጥመው የሚደረገው ለውጥ ጥቅማችንን ያሳጣናል ከሚሉ የስርዓቱ ጋሻ ጃግሬ ከሆኑት ወታደራዊና ሲቪል ባለስልጣናት ነው። እነኚህ ሃይሎች የህልውና ስጋት ካሸተቱ የመንግስትን ስልጣን መልሰው ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን መፈንቅለ  መንግስት ከማድረግ ጀምሮ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ሴራዎችን እና አሻጥሮችን በመጠቀም ለውጡን እየመሩ ያሉ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከማጥፋት አይመለሱም። የነ ዶ/ር አብይ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚሊተሪውና የደህንነቱ ጥላ እንዳጠላበት መሆኑን በፅኑ ማመን የተገባ ይሆናል። በሌላ አባባል የለውጡ አራማጅ የሆኑት ቡድኖች የሃገሬቱን የስልጣን ዋንኛ መሳርያ “Deep State” የሚባለውን ወታደራዊና ፀጥታ ክንፉን ሙሉ በሙሉ ባልተቆጣጠሩበት ሁኔታ፣ ዛሬም ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የፀጥታ ሃይሉ እውነተኛውን ስልጣን በያዘበት አጋጣሚ፣ ለውጥ አራማጆቹ ካደጋ የራቁ አይደለም።

በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችን እና ተቃውሞዎችን እንቆጣጠራለን፣ ህግና ሥርዓትን መልሰን እናሰፍናለን (to restor order)  በሚል ሰበብ ነባሩ አመራር በወታደሩ እየታገዘ ስልጣን ለመቀማት አይሞክርም ማለት ዋጋ የሚያስከፍል የዋህነት ይሆናል። ለዚህም ሲባል ወታደሩን እና ጥቅም አስጠባቂውን ነባር ሃይል እየአባበሉ በዘዴ  መያዝ፣ ዋስትና መስጠት፣ ከተቻለም የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል። ለውጥን በሚያራምደው እና የለም ጥቅሜን አላስነካም በሚለው ሃይል መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ እና የጠላትነት መንፈስ እስኪረግብ ጊዜ ይወስዳል። ግብተኛ  እና ችኩል እርምጃ መውሰድ ለውጡን ከማደናቀፍ አልፎ ሀገርን ውድ ዋጋ ያስከፍላል።

ህዝቡ እጅግ መራር በሆነ የጭቆና ቀንበር ተቀይዶ እንደመቆየቱ፣ ብሎም ለውጡ እንዲመጣ ከባድ ትግል እንደማድረጉ መጠን፣ ፈጣን እና አስተማማኝ ለውጥ መጥቶ ከመከራው ለመገላገል መቋመጡ የሚጠበቅ ነው። ከመሰንበቻው የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የመጣው ህዝቡም ሆነ ሌሎች የለውጥ ጠያቂ ቡድኖች በከፊልም ቢሆን እነ ዶ/ር አብይ የምንፈልገውን ለውጥና የምንሻውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ያደርጉልናል የሚል መተማመን መፍጠር በመቻሉ ነው። የህዝቡ ጥያቄ፣ የወጣቱ ፍላጎት፣ የፖለቲካ ሀይሎቹ ምኞት፣ የመብት ተሟጋቾቹ ፍላጎት እጅግ ውስብስብና መጠነ ሰፊ ነው።  እነኚህ ወገኖች የጠየቁት ሁሉ ቢቻል በአንድ ጀንበር ተሳክቶ ቢመለከቱ ደስታቸው ነው። በሌላ አነጋገር ሃገሪቱ ላይ ያለው ኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት እና ሌሎችም ዕልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሃገራዊ ችግሮች በፍጥነት መፈታት ሲችሉ ነውና ለውጥ መጣ ለማለት የሚቻለው፣ ህዝብ ለጥያቄዎቹ አፋጣኝ መልስ ካላገኘ ፊቱን ማዞሩን ብሎም ወደ ተቃዋሞች ተመልሶ መግባቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ለውጡን እየመሩ ያሉት አካላት በተቻለ ፍጥነት ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ሊኖርባቸው ነው። ከህዝቡና ከፖለቲካ ሃይሎቹ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የነ ዶ/ር አብይ ቡድን የቱንም ያህል ቀናይ ቢሆን የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ሊዘነጋ አይገባውም።

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ወሳኝ ሁነቶች በመነሳት የተጀመረው የለውጥ መስመር ከስጋት የራቀ አይደለም። ስጋቱ ውስጣዊና ውጫዊ ነው ብለን ብናስቀምጠው፣ ከውስጥ አሮጌውን መስመር

አስጠባቂ የሆኑት ቡድኖች ያሰመሩትን ቀይ መስመር ላለማስደፈር ወደ ኋላ ባገኙት ሃይል ተጠቅመው ሲስቡ፣ ለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ደግሞ በተቻለ መጠን ገዢው ሃይል ተገርስሶ በምትኩ አዲስ ሥርዓት እንዲተከል  ወደ ፊት ይጎትታል። እነ ዶ/ር አብይ የሚመሩት የለውጥ ቡድን በነዚህ ሁለት ሃይሎች በሚጎትቱት ገመድ ላይ በጥንቃቄ ለመጓዝ ይገደዳሉ። የተፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዳይደናቀፍ፣ በሌላ በኩል የስልጣን ክፍተት ተፈጥሮ  ዳግም ሃገሪቱ ከነበረችበት ትርምስ የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የማድረግ፣ ሀገርን ከውድቀት፣ ህዝብን ከእልቂት የማዳን ከባድ ሃላፊነት ታሪክና አጋጣሚ ጫንቃቸው ላይ ጭኖባቸዋል። የለውጡ መሪ ሃይሎች ሚዛናቸውን ጠበቀው በዚህ ገመድ ላይ በጥበብ ወደ ፊት የመጓዝ፣ በትግስት የሁሉንም ፍላጎት የማስተናገድ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ይህ ፈተና ማለፍ ከሚታሰበው በላይ ከባድ ይሆንባቸዋል።

ፈተናውን የበለጠ የሚያከብደው የለውጥ ሃይል ሆነው የወጡት ሰዎች ያለመታመን እዳ ስላለባቸውም ጭምር ነው። የአሮጌው ቡድን ክብር አስጠባቂዎች “ከእጃችን በልተው፣ በኛ ጀርባ ታዘለው ወደ ላይ ከመጡ በኋላ ከዱን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ንቀው ሊብራሊስት ሆኑ” በማለት ከመንጫጫት አልፈው ክፉኛ መርዘዋቸዋል። በሌላኛው ወገን ያለው ጎትጓች በተለይም “አክቲቪስቶች” እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድኖች፣ ዛሬ ለውጡን እየመሩት ባሉት ሰዎች ላይ ከባድ የሚባል ጥርጣሬ  አላቸው። ሰዎቹ ከአሮጌው ሥርዓት ብብት ውስጥ የወጡ በመሆናቸው፣ የጨቋኙ አገዛዝ ፍድፋጅ ናቸው በማለት፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ገዢው ግንባር በ27 ዓመታት ጉዞው ለሚጠየቅበት ጥፋትም ሆነ ውድቀት እኩል ሃላፊነት መውሰድ ያለባቸው እንጂ የምንፈልገውን ለውጥ አያመጡልንም ብለው ያምናሉ። በመሆኑም እነ ዶ/ር አብይ ይህንን ሁሉ ፈተና በትጋት ማለፍ ከቻሉ ብቻ ነው ሀገራችን ከገጠማት ከባድ አደጋ ተሻግራ የምንመኘው ዴሞክራሲ በሀገራችን እውን ሆኖ የምናየው።

የለውጡ መሪዎች የክልል ስልጣን በተቆጣጠሩ ማግስት የጀመሩት “የሊብራላዜሽን” ስራዎች የሃገሪቱን የፖለቲካ አየር መቀየር ብቻ ሳይሆን የኖረውን የቸከና የመነቸከ የጥላቻ ፖለቲካ በመጠኑም ቢሆን ቀይረውታል። ከሁሉም በላይ ሃገራዊ ትስስርና አንድነት ዳግም እንዲያንሰራራ ስሜት የሚሰጥ ስራዎች በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙሃን አማካይነት ሰርተዋል። በተደጋጋሚ ያቀረቧቸው ዘገባዎች የለውጡን ግለት እንዲጨምረው ብቻ ሳይሆን በህዝቡ መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲፈጠር አስችለዋል። ከሁሉም በላይ በህዝብ መካከል በሃሳዊ ንቃት ተፈጥሮ  የኖረውን የፀብ ግርግዳ ንደው፣ ህዝብ ከህዝብ ዳግም እንዲዋሃድ በሰሩት ስራ ታላቅ ከበሬታን ቸሯቸዋል። ወደ ፌደራል ስልጣን ሲመጡ፣ የለውጡን ሂደት ያስቀጠሉት በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት ለፍትህ ያላቸውን አክብሮት በመጠኑም ቢሆን በማሳየት ነው። ይህ እርምጃቸው ከተጠበቀው በላይ ሀገር ቤት ካለው ህዝብ አልፎ የአለም አቀፍዊ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። ይህ መሰሉ አውንታዊ ግብረ-መልስ የተሟላ እንዲሆን ተጨማሪ የሌሎች የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፈታት ይኖርባቸዋል። ከላይ የተጠቀሱትን ፈተናዎች በብቃት ለመሻገር ያስችላቸው ዘንድ ግን ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስት የለውጥ መተግበሪያ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ-መንግስቱን ጨምሮ ብዙ የማያግባቡ ህግጋቶች በስራ ላይ ውለዋል። ሲጀምር ህገ-መንግስቱ በርካቶች ቅብልነትን ያጣበት ዋንኛው ምክንያት የአንድን የፖለቲካ ድርጅት  አመለካከት የሚንፀባርቅና የጠባብ ቡድኖችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ በመሆኑ ነው። ህገ-መንግስቱ የግለሰብ መብቶችን በቁንፅልነት የሚያይ ከመሆን አልፎ ሃገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አንቀፅ የተካተቱበት ነው። ከሁሉም በላይ ህገ-መንግስቱ የፀደቀበት መንገድ ብዙዎችን አያስማም። ያልተወከለ የህብረተሰብ አካል እንዳለ በስፋት ሲገር የኖረ ጉዳይ ነው። ይሁንና አንዳንድ ህገ-መንግስቱን እንደሚቃወሙ ወገኖች  እንደሚሉት ተቀዶ ይጣል ለማለት የሚከብድ ቢሆንም እንኳን መሰረታዊ የሚባሉ ማሻሻያዎች ሊደረግበት ይገባል። የማሻሻያ ሂደቱ ግልፅና አሳታፊ መሆን ይኖርበታል። ከፌዴራሉ ህገ-መንግስት ባልተናነሰ የክልል ህገ-መንግስቶችም አንዱን የክልል ባለቤት፣ ሌላኛውን መጤ የሚሉበት፣ ጠባብነትን እና አግላይነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያራምዱ በመሆናቸው ማሻሻያው ሊጎበኛቸው ይገባል። ለሚደረገው ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ሽግግር ደጋፊ የሆኑ፣ ፖለቲካዊ ታህድሶን የሚያበረታቱ  ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል። በተለይ ከ1997 ወዲህ የወጡ አፋኝ የተባሉ ህግጋት ሊሰረዙ አልያም ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገባ ነው።

ሀገራችን በተለየ መልኩ ወደ ኋላ ከቀረችባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ የተቋማት አደረጃጀቶች ጉዳይ ነው። ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መንግስታዊ ተቋማት ከገዢው ፓርቲ ጠለል ያራቁ ብቻ ሳይሆን ብርቱ ጫና  ያረፈባቸው ናቸው። ወታደራዊና ሲቪል የሚባሉት የተቋማት አደረጃጀቶች የሚመሩበት መርህና የሚመሯቸው ግለሰቦች የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ርዮት አራማጆች ከመሆን አልፈው፣ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ግብ ማስፈፀሚያ ሁነኛ ግዞቶች ሆነው ቆይተዋል። ለዚህም ነው በመንግስትና በተቋማት መካከል ያለው መስመር ነጭና ጥቁር መሆን ያልቻለው። ይሄ አይነት አደረጃጀት ለገዢዎች አመቺ ቢሆንም ዴሞክራሲን ከማኰስመን አልፎ  ለሀገር ህልውና ከፍተኛ ስጋት ሆኗል። ከእንግዲህ ወዲያ ሊኖሩን የሚገቡ ሃገራዊ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ ሆነው በራሳቸው ለሚቆሙ የሚያስችል ብቃትና አቅም ሊፈጠርላቸው የተገባ ነው። የዚህ አይነት አደረጃጀትን የሚፈቅዱ ፖሊሲዎችና ደንቦች በተገቢው ተቀርጸው ስራ ላይ መዋል ሲጀምሩ ተቋማቱ እራሳቸውን ከፓርቲ ሞግዚታዊ አገዛዝ ዐርነት እያወጡ ነፃና ገለልተኛ መሆን ይጀምራሉ። ያኔ የትኛውም ፓርቲ ወደ ስልጣን መጣ ሄደ እነኝህ ተቋማት ሃገራዊ ሆነው ይቀጥላሉ። ከዚያም አልፎ  መንግስት በማይኖርበት አጋጣሚ ቢፈጠር እንኳን፣ ተቋማቱ ስራቸውን ከማከናወን የሚያግዳቸው ስለማይኖር የሀገርን ህልውና ጠብቀው ያቆያሉ። ከሁሉ በላይ ሚሊተሪውን፣ ደህንነትን ፣ ምርጫ ቦርዱን፣ የሰባዊ መብቶች ኮሚሽንን የመሳሰሉት ወሳኝ ተቋማትን በተቻለ ፍጥነት አደረጃጀቶቻቸውን በማስተካከል ከፖለቲካ ውክልና ጸድተው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቋም እንዲሆኑ በስፋት ሊሰራበት ይገባል።

ከላይ የተዘረዘሩትን ህጋዊና ተቋምዊ  ማሻሻያዎችን ማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሞከር አይደለም። ጊዜ፣ትግስት፣ መግባባት፣ ማመቻመችና ተባባሪ መሆንን ይጠይቃል። እነኚህን ስራዎች ለመከወን በትንሹ ከአንድ እስከ ሁለት አመት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። አፍርሶ መስራት አዲስ እንደመገንባት ቀላል እንደማይሆን መቼም ከማንም የተሰወረ አይደለም። ከባድ ነው። ቀላል ያማይባል ተከላካይ ሃይል መነሳቱ አልቀርም። ሆኖም በመስጠትና በመቀበል መርህ ሁሉንም ማግባባት ባይቻል እንኳን ቅሬታን በተቻለ መጠን በመቀነስ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። ዛሬ ላይ ከለውጡ መሪዎች የሚጠበቀው ፍኖተ-ካርታቸውን ማሳወቅና አስፈፃሚ አካላትን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ ሂደቱ እንዲቀላጠፍ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቀና ተሳትፎ  ማስተባበር ነው።

የሀገራችን ፖለቲካ አግላይ ነው። አንዱን የበህር ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ የሚያደርግ። የፖለቲካ አደረጃጀቱ አንዱን አዳጅ ለኤላውን ተሳዳጅ ያደረገ፣ በጠላትነት፣ በመጠፋፋትና በአውጋዥነት የተቃኘ የግራ ዘመሞች የኖረ የፖለቲካ ባህል ነው ሃገሪቱን የተጫናት። በተለይ ዘውግ ተኮር አደረጃጀት የትኛውም አይነት መስመራዊ ቅራኔ  በማንነት መገለጫዎች ላይ እንዲመረኮዝ ስለሚጋብዝ እኛ እና እነሱ የሚል ክፍፍል ላይ ተንጠላጥሎ ልዩነት እንዲሰፋ ይጋብዛል። ህብረ ቤሄራዊ ወይም የዜግነት ፓለቲካን የሚራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፖለቲካው መድረክ ተግፍረዋል። ከሁሉም በላይ የአሸባሪነት ሰሌዳ ተለጥፎባቸው ከህጋዊዉ የፖለቲካ መድረክ የተገለሉ ሃይሎች እንዳሉም የሚታወቅ ነው። እነኚህን ሃይሎች ወደ መድረኩ ለማቅረብ የሚስችል የህግ ማሻሻያ በማድረግና በመጋበዝ የለውጥ ሂደቱ አካል እንዲሁኑ ማድረግ  ሽግግሩን የሚያግዙ ለማድረግ ይቻላል። የሀገራችን ፖለቲካ ካግላይነት ወደ አካታችነት ማሸጋገር የሚኖረው ፋይዳ ያኮረፉ ሃይሎችን ከማሰባሰብ አልፎ የፖለቲካ በሃላችንን በተገቢ መልኩ የሚለውጥ በመሆኑ የጠላትነት ስሜትን በተፎካካሪነት በመለወጥ የተሻለ ነገን ለማለም ያስችላል። ለዚህ ስከት የለውጥ አራማጆቹ ከአፋዊ ጥሪ ባለፈ አስተማማኝ እርምጃዎችን ባፋጣኝ መውሰድ ሲኖርባቸው፣ እስካዛሬ ሲንገዋለሉና ሲገፉ የኖሩት የፖለቲካ ቡድኖች ቁሮሻቸውን ወደጎን በመተው በቶሎ ለውጡን መቀላቀል ይኖርባቸዋል።

እነ ዶ/ር አብይ የጀመሩት የለውጥ ጎዳና የሰመረ እንዲሆን፣ ከአንባ ገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚደረገው ሽግግር በስኬት እንዲጠናቀቅ በተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎችና በስልጣን ላይ ባለው ፓርቲ መካከል እውነተኛ ድርድር ሊደረግ ይገባዋል። ድርድሩ በህግ ማሻሻያዎች፣ በፖሊሲ ጉዳዮች፣ በተቋማት አደረጃጀትና አመራር ላይ አተኩሮ  ለመጪው ዘመን ምቹ መደላደልን በመፍጠር ላይ ማድላት ይኖርበታል። ድርድር መደረግ ያለበት የትላንት ሂሳብን ለማወራረድ ሳይሆን ለነገ ምን የተሻለ እንስራ በሚለው ጉዳይ ላይ እንዲሆን በጽኑ ይመከራል። ድርድሮች በቅድመ ሁኔታ ሳይታጠሩ በጋራ መግባባት (concession) ላይ አተኩረው፣ ለዩነቶችን በማመቻመች (compromising) የለውጥ ሃይሉ ጠንክሮ  የተጀመረውን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል አቅም በመፍጠር ግብ ላይ ማተኮር አለበት። ተደራዳሪዎቹ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት አሻግረው የህዝብን ደህንነት እና ሃገራዊ ህልውና ታሳቢ እንዲያደርጉ ግድ ይላቸዋል። ለዚህም ሲባል ድርድሮቹ በመርህ መገዛትና መመራት ይኖርባቸዋል።

በድርድር ሂደቱ መግባባት የሚፈጠረው በተቃዋሚዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል ብቻ  ሳይሆን በተቀዋሚ ጎራ ተሰልፈው ላይተያዩ በተማማሉት መካከልም ጭምር ይሆናል። በድርድር ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው መቀራረብ የበለጠ እርስበርስ ለመናበብ እድል ስለሚፈጥር በድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት ከጠላትነት ይልቅ የሃሳብና የርዕዮት አለም ልዩነት ብቻ እንዲሆን እድል ይፈጥራል።  ሂደቱ አታካች፣ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን የሚችልበት ምዕራፍ ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል። በመጨረሻ ውጤቱ ለዴሞክራሲ እንደሚሆን ታውቆ በእርቅና በመተማመን መንፈስ ወደፊት ሊገፋ ይገባዋል እንጂ ተደነቃቅፎ ወደ ኋላ መቅረት ሀገርን የሚጎዳ ይሆናል። ይሄም ሂደት ጊዜ ሳይሰጠው በፍጥነት መጀመር ይኖርበታል።

ለውጥን መሻት በራሱ ግብ አይደለም። ይልቁንም እንዲመጣ የምንፈልገው የለውጥ አይነትን በውል ከመነሻው ለይተን አውቀን፣ ለተፈፃሚነቱ መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ወንዝ መሃል ላይ ፈረስ ለመቀየር ልንገደድ እንችላለን። በጭፍን ለውጥ ጠያቂ ከመሆን አልፈን ለውጡ የሚሳካበትን መንገድ በቅጡ ሊበየን ይገባል። በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዕሳቤ ከተጓዝን ችግር ሊገጥመን ይችላል። ለምን ቢባል አንዳዴ የፖለቲካ ለውጥ የመጣበት መንገድ ከውጤቱ እኩል ፋይዳ ስላለው። አንዳንድ ሃገራት ለበጎ ግብ ተነስተው የሚጓዙበት መንገድ የተሳሳተ ሆኖ ያልፈለጉት ውጤት አስመዝግበዋል። በሌላ በኩል ለውጡ የመቀልበስ አደጋ ሊገጥመውም ይችላል። ሀገራችን ላይ በተጀመረው የለውጥ መስመር ላይ ሁለት ተወዳዳሪ የለውጥ አማራጮች ወደ ፊት ሲገፉ ይታያሉ። አንደኛው ስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ የሚባለው መንገድ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ሂደታዊ ለውጥን ተመርኩዞ የሚሰራ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ነው። የትኛው የተሻለ  አዋጭ ነው የሚለውን ለመገምገም ያስችለን ዘንድ ባጭሩ እንቃኛቸው።

ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ሃይሎች ስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ በተቻለ ፍጥነት እውን እንዲሆን እየወተወቱ ይገኛሉ። ለዚህ አፈፃፀም ያመች ዘንድ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል እቅድ ወደ ፊት ይገፋሉ። የሽግግር መንግስት መመሥረት ብቸኛው ከአምባገነንናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት መሸጋገሪያ መንገድ ነው ብለው በጽኑ እንደሚያምኑ በተለያዩ መድረኮች ከሚያነሷቸው ሃሳቦች ለመረዳት ይቻላል።

የሽግግር መንግስት ይቋቋም ጥያቄም ሆነ እራሱ የሽግግር መንግስት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንግዳ ጉዳይ እንዳልሆኑ ሁላችንም የምንረዳው ነው። ጊዜያዊ መንግስት ማቋቋምም ሆነ ወደ መደበኛ መንግስት የመሸጋገር ልምዳችን የሚነገረን ከአንዴም ሁለቴ እንዳልተሳካልን ነው። በሁለቱም ጊዜ በሽግግር ስም ቀድሞ ስልጣኑን የያዙት ሃይሎች ሃሳብ ፍላጎታቸውን ከመጫን አልፈው ሃገሪቱን ቁልቁል ሲነዷት እንጂ የተሻለ ሽግግር ሲያደረጉ አላየንም። አለ የሚል ካለ ለሙግቱ ዝግጁ ነኝ። ዛሬ ምን ዋስትና ኖሮን ነው የሽግግር መንግስት ይመስረት ብለን የምንሞግት? ለመሆኑ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚፈቅድ ውስጣዊና አከባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታ አለን? በተለይም ነበረን የምንለው ማህበራዊ እሴቶቻችን (social capitals) ሁሉ ተሟጠው እርስበርስ ለመጠፋፋት ስለት በምንማዘዝበት ወቅት፣ ከመንግስት ስልጣን ውጪ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ርዕዮት አለም እያራመዱ እንኳን በጥቃቅን የጥቅም ወይንም ግለሰባዊ ግጭት መተማመን ባልቻሉበት ሁኔታ፣ በሀገር ውስጥና በውጪ ሃገራት  የሚኖሩ የፖለቲካ አቀንቃኞች ተቀራርበው ለመነጋገር አይደለም ጎን ለጎን ለመተላለፍ ጽዩፍ የሆኑበትን የፖለቲካ ባህል ይዘን ነው ዛሬም ጊዜያዊ መንግስት ይቋቋም የምንለው? የሽግግር መንግስቱስ ከተቋቋመ በኋላ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገራችን ያለን ዋስትና ከቶ ምን ይሆን? ከመቶ የማያንሱ ጥቃቅን እና እራሳቸውን እንደ ትልቅ የሚቆጥሩ ግን ደግሞ ያልሆኑ የዘውግና የህብረ ቤሔራዊነትን አቀንቃኝ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳችም አስተማማኝ ስራ መሬት ላይ ሳይሠሩ፣ ከምር ከገዢው ግንባር ጋር የሽግግር መንግስት መስርተው እንዳሰቡት ስኬታማ ሽግግር እናደርጋለን? የህዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ምንድን ነው? በህዝብ ውስጥ ያለው ስጋት ምንድን ነው? የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚሉት ወገኖች ቀላል እና ፈጣን ግን ደግሞ ሳይንሳዊ የዳሰሳ ጥናት እንኳን አድርገው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማገናዘብ ሙከራ አድርገው ያቃሉን? ወይንስ የፖለቲካ መሪ ተብለው የተሰየሙት ከየወሬ ማሰራጫዎች በሚሰሙት ትንተና ነው መሬት ላይ ላይ ያለውን የሚለኩት? የፖለቲካ ድርጅቶቹ በህዝብ እየተመሩ ነው ወይንስ ህዝብን እየመሩት?

እውነት ነው ህዝብ ምን ጊዜም ቢሆን ጥያቄ ያነሳል። ለመብቱ ቀናአይ፣ ለህልውናው ሥጉ የሆነ ማህበረሰብ የሚበጀውን እስኪያገኝ ድረስ ይሞግታል። ፖለቲካ በህዝብ ፍላጎት ሊመራ እንጂ በህዝብ መሪነት ግን ሊመራ አይችልም። ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ ክብር፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ የዜግነት ዋስትና፣ ስራ፣ ልማት፣ ብልጽግና፣ በልቶ የማደር ዋስትና፣ በሀገሩ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ፣ ባይተዋርነት ሳይሰማው በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የመኖር ወዘተ….. ወዘተ። እነኚህ ሁሉ የግድ መሳካት የሚችሉት የሽግግር መንግስት በመመሥረት ነው? ለመሆኑ የሽግግር መንግስት እናቋቁም፣ በዚህ እንስማማለን በዚህ አንስማማም እያልን እንድንተራመስ ያለንበት የአከባቢ ሁኔታ ይፈቅድልናል?  እነኚህ ብቻ ሳይሆኑ ለሎችም የነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳና ትንታኔ ሳይደረግ፣ ካለፈው ተመኩሯችን እና ታሪካችን ትምህርት ሳንወስድ፣ ሌሎች ሃገራት እንዴት ያለ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደት ውስጥ አልፈው በስኬት ተወጡት እና የመሳሰሉትን ወሳኝ ጉዳዮችን ሳንመዝን ባወጣ ያውጣው ብለን የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለውን ጥያቄ ማቀንቀን ብዙ የሚያራምድ አማራጭ አይሆንም።

ሀገራችን ላይ እንዲመጣ የምንሻው የብዝሃነት ዴሞክራሲ፣ ዝመናና ልማት፣ ልንገነባቸው የገቡን ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት፣ እንዲኖረን የምንፈልገው የፖለቲካ ባህል፣ ህግ ላይ ተመስርቶ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን የምንሻ ፖለቲካ፣ ፖለቲከኞቻችን እንዲኖራቸው የምንፈልገው ፖለቲካዊ ተክለ-ስብዕና ከስሜት፣ ከጎጠኝነት፣ ከቡድነኝነት የፀዳ ሆኖ ምክንያታዊ እንዲሆን፣ የሀገራችን ህዝብ ከሰለባ ስነ-ልቦና ተላቆ ለአንዲት ሀገራችን የከፈለውን ዋጋ እያሰበ የሀገር ባለቤት መሆኑን በኩራት እንዲመሰክር የሚስችለውን አቅም ያገኝ ዘንድ ልንሻገረው የሚገባን አዘቅት፣ ልንሰብረው የሚጠበቅብን አዙሪት አለ። ከኖረው የቸከና የመነቸከ ባህላዊ ፖለቲካን የመረዳት አስተምሮታችን ተሻግረን አዲስ የፖለቲካ መተግበሪያ (Ways of ‘Doing’ Politics) መስራት ያስፈልገናል።  የምንተገብረው የፖለቲካ ሞዴል አፍርሶ በፍርስራሽ ላይ ሌላ ፈራሽ ሥርዓት ከመትከል እርግማን የተላቀቀ መሆን አለበት። ጊዜው ደግሞ አሁን መሆን አለበት። በመሆኑም ስር ነቀል ለውጥ ለተባለው ግብ መዳረሻ የሽግግር መንግስት ማቋቋም አያዋጣም የሚል ክርክር ከተነሳ አልቀረ አማራጩን መንገድ መፈተሽ የተገባ ነው።

በእኔ እምነት ከደረስንበት የፖለቲካ እድገትና ካለንበት ሃገራዊና አከባቢያዊ ፈታኝ ሁኔታዎች በመነሳት፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድርግ ብንከተለው የሚያዋጣን ሂደታዊ ለውጥ (transplacement) የተባለው አማራጭ ነው የሚል አቋም አለኝ። ሳሙኤል ሃንቲግተን የተባለ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሀያኛው ክፍለዘመን መባቻ ላይ የተካሄዱ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግሮች  በተነተነበት “The Third Wave: Democratization in the Late Twentieth Century” በተባለው መጽሐፉ ካስተዋወቃቸው የለውጥ መተግበሪያ ዘዴዎች አንዱ ስለሂደታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር (transplacement) ነው። በሃንቲግተን እይታ በሂደታዊ ለውጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እውን ሊሆን የሚችለው አገዛዝ ላይ ባለው መንግስት እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ወገኖች ጥምር ጥረት ነው። መንግስት በሚወስዳቸዉ ህጋዊ ማሻሻያዎች፣ በሚፈጥራቸው የተደላደለ ምህዳሮች እና የሊብራላዜሽን እርምጃ ላይ ተመስርቶ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይሎች በመደበኛና ኢ-መደበኛ በሆኑ የድርድር መስመሮች ተጠቅመው ለውጡ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋፆ  ያደርጋሉ። ምንም እንኳን የተቀዋሚ ሃይሎች በመንግስት ውስጥ ባሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቡድኖች ላይ ተጽኖ የመፍጠር አቅም ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ቢታመንም እንኳን፣ መንግስትን ግን ገልብጠው አዲስ ስርአት መትከል የማይችሉበት ሁኔታ፣ በዚህ አይነት የሽግግር ዘዴ መታገዝ ካልቻለ ሀገርን አደጋ ላይ ይጥላል። በመሆኑም ከመንግስት ውስጥ የለውጥ ፋና ወጊዎች በሚነሱበት ወቅት ከነዚህ ሃይሎች ጋር በተገቢው መንገድ በመደራደር፣ ስምምነት በመፍጠር (concession)፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ እየተመሩ ስርዓቱን ከጨቋኝነት ወደ ዴሞክራሲያዊ መድረክነት ለማሸጋገር ይቻላል ይላል።

ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተዋረድ እና የጎንዮሽ የሆኑ በርካት ጽንፎች አሉ። እነኝህን ጽንፎች ማቀራረብና መካከለኛ መስመር ላይ ማምጣት ረዥም ጊዜ ይጠይቃል። በፖለቲካ መስመር ውስጥ ዴሞክራቶች እና ፀረ-ዴሞክራሲያን በተለያየ ጎራ ተሰልፈው ገመድ በሚጓተቱበት ሰርዓተ ማህበር ውስጥ በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲን የወል ግብ ማድረግ ከባድ ይሆናል። ለዚህም ነው ተጀምሯል ያልነው የለውጥ መስመር የአኩራፊ ቀደምት የስልጣን ወሰን አስጠባቂ ወገን እና የፀጥታ ሃይሉ ጥላ የአጠላበት ነው የምንለው። ተደጋግሞ የሚቀርበው ማስረጃ ዶ/ር አብይ አዲስ የተባለውን ካቢኔ ያዋቀሩበት መንገድ ነው። በተጨማሪም ጡረተኞቹ የህውሃትና የብአዴን መሪ ተብዬዎች ከሰሞኑ መቀሌ ላይ ሲናገሩ እንዳዳመጥነው ለ27 ዓመታት በተጓዙበት መንገድ ለመቀጠል እንደሚፈልጉ ቢያንስ ቅዠታቸውን ነግረውናል። በመሆኑም ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ሰላማዊ፣ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ሂደቱ ከላይ ወደታች (top-down) መሆን ያለበት እና በአንፃራዊነት ዘገምተኛ (gradual approach) ሂደትን መከተል ያለበት። በመሰረቱ ዴሞክራሲን ከታች ወደ ላይ (democracy from below) ሞክረነው ካንዴም ሁለቴ ከሽፏል። ለዚህም ነው ሦስተኛውን አብዮት በሃይል ለማምጣት ከሞክርን ያሰብነውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያለመሳካት ስጋት ብቻ ሳይሆን ሀገርን የሚሰዋ አደጋ ሊሆን የሚችለው።

እውነት ነው  ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የለውጥ ንቅናቄ  የፈጠረውም ሆነ አዳዲሶቹን መሪዎች ወደ ስልጣን ማማ ያመጣቸው የህዝብ ግፊት ነው። ይሁንና ለውጡ ከግብ እንዲደርስ ባለቤት ያስፈልገዋል። የለውጥ ሃዋርያ ሆነው ብቅ ያሉት ሰዎች በያዙት መስመር ወደ ፊት እንዲጓዙ እድል ሊሰጣቸው ይገባል። ከቦታ ቦታ እየተዟዟሩ ለመፍጠር የሚሞክሩት የማረጋጋትና የጋራ ሃገራዊ ራዕይ የመፈጠር ሂደት፣ ዝግባ ዝግባ የሚያክሉ የአገዛዙን ሰዎች ከመድረኩ ገለል የማድረግ ሙከራው፣ የሥርዓት ሽግግሩን ለማስጀመር ጎባጣን የማቃናት ረባዳውን የመደልደል ጅምር ስራ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በብዙዎች እንደሚባለው ስርዓታዊ መዋቅሩን በአንድ ጊዜ ከላይ እስከታች በመናድ አዲስ መዋቅር መትከል ቀላል ጉዳይ አይሆንም። ይልቅ ደረጃ በደረጃ ማሻሻያዎች እያደረጉ የተቋማትን ይዘትና ቅርፅ በመቀየር ለውጡን የተሳለጠ (readjust) በማድረግ አላስፈላጊ ግጭትን ወይም የለውጥ ተቀዋሞን መቀነስ ያስችላል። ተቋማትና መዋቅሮች በሂደት ሲለውጡ ህግጋትና ፖሊሲዎች አብረው እየተሻሻሉ ይመጣሉ።

ይህን መሰሉ ሂደታዊ ለውጥ ፋይዳው ዘረፈ ብዙ እንዲሆን ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ለተቃዋሚ ሃይሎች የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሲቪል መብቶች፣ የፖለቲካ ነፃነቶች እየሰፉ ሲመጡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ከኖረው የተሳዳጅነት መንገድ ወጥተው፣ ሃሳብና ሃይላቸውን ተደራጅተው በተሻለ መስተጋብር እና የድርድር አቅም በመቅረብ ገዢውን ሃይል ለመሞገትም ሆነ  እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ እውን እንዲሆን የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል። ምናልባትም ከሁለት አመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ላያሸንፉ እና ስልጣን ላይዙ ይችሉ ሁሉ ይችላል። በቀጣይ ምርጫዎች የተሻለ አቅም አደርጅተው መምጣት ከቻሉ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመሰረቱ ሃገራት የምናየውን ሰላማዊ ሽግግር ለምድረግ አቅም ይፈጥርልናል።

የፖለቲካ ለውጥ በመጣባቸው በርካታ ሃገራት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሲደረግ የተከተሉት የተለያየ ሞዴል እንዳለ  ይታወቃል። ከዚህ ረገድ ሁሉንም ሃገራት ለማካተት አስቸጋሪ በመሆኑ በሂደታዊ ለውጥ (transplacement) መንገድ ከአምባገነንዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገሩ ሁለት ሃገራትን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ስፔንን ከአውሮፓ፣ ደቡብ ኮርያን ከሩቅ ምስራቅ ሃገራት ወስደን ባጭሩ ዴሞክራሲያዊ ሽግግራቸውን በሂደታዊ ለውጥ እንዴት እንደገነቡ እናጣቅስ።

ከደቡብ አውሮፓ ዘግይተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተከሉ ሃገራት መካከል አንዷ ስፔን ነች። ስፔን በፋሽስቱ ጀነራል ፍራንስኮ ፍራንኮ ለአርባ አመታት ያህል በከባድ የአፈና፣ የጭቆና፣ የጭፍጨፋ እና የማሳደድ መራር መከራውስጥ አልፋለች። በፍራንኮ  የመጀመሪያዎቹ ሦስት የስልጣን አመታት ሃገሪቱ በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ አልፋለች። ካታላንን፣ ባስክ ካንትሪን እና ጋሊሲያ የተባሉት የስፔን ግዛቶች በቋንቋቸው የመስራት፣ የማስተማር እና እራስን በራስ የማስተዳደር እድል ተነፍገው በመሰንበታቸው የመገንጠል  ጥያቄን ጭምር አንግበው ሲታገሉ ቆይተዋል። በተለይ የባስክ ተገንጣዮች የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ ጭምር ተሳትፈዋል። የሶሻሊስትና የኮሚኒስት ፓርቲዎች በህግ ታግደው አባሎቻቸው ይሳደዱና በተገኙበት ይረሸኑ ነበር። ስፔን ውስጥ የነበረው ፖለቲካዊ ድባብና ሁነት በተወሰነ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ነበረው። እ.ኤ. አ 1975 ፍራንኮ መሞቱን ሲረዳ ስልጣኑን እንዲወረስ ያጨው ዙፋኑን ገልብጦ ከሀገር ያባሮት የነበረውን ንጉስ ልጅ ሂዋን ካርሎስ ነበር።  ካርሎስ ከአስር አመት እድሜው ጀምሮ በፍራንኮ ቤት ነው ያደገው። አዲሱ ንጉስ ካርሎስ የወታደሩና የፍራንኮ ታማኝ ዙፋን አስጠባቂዎች ከፊል ድጋፍ ነበረው። ካርሎስ የንግስናውን ስፍራ ይዞ ለጠቅላይ ሚንስቴርነት አዶልፎ ሶዋሬዝ እንዲሾም አደረገ። ሶዋሬዝ ጠቅላይ ሚንስቴር ሲሆን የ40 አመት ጎልማሳና ለውጥ ናፋቂ ተራማጅ የነበረ ቢሆንም እሱም ቢሆን በፍራንኮ ዘመን ቁልፍ ስፍራ የነበረው፣ በስርዓቱ ተኮትኩቶ ያደገ ሰው ነበር። የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጥያቄ ቢደግፍም ከአክራሪ የፍራንኮ ባለስልጣናት፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሚሊተሪው ማስፈራራትና ተጽኖ እየደረሱበት ነበር ህዝቡ የሚፈልገው አይነት ለውጥ እንዲደረግ ጥረት ሲደርግ የቆየው። የህገ-መንግስት በማስቀረጽና በማጸደቅ፣ በርካታ አፋኝ የሆኑ ህጎችን በመሻር፣ አዳዲስ ህጎች እንዲወጡ በማድረግ የለውጡን ሂደት አስጀመረው።  በሂደት ያታገደው የነበሩ ፓርቲዎች ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ፖለቲካው መስመር ገብተው እራሳቸውን በማዋሃድና በማጠናከር፣ ከመንግስት ጋር ጠንካራ የሚባሉ ድርድሮችን በማድረግ ለውጡ እውን እንዲሆን አስችለዋል። ከሀገር የተሰደዱ የየግዛቶቹ መሪዎች ተመልሰው የራስ-ገዝ አስተዳደር መስርተው ክልላቸውን እንዲያስተዳድሩ እድል ተሰቷቸዋል። ይሄ ሁሉ ሆኖ የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ሁለት አመታትን ወስዷል። በ1978 አሁንም እ. ኤ. አ በተደረገው ምርጫ ያሸነፈው የሱዋሬዝ ፓርቲ ነበር። ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች በተደረገ ቁጥር የአሮጌው ስርአት ጥቅም አስጠባቂዎች መቆጣታቸውን፣ ሚሊተሪው ማስፈራራቱን አልቀነሰም ነበር። በተለይ 1981 እ. ኤ. አ በአዲሱ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎ ከሽፏል። በሁለተኛው ዙር ሶሻሊስትና ኮሚኒስት ፓርቲዎች ተዋህደውና እራሳቸውን አጠናክረው በመምጣት 1982 እ. ኤ. አ  በተደረገው ምርጫ አሸንፈው የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥረዋል። በስፔን ምድር ይህ አይነት ሽግግር ሲደረግ ሀገራችን በአብዮት ማግስት ላይ ትገኝ ነበር። ለበርካታ መቶ አመታት ያህል የኖረው ሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት በህዝብ አመጽ ተገርስሶ ወድቆ ወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት የተተካበት ዘመን።

የስፔናውያንን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ከአገዙ እና እንዳይደናቀፍ ከአደረጉ ጉዳዮች መሰረታዊ የሚባለው የመርሳት ፖለቲካዊ ውስኔያቸው (El Pacto de Olvido/ The Pact of forgetting) አንዱ ነው። በለፈው አርባ አመት የሆነውን ነገር ሁሉ ረስቶ በወደፊቱ ላይ ብቻ ማተኮር በሚለው ውሳኔያቸው በመስማማታቸው ባለፈው ጥፋት ከቀኝም ከግራም በኩል የተከሰሱና በፍርድ ሂደት ውስጥ ያለፉ  አልነበሩም። ያለፈው ምዕራፍ ተዘግቶ በወደፊቱ ጉዳይ ላይ ሃይላችንን እናውል የሚለው አቋማቸው ሽግግራቸውን ከቂም በቀል የፀዳና ዴሞክራሲያቸውም ዘላቂ እንዲሆን እድል ሰጥቷል። እውነት ነው በዚህ የመርሳት ፖለቲካ የተከፉና ዛሬም ድረስ የፍትህ ያለ የሚሉ ወገኖች ስላሉ ድምፃቸውን በተቀዋሞ ያሰማሉ። ቢሆንም ግን ሀገራቸው በአንፃራራዊነት በሰላም ለረጅም አመታት በተሻለ ብልጽግና ወደፊት ተጉዛለች።

እንደሚመስለኝ የዶ/ር አብይ ንግግሮች ላይ የሚንፀባረቀው አቋም ይሄው ነው። ያለፈውን ወደ ኋላ  ትተን ወደ ፊት ያለውን ለማስዋብ እንጣር ማለታቸው። ከፍትህ አኳያ ይህ አይነቱ የመርሳት ውሳኔ ከባድ ጥያቄ ያስነሳል። ሆኖም ከጠቀመን ለምን አንሞክረውም?

ደቡብ ኮርያ ከአምባገነናዊ ወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተሸጋገረችው እ. ኤ. አ 1987 ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው አብዮት ከመደረጉ አራት አመታትን ብቻ አስቀድሞ  በነበረው ጊዜ መሆኑ ነው። የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ያስገደደው ህዝባዊ አመፅ ነበር። የቹን ዱዋን መንግስት በደረሰበት ከፍተኛ ጫና ለተተኪው ሮህ ቲ ው ስልጣን በማስረከብ ገለል ሲል፣ ሮህ እና እሱን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው የኪም ያንግ ሳም መንግስቶች የደቡብ ኮርያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲፋጠን ከፍተኛ የሚባል ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያዎችን እና  የተቋማት ማደራጀቶችን በመስራት ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ከውስጥ ወደ ውጪ እንዲሆን አስችለውታል። በሃንቲግተን ትንተና የደቡብ ኮርያው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደታዊ ለውጥ ለሚባለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ ማሳያ ሞዴል ነው።

መንግስት የመግባቢያ ሃሳቦችን ሲያቀርብ ተቀናቃኝ ቡድኖች እየተቀበሉና እየተደራደሩ፣ ልዩነቶችን በማመቻመችና በጋራ መጠፋፋትን (mutual catastrophe) ተሻግረው አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በቅተዋል። በሂደት በርካታ መዋቅራዊ ሽግግሮችን በመተግበር በነበረው ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን በማድረግ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንዳይደናቀፍ ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል ። በደቡብ ኮርያ ሁኔታም ቢሆን ተቃዋሚዎቹ በምርጫ ተወዳድረው በቶሎ ወደ ስልጣን አልመጡም። ይልቁንም እራሳቸውን የበለጠ እያደራጁና እያጠናከሩ ቆይተው፣ ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው በኋለኛው ዘመን ነው በምርጫ ማሸነፈ  የጀመሩት።

በዚህ ጹሑፍ ለመዳሰስ እንደተሞከረው ሀገራችን አስፈሪ ከነበረው የመበታተን አደጋ ለጊዜውም ቢሆን ተርፋ የለውጥ ተስፋን ከሩቅ ማየት የጀመርን ይመስላል። ይሁንና ሊመጣ ያለው ለውጥ ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ ተግዳሮቶች የተከበበ በመሆኑ አስተማማኝ መደላድል ላይ አልቆመም። በመሆኑም በብዙዎች መስዋእትነት የተገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን ተገቢውን ድጋፍ ከሁሉም ወገን ሊያገኝ ይገባዋል። በሌላ በኩል በለውጡ መድረክ ላይ ከሚቀርቡ በርከት ያሉ አማራጮች መካከል ለሀገራችን ነባራዊ ሁነቶች አመቺና ተስማሚ ነው የምንለውን መርጠን መውሰድ ይጠበቅብናል። በዚህ ጹሑፍ ለማመልከት እንደተሞከረው ከስር ነቀል (radical) ለውጥ ይልቅ በቆይታ እየተገነባ የሚሄድ ሂደታዊ ለውጥ (transplacement) ካለንበት ሁኔታም ይሁን ከሌሎች ሃገራት ተመኩሮ  አንፃር የሚሻለው የስርአት ሽግግር ዘዴ ነው ብዬ አምናለሁ። ለማጠቃለል ያህል የዚህን መንገድ ሦስት ዋንኛ ትሩፋቶችን በአጭሩ ልጥቀስ።

  1. በሂደታዊ ለውጥ የሚመጣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለውጡን ሊቀለብሱ የሚችሉ ሃይሎችን አቅም እየቀነሰ  ስለሚሄድ ግጭትና አላስፈላጊ አሉታዊ ተጽኖዎችን (unintended consequences) የመቀነስ አቅም አለው።
  2. በድርድር፣ በመግባባት፣ ሰጥቶ በመቀበልና በይቅር ባይነት ላይ የሚመሰረት ፖለቲካዊ ሽግግር የአብዛኛውን ወገን ይሁንታ የሚያገኝ በመሆኑ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዘላቂና አስተማማኝ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።
  3. ተቃዋሚ ሃይሎች እርስበርስ ከመሻኮት ወጥተው በጋራ አቋሞቻቸው ላይ በማተኮር ሃይል የማሰባሰብ፣  የማደራጀት፣የጠራ መስመር ለሚያዝ የሚያስችል እድልና ምቹ ጊዜ ይፈጥርላቸዋል።

በነዚህም ሂደቶች አስተማማኝ፣ ተራማጅ፣ አርቆ  ተመልካች የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር፣ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል አቅም በሂደት እንፈጥራለን። ሀገራችንን ከውድመት፣ ህዝባችንን ከጥፋት የሚያተርፍ፣ ፖለቲካችንን መውጫ  ከጠፋበት የአምባገነንነት አዙሪት ውስጥ ሊያወጣልን ከቻለ፣ የምንናፍቀውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊገነባልን ከቻለ፣ ደም አፋሳሽ ከሆነው አብዮት በመለስ ያለን ሂደታዊ ለውጥን ብንሞክረው ምን ይለናል? አበቃሁ!