በደህንነት መ/ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎችን ለብይን የሚዳርገው አሰራር ሊቀር ነው

በደህንነት መስሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎችን ለብይን የሚዳርገውን አሰራር በሚያስቀረው አዋጅ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

ከዚህ በፊት በስራ ላይ የነበረው የፀረ ሽብር ህግ አዋጅ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይጥሳል፤ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለማሰር ተጠቅሞበታል የሚል ክስ ይቀርብበታል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲሻሻል የቆየው ይህ ህግ በይዘትም ሆነ በአተገባበሩ ላይ በርካታ ችግሮች ሲስተዋሉበት እንደነበረ ነው የሚነገረው።

ይህንንም ተከትሎ 13 አባላት ያሉት የህግ አማካሪ ጉባኤ ረቂቅ አዋጁን ሲፈትሽ ቆይቷል፤በተለያዩ አካላትም ጥናትና ውይይት ተካሂዶበታል።

በዛሬው ዕለትም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶበታል።

ረቂቁ ቀድሞ በነበረው የጸረ ሽብር አዋጅ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች ተደረገውበት የተዘጋጀ ሲሆን፥ አስፈጻሚ አካላትንም ተጠያቂ የሚያደርግ ድንጋጌ የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።

ረቂቅ ህጉን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፥እየተሻሻለ የሚገኘው የፀረ ሽብር ህግ መሰረታዊ የህገ መንግስት መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ህጉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የሽብርተኝነት ስጋት መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለትርጉም ተጋላጭ እንዳይሆን መደረጉን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ፥ እንደ ወንጀሉ ባህሪና መጠን ተመጣጣኝ ቅጣት ማስቀመጡን አንስተዋል።

በረቂቅ አዋጁ በደህንነት መስሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎች ለብይን የሚዳረጉበት አሰራር እንዲቀር መደረጉም ተጠቁሟል።

ረቂቅ ህጉ የተቋማትን ሃላፊነት በግልፅ ያስቀመጠ፤ አስፈፃሚ አካላት በሽብርተኝነት የተጠረጠረ አካልን በቁጥጥር ስር ሲያውሉና ሲመረምሩ ለሚፈጽሙት ስህተት ተጠያቂ የሚሆኑበት አንቀፅን ያካተተ ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ