የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እያካሄደ ያለው ሪፎርም ያከናወናቸውን ተግባራት ይፋ አደረገ

ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በሪፎርም ስራዎች ያከናወናቸውን ተግባራት ይፋ አደረገ

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እያካሄደ ያለው ሪፎርም ተልዕኮውንና የስራ ባህሪውን ግምት ውስጥ በማስገባት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ፕሮፌሽናል ተቋም መመስረት ላይ ነው፡፡

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል የተቋሙ የ100 ቀን እቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ እንዳብራሩት፤ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ባካሄደው የሪፎርም ስራ ተቋሙን እንደገና ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አጠናቋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ አሁን ያለው የተቋሙ ስያሜ በአዲስ የሚቀየር ይሆናል፡፡ አዋጁን መነሻ በማድረግም ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች እንደ አዲስ ተቀርጿል።

በተጨማሪም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚመራበት ስትራቴጂክ ዕቅድ የተጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ስትራቲጂክ ዕቅዱ ተቋሙ ከፖለቲካ ገለልተኛ፣ ብሄራዊ ጥቅምን እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮፌሽናል የመረጃ ተቋም እንዲሆን አቅጣጫ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶች ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች ሰነዶችም ጭምር በሪፎርም ሂደቱ ተዘጋጅተው በተለያየ ደረጃ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ባለፉት ወራት ተልዕኮውን የሚመጥንና ከታወቁ ዓለም አቀፍ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው አሰራርና አደረጃጀት ከመፍጠር አንፃርም በርካታ ስራዎች በሪፎርም ማዕቀፍ ስራ ተከናውነዋል፡፡ ለአብነትም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ስጋቶችንና ሊፈጸሙ የሚችሉ አሻጥሮችን እንዲሁም ከባድ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈለጊ መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል የሚያቀርብ የኢኮኖሚ ደህንነት ዋና መመሪያ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ሙያዊ ብቃትን፤ የትምህርት ውጤትንና ስነ-ምግባርን እንዲሁም የብሄርና የፆታ ስብጥርን ግምት ውስጥ በማስገባት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንን በመመልመልና በመረጃ ኪነሙያ በማስልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ተግባራት በሪፎርሙ ተከናውነዋል፡፡ የሰው ሀይል አቅምን ከማሳደግ አንፃር ሰራተኞች በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የትምህርት ዕድሎችን አግኝተዋል፡፡

በቀጣይ ለሰው ሀይል አቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠትም ቀድሞ የነበረውን የስልጠና ተቋም በከፍተኛ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ፕሮግራሞቹን በማስገምገም በኮሌጅ ደረጃ በማሳደግ የብሄራዊ የመረጃ ኮሌጅ በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ እና ወደ ስራም እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ኮሌጁ በቀጣይ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ በተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም ለማደራጀት ልምድና አቅሙ ካላቸው አቻ ዓለም አቀፍ የመረጃ ተቋማት ጋር በተደረሰ ስምምነት በርካታ ስራዎች እና አቅሞች እየተፈጠሩ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

የተቋሙን የሪፎርም ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ባለፈው ወር ከአመራሮችና ከሰራተኞች ጋር ጥልቅ ውይይቶችና ግምገማዎች ተደርግዋል፡፡ በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስምሪት የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩት የማበረታቻ እንዲሁም የስነ ምግባር ችግር የታየባቸውን ግለሰቦች ከስራ የማገድ፤ ጉዳያቸውም በህግ አግባብ እንዲታይ የማድረግና በሌሎችም ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ሪፎርሙን ተከትሎ በሁሉም ዘርፎች ያመጣቸውን ውጤቶች በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡ ሁሉንም ዜጎች በፍትሃዊነት የሚያገለግል የመረጃ ተቋም ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ህዝቡ በባለቤትነት ከተቋሙ ጎኑ እንዲቆም ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ተቋሙ የሪፎርም ስራዎችን ያከናወነው ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ እንዳይሆኑና የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትሉ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለመንግስት ውሳኔ በግብአትነት እንዲውሉ ከማድረግ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃና በቀጣናው ስጋት የሆነው ሽብርተኝነት በአገሪቱ ላይ ደቅኖት የነበረውን አደጋ በማስቀረት ረገድ ተቋማዊ ተልእኮውን ተወጥቷል፡፡

ምንጭ፡- ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት