“በአማካሪ ስም የተቀመጡትን የህወሓት ካድሬዎችን በሙሉ አስወግጄ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን እና ተወላጆች ቦታ እንዲይዙ አድርጌለሁ” አቶ ኦኬሎ አኳይ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት

“በአማካሪ ስም የተቀመጡትን የህወሓት ካድሬዎችን በሙሉ አስወግጄ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን እና ተወላጆች ቦታ እንዲይዙ አድርጌለሁ” አቶ ኦኬሎ አኳይ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት
(ኢፕድ)
• ይህን በማድረጌና አዲስ መዋቅር በማበጀቴ ችግር ደርሶብኛል፡፡ መዋቅሩ ካድሬዎቹን በማንሳፈፉ በህወሓት ዘንድ ንዴት አስከተለ፤ ችግሩ እስከ ግድያ ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡

• ያ ወቅት ሆን ተብሎ ብሄር ከብሄር እንዲጋጭ የሚደረግበት ጊዜ ነበር፡፡ ግንባሩ ቀደም ሲል ብሄርን ከብሄር ያጋጭ ነበር፡፡

• ህወሓት እቅድ በማውጣት የሰው ህይወት ወደማጥፋት አኩይ ተግባር ተሰማራ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ዝም ብዬ ማለፍ አልፈለኩምና መልሼ ያዝኳቸው፡፡

• መጀመሪያ ላይ እኔ የክልሉ ፕሬዚዳንት ከመሆኔ አስቀድሞ አኙዋኩን ከኑዌር፣ መዠንገሩን ከአኙዋክ ጋር ሲያጋጩ ነበር፡፡

• ህወሓት ራሱ እቅድ በማውጣት አኝዋክ እንዲጨፈጨፍ አደረገ፡፡ ይህም ከታህሳስ 3 ቀን 1996 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1996 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡

• በወቅቱም መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲጣራ ለማድረግ አጣሪ ኮሚሽን አቋቁሞ ምርመራ አካሂዷል፡፡ የምርመራ ውጤቱም አቶ መለስ ዜናዊ ባሉበት ለፓርላማ ቀርቦ እርሳቸውም አምነዋል፡፡

• የሟቾቹ ቁጥር 61 መሆኑን ኢህአዴግ/ህወሓት አስታውቋል፡፡ እኔ በወቅቱ ሊገድሉኝ ስለሚፈልጉ ከሀገር ወጥቼ ነበር፤ጉዳዩን እከታተል ነበርና ግንባሩ የጠቀሰው ቁጥር ስህተት መሆኑን አስታውቄያለሁ፡፡

• የተገደሉት አኙዋኮች ከ400 በላይ መሆኑን ገልጫለሁ፡፡ ከዚህ መረጃ በኋላ ሂዩማን ራይትስ ዎች አጣርቶ ገዳዮቹ እነማን እንደሆኑም ገልጿል፡፡

• ከሂዩማን ራይትስ ዎች በተጨማሪም የዘር ጭፍጨፋውን አስመልክቶ ከስድስት ዓመት በኋላ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱም አኙዋኮች ከመገደላቸው በፊት ኢህአዴግ እቅድ እንደነበረው የሚገልፅ ነው፡፡

• እቅዱ ደግሞ የተቀነባረው በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አማካይነት ሲሆን፣ ወቅቱም እኤአ መስከረም 24 ቀን 2003 ነው፡፡ በእቅዱ ወስጥ የሚገደሉ አኙዋኮች ስም ዝርዝርም ወጥቶ ነበር፡፡

• እኤአ ከታህሳስ ወር 2003 እስከ ግንቦት 2004 ድረስ ሁለት ሺህ 500 ወንድ አኙዋኮች ተገድለዋል፤ 164 ሴቶች ደግሞ ተደፍረዋል፤ ንብረትም ተዘርፏል፡፡ በማሳ ላይ ያለ ሰብል ተመንጥሯል፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ ቤቶችም ተቃጥለዋል፡፡

• ይህ ሁሉ በደል በአኙዋክ ላይ በመደራረቡ ምክንያት ከ20 ሺ በላይ አኙዋኮች አገር ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡

• እነዚህም ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን፣ በዑጋንዳ፣ በኬንያ፣ አሜሪካ፣ አውስትሪሊያ፣ ካናዳ እንዲሁም በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡

• አኙዋኮቹ እንዲገደሉ የስም ዝርዝር በማውጣት ሲተባበር የነበረው የአኙዋክ ተወላጅ መሆኑም ነው፤ እሱም በአቶ መለስ ዜናዊ ታዝዞ የፈፀመ ነው፡፡

• በዚህም መሰረት 762 አኙዋኮች እንዲገደሉ ነው እቅድ የወጣው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግዲያ ምክንያቱ በጋምቤላ ነዳጅ ከመውጣቱ በፊት በመጀመሪያ አኙዋኮችን በመግደል እንዲፈሩ ማድረግ ነው። ነዳጅ በሚወጣበት ጊዜ ምንም ዓይነት ንግግር እንዳይኖርና አፋቸውን ለማዘጋት በመታሰቡ ነው፡፡

• የስም ዝርዝር በመስጠት የተባባረው ሰው ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በኢህአዴግ አስገዳጅነት ወደ ፊሊፒንስ እንዲሄድ ተደርጓል፤ ግለሰቡም ባልታወቀ ሁኔታ እዚያው ሞቶ አስክሬኑ ወደ አገር ቤት መጥቶ ተቀብሯል፡፡

• ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቱ ጋር ውህደት መፍጠሩ መልካም ነው፡፡

• በጋምቤላ ክልል ቀድሞ የነበረው የክልል ስልጣን ለይስሙላ ብቻ የክልሉ ህዝብ የሚተዳደረው በክልሉ ተወላጅ ነው ይባል እንጂ ይህ በአግባቡ ሲተገበር እንዳልነበረ እኔ ምስክር ነኝ፡፡

• አገር በአራት ብሄራዊ ድርጅቶች፣ የእኛ ክልልም ሆነ መሰል አጋር ድርጅቶችን በሞግዚትነት የሚያሾሯቸው ካድሬዎች ነበሩ፡፡

• ይህ ዓይነቱ አስተዳደር ኢህአዴግ ከአጋሮቹ ጋር ውህደት ካደረገ በኋላ አንድ ወጥ ፓርቲ ስለሚሆን ጣልቃ ገብነቱንም ሆነ በክልላችን ያለውን ሀብት ባለመጠቀም የበይ ተመልካች መሆናችንን ያስቀረዋል የሚል እምነት አድሮብኛል፡፡

• በአሁኑ ወቅት የኢዜማ አባል ነኝ፡፡ በጋምቤላ ክልል በመገኘት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ከፓርቲው ጋር በተያያዘ የማደራጀት ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ህዳር 09 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትም ፖለቲካ ዓምድ