በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መኖሪያ የእሳት አደጋ በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም

(ኢዜአ)  በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በአንድ የተማሪዎች መኖሪያ ክፍል ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉንና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምእሸት ተሾመ እንደገለጹት በአደጋው በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በሚያድሩበት “ዲ.ኤስ.ኤም ህንጻ” የመኝታ ክፍል ቁጥር 09 ላይ ትናንት ድንገተኛ የእሳት አደጋ መከሰቱንና የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች ባደረጉት ርብርብ ከአንድ ሰዓት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

አቶ ዓለምእሸት እንዳሉት ባልታወቀ ምክንያት ከቀኑ 7፡30 ሰዓት ላይ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ የአንድ መኝታ ክፍል ንብረት ቢወድምም በሰው ሕይወት ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም።

በተደረገው ርብርብ አደጋው ሳይስፋፋ ወዲያውኑ መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጸው የአደጋውን መንስኤ ፖሊስ በማጣራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሕብረት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ተማሪ ፍራንክሰን ጉደታ በበኩሉ “በክፍሉ ውስጥ የደረሰው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል” ብሏል።