የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ትልቅ ፈተና እጁ ላይ አለ። (ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ)

የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ትልቅ ፈተና እጁ ላይ አለ። ይህን ተቋም ከመለስ ወአላሙዲ ደባ ጠብቀው እዚህ ለማድረስ የታገሉ ሁሉ ዛሬ ደስ ሊሰኙ ይገባል። ማኅበሩን ቢቻል ለማፍረስ ባይቻል ለማዳከም የሞከረው መንግሥት መሪ በፌዴሬሽኑ በዓል ላይ ለመገኘት መጠየቃቸው ለፌዴሬሽኑ መልካም አጋጣሚ ነው። ጠሚ ዐቢይ የመንግሥታቸውን የኖረ የቂምና የበቀል ጎዳና ትተው፣ በትህትና ጥያቄ ማቅረባቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፣ የፖለቲካ አጀንዳ ቢኖራቸውም እንኳን። እዚህ ድረስ ሁለቱም አካሎች ባለክብር ናቸው። ይህ የሁለቱም አካላት አመለካከትና አቋም የዛሬው የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ምንም ቢሆን ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እመኛለሁ።

ብዙዎች እንደሚያስቡት ወሳኔው ለፌዴሬሽኑ ቀላልና ግልጽ አይደለም። ቀላሉና ዘላቂው፣ በመርህና በሕግ ላይ ብቻ ተመስርቶ ውሳኔ መስጠት ነው። ሆኖም መርሖችና ሕጎች ወደፊት የሚመጡ ጥያቄዎችን በሙሉ ለማስተናገድ የማይችሉበት አጋጣሚ መኖሩ የታወቀ ስለሆነ፣ ነገሩን በልዩ ሁኔታነት ማስተናገድ ይገባ እንደሆነ መጠየቅ አግባብ ይሆናል።

ለእኔ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ቁልፍ ጥያቄ መሆን ያለበትም ይኸው ነው። ይህ ጥያቄ ባለው ሕግና አሰራር ይመለስ ወይስ በልዩ ሁኔታ ይታይ? (የፌዴሬሽኑን ሕግ በሙሉ ስለማላውቅ ብዙ ማለት አልችልም።)

በየትኛውም መንገድ ቢኬድ ግን ፌዴሬሽኑ፣ በዐቢይ (አለ)መምጣት የሚያገኘውን ትርፍ ማስላቱ ተፈጥሯዊ ነው። አሁን እንደማየው በሌሎች መንገዶች ማግኘት የሚገባንን ፖለቲካዊ መፍትሔዎች በፌዴሬሽኑ ላይ አብዝቶ መጫን ትክክል አይደለም። ይህን ስል፣ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ነገር አያገባኝም ብሎ ማለፍ አለበት ማለቴ አይደልም። ፌዴሬሽኑ እንደተቋም፣ ከዚያም አባላቱ ከጠሚ ዐቢይ ግብዣ የበለጠ ትርፍ የሚያገኙበትን ስሌት ማግኝት ወሳኙ ስራ ነው። ለምሳሌ፣ አሁን ባለበት ሁኔታ፣ ፌዴሬሽኑ ተጠያቂ እንደመሆኑ መጠን፣ ለጠሚ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ይችላል።

ጠ/ሚ ዐቢይና ቡድናቸው፣ ፌዴሬሽኑን አጣብቂኝ ውስጥ የመክተት ፍላጎት አላቸው ብዬ አላምንም። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ጥያቄያቸውን አልቀበልም ቢል፣ ውሳኔውን አድንቆ በመቀበል፣ በአሜሪካ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን በሌሎች ቦታዎች ለማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ይችላሉ።

ፌዴሬሽኑ የዐቢይን ጥያቄ ባይቀበል፣ በመርሕና በሕግ ላይ ተመሥርቶ እስከወሰነ ድረስ፣ እርቅን እንደገፋ፣ የኢትዮጵያን መሻሻል እንደማይወድ ወዘተ መታየት የለበትም። መንግሥትና ፌዴሬሽኑ ወደ እርቅ እየመጡ ከሆነ፣ ሂደቱ መጀመር ያለበት በፌዴሬሽኑ በዓል ላይ አይደለም። ከዚያ በፊት ኤምባሲው ጠይቆ ውይይት ስለመጀመሩ አላውቅም።

በተመሳሳይ መልኩ፣ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ቢቀበል ደግሞ የዐቢይን መንግሥት እንደደገፈ፣ የኢትዮጵያውያንን መከራ ችላ እንዳለ መቆጠር የለበትም። ፌዴሬሽኑ የተመሠረተው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በባለቤትነት ለማከም አይደለም። አሁን ያለውን የአገሪቱን ሁኔታ ያሻሽል ይሆናል፣ በመንግሥትና በዳያስፖራው መካከል ያለውን ቅራኔ ያረግብ ይሆናል ወዘተ ከሚል የጋራ አቋም የጠሚ ዐቢይን ጥያቄ ቢቀበለው፣ ኢትዮጵያን ለማገዝ ድጋፍ የማድረግ ሙከራ እንጂ መንግሥትን የመደገፍ አቋም ተደርጎ ባይታይበት እወዳለሁ። ተቋሞቻችን በነጻነት እንዲሰሩ እንፈልጋለን ካልን፣ አንዳንድ ጊዜ የማይጥሙንን ውሳኔዎች እንዲወስኑ መፈቀድ ይኖርብናል።

ከሁሉም ከሁሉም የምመኘው ግን፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ በኢትዮጵያዊ ወገናዊነት ስሜት ተነጋገረው፣ ውሳኔያቸውን በስምምነት እንዲያጽድቁ ነው። በጭራሽ የማይቻል ካልሆነ፣ በድምጽ ብልጫ እንዳይወስኑ እመኛለሁ። ዐቢይ አጋጣሚዎች ልዩ የመንፈስ ልዕልናና ጥንቃቄ ይሻሉ። የፌዴሬሽኑ አባል ማኅበራትም የመረጣችኋቸውን መሪዎች የጋራ ውሳኔ በመቀበል ተቋማዊነትን አበረታቱ። ፌዴሬሽኑን እንደግና የመከፋፈልና የማዳከም ፍላጎት ላላቸው መሰሪዎች በር አትክፈቱ።

መልካም ዕድል ለፌዴሬሽኑና ለአመራሮቹ።

ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ