በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ዞኖች ጨምረዋል።

DW : በደቡብ ክልል የጌዲኦ ዞን ምክር ቤት አባላት የጌዲኦ ህዝብ አስተዳደራዊ አደረጃጀት በልዩ ሁኔታ አንዲታይልን ሲሉ ጠየቁ። የጌዲኦ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ ዞኑ በቀጣይ ምን አይነት አስተዳደራዊ መዋቅር ሊኖረው ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ በምክር ቤት አባላት የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። ዶቼ ቨለ ( DW ) ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባል አቶ ተካልኝ ፅጌ የጌዲኦ ዞን በመልካ ምድራዊ አቀማመጡ ከሲዳማና ከኦሮሚያ ክልል የምስራቅና የምዕራብ ጎጂ ዞኖች ጋር እንደሚጎራበት ይናገራሉ።

አቶ ተካልኝ በማያያዝም «የሲዳማ ብሄር በህዝበ ውሳኔው ውጤት መሰረት እራሱን ችሎ በክልል የሚደራጅ ከሆነ የጌዲኦ ዞን ከነባሩ ክልል ተነጥሎ ለብቻው ሊቀር ይችላል የሚል ስጋት አለን» ብለዋል። በመሆኑም ዞኑ በቀጣይ ሊኖረው የሚገባው አስተዳደራዊ መዋቅር ዞኑ ካለው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ በመነሳት በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ለምክር ቤቱ ሀሳብ ማቅረባቸውን ነው አቶ ተካልኝ የገለጹት።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ታደሰ ደያሶ በበኩላቸው የጌዲኦ ዞን ቀደምሲል ራሱን ችሎ በክልል እንዲደራጅ ለመጠየቅ የሚያስችሉ ሂደቶች ተጀምረው እንደነበር አስታውሰዋል። «ይሁንእንጂ ክልሉን በገዢ ፓርቲነት ከሚያስተዳድረው ከደቡብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( ደኢህዴን ) የተሰጠ አቅጣጫ ነው በሚል ጥያቄው ባለበት እንዲቆም ተደርጓል» ብለዋል። በአሁኑ የምክር ቤት ጉባኤ ላይ ቀደምሲል ተቋርጦ የነበረው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ካቆመበት እንዲቀጥ በአባላቱ መጠየቁን አቶ ታደሰ ተናግረዋል።

ከአቶ ታደሰ ሀሳብ ጋር እንደሚስማሙ የሚናገሩት አቶ ተካልኝ ፅጌ በበኩላቸው የአደረጃጀት ጥያቄዎች በህዝቦች ፍላጎትና ይሁንታ እንጂ በድርጅት ውሳኔ ሊፈጸሙ አይገባቸውም ይላሉ። አክለውም «የጌዲኦ ዞን በቀጣይ ሊኖረው በሚገባው አስተዳደራዊ አደረጃጀት ላይ ህዝቡ ተወያይቶ እንዲወስን በምክር ቤቱ በኩል ከመግባባት ላይ ተደርሷል»ብለዋል።

ዶቼ ቨለ ( DW) በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በተነሱት የአደረጃጀት ጥያቄዎች ዙሪያ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ እና የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤን አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ የስልክ ቀጠሮዎችን ለመያዝ ቢሞከርም ሃላፊዎቹ ለጥሪዎቹ ምላሽ ባለመስጠታቸው ሊሳካ አልቻለም ።