ጀዋር መሐመድ ላይ የጥቃት ዛቻ እና ማስፈራሪያ የፈጸሙት የፌደራል መንግሥት አካላት ናቸው – ኦነግ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር በሆነው ጀዋር መሐመድ ላይ ከትናንት በስቲያ ለሊት “የጥቃት ዛቻ እና ማስፈራሪያ” የፈጸሙት የፌደራል መንግሥት አካላት ናቸው ሲል ከሰሰ።

ግንባሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ለመጣው የፖለቲካ ለውጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱ የሕብረተሰብ ክፍሎች «ተገቢዉን መብት፣ ክብርም ሆነ እዉቅና ተነፍጓቸዋል» ብሏል።

ኦነግ መግለጫውን ያወጣው የማክሰኞ ለሊቱን ክስተት ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ከተሞች ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

ተቃውሞው ጅማ፣ ቢሾፍቱ እና አምቦ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ዛሬም ቀጥሏል። ትናንት በሐረር እና በአዳማ ከተሞች በነበሩ የተቃውሞ ሰልፎች አምስት ሰዎች መገደላቸውን ዶይቼ ቬለ (DW) ከባለሥልጣናት እና የዐይን እማኞች አረጋግጧል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «የጀዋር መሐመድን ጠባቂዎች ለማንሳት የተፈጸመው ተግባር በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው፤ ድርጊቱ በመንግሥት የማይታወቅ ነው» ብለዋል።

ኦነግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ «ሕዝባችን የብዙ ሺህዎች ዉድ ልጆቹን ህይወት፣ ደምና አጥንት ገብሮ ያስገኘዉ ለዉጥ በአግባቡ እየተስተናገደ አይደለም» ሲል ከሷል።

«እንደ ግለሰብም ሆነ በቡድን ወይም በድርጅት ታግለው በከፈሉት መስዋዕትነት ይህንን ዛሬ የምናየዉን ለዉጥ እንዲመጣ ያስቻሉት የሕብረተሰቡ ክፍሎች ተገቢዉን መብት፣ ክብርም ሆነ እዉቅና ተነፍጎ ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ» ሆነዋል ብሏል ኦነግ።

ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ምኒስትር ከሆኑ በኋላ «በሕዝባችን ላይ የሚደርስ እሮሮ በይበልጥ እየከፋ፣ ፍትሃዊ ጥያቄዉ እና ድምጹም ከምንጊዜዉም በላይ እየተናቀ እና ወደጎን እየተተወ መጥቷል» ሲል ኦነግ በመግለጫው አትቷል።

«ሕዝባችን የዘመናት ትግሉን ውጤት በዜሮ አባዝቶ፣ ትግሉንም ወደኋላ ለመመለስ የሚኬደዉን ይህንን አስጸያፊ ሁኔታ እና አካሄድ በምንም ተዓምር ዕድል» አይሰጥም ሲልም አስጠንቅቋል።

ኦነግ «ይህ ሁኔታ በጊዜ ካልታረመና ከቀጠለ እስካሁን ካደረሰዉ ጉዳት እና የሰላም መደፍረስ ይልቅ የወደፊት አቅጣጫዉ እና የሰነቀዉ ጥፋት የሚያሰጋ ሆኖ ይታየናል» ሲል የሁኔታውን አሳሳቢነት ጠቁሟል።

dw amharic