በኦሮሚያ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የፀጥታ ኃይሎችን ገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ በትላንትናው ዕለት ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው አንድ ባለስልጣን ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ።

በታጣቂዎች ከተገደሉት ውስጥ ሶስቱ ፖሊሶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። የሜታ ወልቂጤ ወረዳ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ሌንጂሳ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈጸመው በወረዳው ባለ ሚጤሮ በተባለ አካባቢ ትላንት ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ ነው። አቶ ጋዲሳ “የታጠቁ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸው ጥቃት ፈጻሚዎች በመጀመሪያ አንድ የሚሊሺያ አባልን ጭንቅላቱን በጥይት በመምታት መግደላቸውን ገልጸዋል።

የተኩስ ድምጹን የሰሙ ሌሎች ሚሊሺያዎች እና ፖሊሶች ወደ አካባቢው በደረሱበት ወቅት ታጣቂዎቹ ተጨማሪ ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን አስረድተዋል። በቅድሚያ የተገደለውን የሚሊሺያ አባል አስክሬን ለማንሳት አምቡላንስ ይዘው ወደ ስፍራው ካመሩት ውስጥ የሜታ ወልቂጤ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ኃላፊ እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

“ሚጤሮ የሚባል ልዩ ስሙ ሶምቦ ተብሎ የሚጠራ እዚያ ጋር ጠብቀው፤ አምቡላንሱን መትተው ከጣሉት በኋላ ሶስት ፖሊሶች እና አንድ ሹፌር ገድለው፤ ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ነው የቆሰሉት። ከአንድ ፖሊስ [ከያዘው] በስተቀር ስድስት ክላሽ ወስደው ነው የሄዱት። በአጠቃላይ የሞቱት አንድ የአምቡላንስ ሹፌር፣ ሶስት ፖሊስ እና አንድ ሚሊሺያ ናቸው” ብለዋል አቶ ጋዲሳ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን የታጠቁ ኃይሎች ቀደም ሲልም ይንቀሳቀሱ እንደነበር የሜታ ወልቂጤ ወረዳ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለዶይቼ ቬለው የአሶሳ ዘጋቢ ነጋሳ ደሳለኝ አረጋግጠዋል። የአካባቢው ሚሊሺያዎች ጥቃቱን የሚፈጽሙት የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ቢሉም በወረዳው አስተዳደር በኩል እስካሁን በማስረጃ ማረጋገጥ እንዳልቻሉ አብራርተዋል።

“ከዚህ በፊትም የወረዳው ጸጥታ ኃላፊ እና ሁለት ሚሊሺያዎች ሞተዋል። አሁንም ይሄ ነገር አልተቋረጠም። እንግዲህ አስቸጋሪ ነው። ይሄ ፓርቲ ነው፤ ያ ፓርቲ ነው ብሎም እኮ በማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ እንዲህ መባል አይችልም። አሁን የታጠቁ ሰዎች ናቸው እንግዲህ የሚንቀሳቀሱት” ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል። የትላንቱ ጥቃት የደረሰባት የሜታ ወልቂጤ ወረዳ የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር መቀመጫ ከሆነችው አምቦ ከተማ 152 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።