እኛ ኢህአዴጎች ለ30 ዓመታት አንድ መሆን ተስኖን እንዴት ነው ሀገርን አንድ ማድረግ የምንችለው? – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፓርቲ የውሕደት ጉዳይ አለማለቁንና አይቀሬ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናገሩ፡፡ውሕደቱን በተመለከተ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የተካሄደ ጥናት መኖሩን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) በአንዳንድ ድርጅቶች የሚወራው የተሳሳተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹እኛ ኢህአዴጎች ለ30 ዓመታት አንድ መሆን ተስኖን እንዴት ነው ሀገርን አንድ ማድረግ የምንችለው?›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመርን መጨፍለቅ አስመስለው የሚያወሩ ውስኪ ጠጭ ኢህአዴጎች የተሻለ የማባዛት ሐሳብ ይዘው በመውጣት መደመርን እንዲገዳደሩም መክረዋል፡፡

በውጭ ሀገራት በ10 ሰው ስም ሆቴል የገነቡና ሆቴል የቅንጦት ኑሮ የሚኖሩ ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም መነገዳቸውን እንዲያቆሙ የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢህአዴግ በምን ስምና በምን ግብር ይዋሐዳል የሚለውን እኔ አልወስንም፤ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡

ለእያንዳንዱ ዜጋ እኩል የሆነች ኢትዮጵያን የሚገነባ ኢህአዴግ እንደሚፈጠር ያመለከቱት ዶክተር ዐብይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ጫፎች ያሉ ዜጎች እኩል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑበት ሥርዓት እንደሚገነባ አስታውቀዋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ እንዲሁ የሚቀለድበት ሳይሆን ትክክለኛ ሐሳብ የሚያሸንፍበት መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መልዕክት ያስተላፉት ‹መደመር› በሙል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ በሚሊኒየም አዳራሽ በተመረቀበት ወቅት ነው፡፡ መጽሐፉ በ20 የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችና በውጭ ሀገራት ተመርቋል፡፡ መጽሐፉ አዲስ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይዞ መምጣቱ በሀያስያን ተብራርቷል፡፡

(አብመድ)