ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙና የሰላም ሚኒስትሯ የቅማንትን ሕዝብ እያወያዩ ነው ተባለ።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚልና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ከአማራና ከቅማንት ሕዝብ ከተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

(አብመድ) ውይይቱ በጭልጋ ወረዳ ሰራባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ከሁለቱም የማኅበረሰብ ክፍሎቻቸው የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶች ታድመዋል። የኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢፌድሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦሩ ሹም ጄኔራል አደም መሃመድን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ውይይቱ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት፣ አንድነትና ሠላማዊ ግንኑነት የበለጠ የሚያጠናክር፣ ችግሮቻቻውን በሠላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ቤተሰባዊ ምክክር እንደሆነ ተነግሯል።

የኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ” ሁለቱ ሕዝብ ቤተሰባዊ ናቸው፤ በቤተሰብ መካከል የተፈጠረ ችግር ቤተሰብ ካልፈታው በቀር ማንም ሊፈታው አይችልም። በግጭቱም ማንም አሸናፊ ሊሆን አይችልም። ያለፈው ላይመለስ ለዛሬና ለነገ ሠላማዊ ሂደት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት” ብለዋል።

ሚኒስትሯ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሠላማዊ ውይይቶች በተለየ መልኩ ወደ ሠላም መንገድ ሊያደርስ ያስችላል ተብሎ የታሰበ የመጀመሪያ ዙር ውይይት እንደሆነ አስረድተዋል። በቀጣይም መሠል ሠላማዊ ውይይቶችን ከሕዝብ ጋር እንደሚደረጉ ተጠቁሟል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የተጀመረው ሠላማዊ ውይይት እንዲያብብ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ሠላማዊ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ከሁለቱም ወገኖች የተወጣቱ ምሥጉንና ሚዛናዊ የሀገር ሽማግሌዎች የተለያዩ ሥራዎችን ሲየከናውኑ መቆየታቸውንም አስረድተዋል።

ተሳታፊዎቹም የታሠሩ ሰዎች በምሕረት አዋጁ እንዲለቀቁና የተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።