ቤተክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለው አውዳሚ እና አደገኛ ጥቃት እጅግ በጣም አሳሳቢ፣ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ችግር ነው።

(መስከረም አበራ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለው አውዳሚ እና አደገኛ ጥቃት እጅግ በጣም አሳሳቢ፣ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ችግር ነው።

በቤተክርስቲያኗ ላይ የተቃጣው አደጋ የሚያሳዝነው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዩን ክርስቲያን ብቻ አይደለም ይልቅስ ነገሩ መላውን የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ነው።ከክርስቲያኑ አልፎ ሙስሊም ወገኖቻችንም ይህን ድርጊት እያወገዙ ነው።

ክርስቲያኑ ህዝብ በቤተክርስቲያኗ ላይ የተቃጣው ትልቅ አደጋ፣የአማኞች እና አገልጋዮች አሰቃቂ ሞት ምንያህል እንዳስከፋው ለማወቅ ራሴ በዚህ ወቅት የሚሰማኝን መጥፎ ስሜት ማድመጥ ለኔ በቂዬ ነው። ከወዳጆቼ ጋር ስጨዋወት የማየው መሪር ስሜት ደግሞ በጣም አስጨናቂ ነው።

ሆኖም ክርስቲያኑ ህዝብም ሆኑ መሪ የሃይማኖት አባቶች ሃዘናቸውን በምህላ በፀሎት በሃዘንለፈጣሪ ከማሰማት በቀር ወደ ማንም ምንም አላሉም።ይህ ሰላማዊነት ከጥልቅ መንፈሳዊነት የመነጨ አስተውሎ ነው።ሆኖም ሁሉም ገደብ አለው! በትዕግስት እና ፍርሃት መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ለሁሉም አይገለጥምና ደም አፍሳሾች አሁንም ትምክህታቸው በማረጃቸው ላይ ሆኖ ቀጥሏል። ጉብዝናቸውን በቤተክርስቲያን ላይ እሳት በመልቀቅ እየተመኑ ነው።ሴትን ልጅ ሳይቀር በድንጋይ ወግሮ መግደል የደም አፍሳሹ ፖለቲካቸው እድገት መጨረሻ ነው።

ይህ የእነሱ አውሬነት መጨረሻ የክርስቲያኑ ህዝብ ትዕግስት ማለቅ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ያኔ ሃገር ትነዳለች፣ነዳ ስትንቦገቦግ እሳት የማይበላው ይኖር እንደሆን እናያለን።

ፍቅር እና ትዕግስት ከፍታ ነው፤ከፍታው ሲወርድ ፀብ ይሆናል። ወደ ፍቅር መውጣት እንጅ ወደ ፀብ መውረድ የሚያቅተው የለም።ቁልቁለቱ ገሃነብ እሳት እንደሆነ የገባው ብቻ በፍቅር፣በትዕግስት፣በፀሎት፣በምህላ ይቆያል።ይህ ግን ፍርሃት ወይም ጉልበት ማጣት አይደለም።ሌላው ቢቀር በደል ፣ዋስትና ማጣት ራሱ የሚያመነጨው ጉልበት አለ።ይህ ጉልበት የሚያመጣው ጥፋት ስላልተፈለገ እንጅ ርካሽ መሳሪያ ወድሮ ወደ ቁልቁለት መሮጥ ከብዶ አይደለም!

ክርስቲያኑ ህዝብ ግን ወደ ቁልቁለቱ ሳይሆን ወደ ከፍታው በህብረት ማዝገም አለበት።ህብረቱ ደግሞ በጎንደር እና በሻሸመኔ ክርስቲያኖች ሃዘናቸውን እየገለፁ ያሉበትን መንፈሳዊ እና ሰላማዊ ህብረት በመላ ሃገሪቱ ማድረግ ነው።ማቅ በሚያስለብስ ዘመን ጥቁር መልበስ አያስደንቅም።ሌላው ቢቀር በልብሳችን የልባችንን እንግለፅ፣እንደ ባለ አእምሮ መክረን ሰይፍን በጨዋነት እናሸንፍ።እርግብም እባብም እንድንሆን ነው የተነገረን! (መስከረም አበራ)