ኦነግ ከምርጫ ቦርድ የእውቅና ሰርተፍኬት አገኘ

Image may contain: 1 person, sitting

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «ሀገር አቀፍ» ፓርቲ ሆኖ በይፋ መመዝገቡ አስታወቀ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ተብሎ በምርጫ ቦርድ መመዝገቡ ተሰማ። ኦነግ ላለፉት አስርት አመታቶች ሕጋዊ ሳይሆን በተለያዩ የትጥቅ ትግሎች የቆየ ሲሆን አሸባሪ ተብሎም ተፈርጆ ነበር።

Image

በዛሬው ዕለት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊነቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ መቀበሉን ያረጋገጠው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሚጠቀምበት ሰንደቅ ዓላማ እና ዓርማ ሕጋዊ መሆናቸው እንዲታወቅለት ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው ባሰራጨው መረጃ «ዛሬ ኅዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕጋዊ ፓርቲነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መቀበሉን» ገልጿል። ከተመሰረተ 46 ዓመታት ያስቆጠረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር «በሰላማዊ መንገድ እንዳይታገል ሲገፋ፤ አገር አፍራሽ የሚል ስም ተሰጥቶት በጠላትነት ተፈርጆ ሲዘመትበት» እንደነበር በማኅበራዊ ድረ ገፆች ባሰራጨው መረጃ ጠቁሟል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ አስመራ ሔደው ካደረጉት ድርድር በኋላ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በአሁኑ ወቅት «በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ መጥቷል ባይባልም እዚህ መድረሳችን በራሱ የትግላችን ውጤት እና ተስፋ ሰጪም ነው» ብሏል።

«በዚህ ዕድል በመጠቀም ዛሬም ላልተፈቱ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንሰራለን ያለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አድርጓል ላለው እንቅስቃሴ አመስግኗል። የሮሞ ነፃነት ግንባር ሕጋዊ «ሰንደቅ ዓላማ እና አርማ ይዘው በእኛ ድርጅት ስም የሕዝባችንን ስም የሚያጠለሽ እንዲሁም ከሕዝቦች ጋር ለማጋጨት የሚሞክሩ ካሉ ሕዝባችን ተከታትሎ እንዲያጋልጣቸው» ጠይቋል።