በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሰባት ፓርቲዎች በክልሎቹ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚታየው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) እና የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ግንባር በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው የገለጹት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መግለጫ የሰጡት 7 ፓርቲዎች በጋራ

ፓርቲዎቹ ትላንት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፤ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር ከሚያላሉና ወደ ብጥብጥና ከሚያመሩ ማናቸውም ተንኳሽ ጉዳዮች ለመቆጠብና በሕዝቦች ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ለመቀልበስ በመተባበር ለመሥራት መወሰናቸውንም ተናግረዋል።

“ልዩነቶች ቢኖሩንም፣ ልዩነቶቻችን ከአገራችን እና ሕዝባችን የማይበልጡ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ለአገሪቱ ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

ፓርቲዎቹ በሁለቱ ክልሎች እና ዩኒቨርስቲዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ የድርሻቸውን በመወጣት፣ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች አንድነት ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የዛሬ ሳምንት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰውና የሁለት ተማሪዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ጥቃት በኋላ በደምቢዶሎ፣ በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲም ተማሪዎች መሞታቸው ተሰምቷል።

እስካሁን ድረስ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ጥቃት ተሳትፈዋል የተባሉ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሰላም ለማስፈን የጸጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ይገኛሉ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር በዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ የተከሰተውን ለመቆጣር እየሠራ መሆኑን ገልጾ፤ ግጭቱን መቆጣጠር ከአቅሜ በላይ አይደለም ማለቱ ይታወሳል።

BBC Amharic