ወንጀለኞች ማባባል ነገ የከፋ ችግር ያመጣል – ዶ/ር አብይ እንደ ቻምበርሌን አይሁኑ #ግርማካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እንደ አውሮፓዉያን አቆጣጠር ሙሱሊኒ በ1923፣ ሂትለር ደግሞ በ1933 ስልጣን ጨበጡ፡፡ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እነዚህ ሁለት ሰዎች የፈጸሙት ጥፋት ተነግሮ አያልቅም፡፡ሂትለርና ሙሶሊኒ በቀሰቀሱት ጦርነት በጀርመን በጣሊያን ብቻ ወደ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ሞቷል፡፡ ከጀርመንና ከጣሊያን ውጭ ፣ ያሉትን ስንደምሩ ቁጥር ሶስት፣ አራት እጥፍ ይደርሳል፡፡

በ 1935 ዓ.ም ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ የመንግስታት ሕብረት፣ League of Nations የሚባለው ጣሊያን ወራሪ ናት ብሎ አወገዛት፡፡ ሆኖም ግን ዉሳኔው ጥርስ አልነበረውም፡፡ እንግሊዝና ፈረንሳይ (በወቅቱ ኃይል አገራት የነበሩ) ብዙ የጥቅር ህዝብ ጉዳይ አላሳሰባቸዋውም፡፡ሙሶሊኒ ዝም ተባለ፡፡

ከአንደኛ የዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን ራይንላንድ የሚባለው አካባቢ ከዉትድርና እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆን በ1919 የቨርሳይ ስምምነት ተወስኖ ነበር፡፡ ሆኖም ሂትለር በጀርመን ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎችን ሁሉ ከጨፈለቀ በኋላ፣ በ1936 ዓ፣ም ያንን ስምምነት አፍርሶ በራይንላንድ ወታደሮችን አሰማራ፡፡ ይሄን ሲያደርግ ዝም ተባለ፡፡

በማርች 12 ቀን 1938 ሂትለር ፣ ትኩረቱን አውስትሪያ ላይ በማድረግ፣ የአዋስትሪያዉን ቻንስለር ኩርት ሹስሽኒግን አስወግዶ፣ ቪዬናን ወረረ፡፡ አውስትሪያን ወደ ጀርመን ቀላቀለ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሌሎች የአውሮፓ አገር መሪዎች ምንም አይነት እርምጃ አልወሰዱም፡፡ሂትለር ዝም ተባለ፡፡

እዚያ ላይ አላበቃም፡፡በቼኮስሎቫኪያ ጀርመኖች በብዛት ይኖሩበታል የተባሉ አካባቢዎችን፣ በአንድ ላይ ሱድተንላንድ የሚባሉትን፣ ወደ ጀርመን መቀላቀል አለባቸው በሚል ሂትለር ትኩረቱን ወደዚያ አዞረ፡፡ ቼኮስሎቫኪያዎች አገራቸውን ለመከላከል ወታደሮች ወደ ድንበሩ ማዞር ጀመሩ፡፡ በዚያ ያለውን ቀውስ ለማብረድ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስተር ኔቪል ቻምበርለን ሂትለርን እንዲያናገሩ ልኡካን በርሊን ላከ፡፡ በሴፕቴምበር 15 ቀን 1938 ዓ.ምም አሱ ቻምበርለን ራሱ ከሂትለር ጋር ተነጋገረ፡፡ ሂትለርን ለማባባል ሱደትላንድ ለጀርመን እንዲሰጥ ተስማማ፡፡ ከቀናት በኋላ የፈረንሳዩን ጠቅላይ ሚኒስተር ተከተለ፡፡

በሴፕቴምበር 29 1938 ዓ.ም ሱደትላንድ የተባለውን ሰፊ የቼኮስሎቫኪያ ግዛት ለሂትለር መሰጠቱን የሚያረጋግጥ የሙኒክ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው ስምምነት ተፈረመ፡፡ ፈራሚዎቹ ሂትለር፣ ሙሶሊኒ፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ጠ/ሚኒስትሮች ኔቪል ቻምበርሌንና እና ዳላዲዬ ነበሩ፡፡ ሂትለር ዝም መባል ብቻ አይደለም፤ እንደው ለሰራው ስራ ገጸበረከት ተበረከተለት፡፡ የቺኮስሎቫኪያ ግዛት ተሰጠው፡፡ሂተለር የፈለገውን አገኘ።

ብዙም አልቆየም በ May 1940 ሂትለር ፈረንሳይን ወረረ፡፡ ጠ/ሚኒስተር ዳላዲዬ ተወገደ፡፡ የእንግሊዝ ህዝብ አምባገነኖችናን ግፈኞችን የሚለማመጥ መሪ አንፈልግም ብለው ዊንስተን ቸርችል ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆን መረጡ፡፡ ኔቪል ቻምበርሌን ተወገዱ። በጁላይ 1940 ለንደን በጀርመን ሊፍትዋዝ (አየር ኃይል) መደብደብ ጀመረች፡፡የኔቪል ቻምበርሌን ልምምጥና ማባባል ሰላምን ለእንግሊዝ አላመጣም፡፡

ይሄን ምሳሌ ያለምክንያት አላቀረብኩም፡፡ ናዚዎች የጀርመን ዘር የበላይ ነው በሚል ዘረኝነት ተነድፈው ነው ወደ ጦርነት የገቡት፡፡ ዘረኞች ደግሞ አርቀው አያስቡም፡፡ የፈለጉትን ሙሉ ለሙሉ ካላገኙ አይረኩም፡፡ መቻቻል፣ መጋራት፣ መስማማት ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡ ካላሸነፉ፣ ካልጨፈለቁ በቀር በቃንን አያውቁም።

የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም፣ እነ ጃዋር አካሄዳቸውና አሰራራችው ከናዚዎች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ የሚፈልጉት የነርሱ ዘር ወይንም ወገን የበላይ እንዲሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ብቻ አንደኛ ዜጋ ሆነው ልዩ ጥቅም እንዲሰጣቸው ነው፡፡ በዱላ፣ በማስፈራራት ሌላው ለመጨፍለቅ ነው የሚፈልጉት፡፡ ሰዎችን በሜንጫና በገጀራ የሚገድሉት፣ መንገድ የሚዘጉት፣ ንብረት የሚያቃጥሉት በሰው አይምሮ ውስጥ ድንጋጤና ፍርሃት ለመልቀቅ፣ ከፍርሃትም የተነሳ የፈለጉትን ሌላው እሺ ብሎ እንዲቀበል ነው፡፡

ጃዋር መሐመድና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዛሬ የፈለጉትን ቢያገኙ እዚያ ላይ አያቆሙም፡፡ እነርሱን ማባባል፣ መለማመጥ በጭራሽ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ሂትለርና ሙሶሊኒን ማባባል ያኔ መፍትሄ እንዳልነበረው። የኦሮሞ ጽንፈኞችን ማባባል፣ አሁንም መፍትሄ አይሆንም። አይሰራም።

አንዳንድ ሰዎች ጃዋርን መንካት ችግር ያመጣል ይላሉ። እርሱም ዝም ማለት ነው ነገ የባና የከፋ ችግር የሚያመጣው። እነ ጃዋርን ማባባል ሳይሆን፣ በሕግ ፊት ማቅረብ ይሄን በአገራችን ላይ ያንዣበበዉን ትልቅ አደጋ አሁን መጋፈጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ኔቪል ቻምበርላን ደካማ፣ ተለማማጭ መሪ ሳይሆን፣ እንደ ዊንስተን ቨርችል ወንጀለኛንና ግፈኛን በድፍረት ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግን የ እንግሊዝ ሕዝብ ኔቪል ቻምበርላንን ቀይሮ ዊንስተን ቸርችልን ወደ ስልጣን እንዳስገባ ከግለሰቦችና ከጥቂት ቡድኖች ጥቅም ይልቅ የአገርን ዘለቂ ጥቅም ለማስክበር የሚሰራ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር ወደ ቦታው እንዲመጣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ማጠናከሩ ብቻኛ አማራጭ ነው የሚሆነው።