የቅማንት የማንነት ጥያቄ ከውልደት አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ ጉዞው ምን ይመስላል? –

BBC Amharic : የቅማንት የማንነት ጥያቄ በተነሳባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ከመኖሪያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ ቆይተዋል። ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ምክንያት ምንድን ነው?

የቅማንት የማንንት ጥያቄስ በምን መልኩ ተጠይቆ ምን አይነት ምላሽ ተሰጠው? የቅማንት የማንነት ጥያቄ ከውልደት አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ ጉዞው ምን ይመስላል? የተከታዩ ጥንቅር ይህንን ይዳስሳል።

ድህረ –ቅማንት የማንነትና አስተዳደር ጥያቄ

የቅማንት ህዝብ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሃገር፤ በአሁኑ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች የሚኖር ህዝብ ነው። በተለይ በጎንደር ከተማ ዙሪያ በሚገኙ ላይ አርማጭሆ፣ ወገራና ጭልጋ ወረዳዎች ማህበረሰቡ በብዛት የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው።

ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው የመንግሥት አወቃቀርም የብሄር ማንነትን መሰረት ያደረገ ስላልነበር ብሔረሰቡ የጎንደር ክፍለ ሃገር አካል ሆኖ ከአማራው ህዝብ ጋር በብዛት ተቀላቅሎ ይኖር ነበር። የራሱ የተካለለ ልዩ አካባቢና አስተዳደርም እንዳልነበረውም መረጃዎች ያሳያሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ መነሻ?

ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በኢትዮጵያ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የብሔር ፌደራሊዝምን መሰረት ያደረገና ስልጣን በፌደራልና በክልሎች የተከፋፈለ ስርአትን መሰረተች።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ ይህ ስርአት ከሰፈነ በኋላ በ1984 ዓ.ም መነሳቱን በቅማንት ማንነት ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት አቶ ቹቹ አለባቸው ያስረዳሉ።

“የቅማንት ብሔረሰብ ጥያቄ ከየት ወደየት-ከማንነት ጥያቄ እስከ የራስ አስተዳደር ጥያቄና የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ” በሚለው ፅሁፋቸው ጥያቄው በቅማንት ህዝብም ተቀባይነት ያልነበረው ሲሆን ለግለሰቦቹ የተሰጣቸውም ምላሽ “የያዛችሁት ሐሳብ ከአማራ ወንድሞቻችን ጋር የሚያጋጭ ሐሳብ ነው፣ ስለሆነም አንቀበላችሁም” የሚል እንደነበረ ጥናቱ ያሳያል።

በህዝቡ ተቀባይነት ካጣ በኋላም ጥያቄው ለአስራ አምስት አመታት ያህል ተዳፍኖ ሳይነሳ መቆየቱን ይኸው ጥናት ያመላክታል። የ1999 ዓ.ም የሕዝብና ቤት ቆጠራ ግን አዲስ ክስተት ይዞ መጣ።

የማንነት ጥያቄ ባይነሳም በ1984 ዓ.ም በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ የቅማንት ሕዝብ በራሱ ተለይቶ ‘ቅማንት’ በሚል መለያ ኮድ እንደተቆጠረ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪ አቶ መርሃጽድቅ መኮንን ይናገራሉ።

ነገር ግን ለብቻው ተለይቶ መቆጠሩ አልቀጠለም በቀጣዩ 1999 በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ ግን ኮዱ ተሰርዞ ‘አማራ ወይም ሌላ’ በሚል የቅማንት ሕዝብ እንዲቆጠር መደረጉን ያስረዳሉ።

ይህ ሁኔታ ቅሬታን እንደፈጠረና ጥያቄዎችም መቅረብ መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ መርሃ ጽድቅ በተለይም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ማመልከቻ ይዘው ወደ ክልሉ መንግሥት መምጣት መጀመራቸውን ያስረዳሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይርሳው ቸኮልም በአቶ መርሃ ጽድቅ ሃሳብ ይስማማሉ። “ቅማንት ሆነን ሳለ ለምን ‘ሌላ’ ተባልን በሚል ተሰባስበን ጥያቄውን ጀመርን”ይላሉ።

የቅማንትን ህዝብ አምስት በመቶ ድምጽ፣ 18500 ድምጽ ሰብስበው ማንነታቸው እንዲታወቅ ለክልሉ መንግሥት ጥያቄያቸውንም ማቅረባቸውን አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ በተደራጀ መልኩ የቀረበው በዚህ ወቅት ነው።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ማንነት ጥያቄ ምላሽ

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ማንነት ጥያቄንም ለመመለስ የክልሉ የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ጥናት እንዲጠና አድርጓል። የአቶ ቹቹ ጽሁፍ እንደሚያሚያመለክተው በክልሉ መንግሥት አነሳሽነት በተቋቋሙ ኮሚቴዎች አማካኝነት ሁለት ጥናቶች በ2003 እና 2004 ዓ.ም ተሠርተዋል።

ጥናቱም ሞዴል አድርጎ የወሰደው የአርጎባ ልዩ ወረዳ የማንነት ጥያቄ የተመለሰበትን መንገድ እንደነበር አቶ መርሃ ጽድቅ ያወሳሉ። የአርጎባ ጥያቄ በ1998 ዓ.ም ልዩ ወረዳ መሆን ይችላሉ በሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የተጠናው ጥናትም በ2005 ዓ.ም ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡንም የሚናገሩት አቶ መርሃ ጽድቅ ይህ እንግዲህ በሰነድ ደረጃ የአማራ ክልል ምክር ቤት የቅማንት የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ ውይይት ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

በህገ መንግሥቱ መሰረት የማንነትና የራስ አስተዳደርን ጥያቄ ለመመለስ አምስት መስፈርቶች አሉ እነዚህም የጋራ ባህል መኖር፤ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ መኖር፤ አካባቢው ኩታ ገጠም መሆን፤ በስነ ልቦናና ማንነት ለጠየቀው ብሔረሰብ አባል ነኝ ብሎ ማመንና የተዛመደ ህልውና መኖር ሲሆን ፤የአርጎባ ጥያቄም ይህንን በሟሟላቱ እንደሆነም አቶ መርሃ ጽድቅ ያስረዳሉ።

ጥናቱንም መሰረት በማድረግ “ማህበረሰቡ እንደ ማህበረስብ መኖሩ ተረጋግጦ እውቅና ቢሰጠውም የራሱን የውስጥ አስተዳደርና ነጻነት ለመመስረት ግን ህገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን አያሟላም” ተብሎ አደረጃጀቱ በክልሉ ምክር ቤት ውድቅ መደረጉን ይናገራሉ።

የማንነት ጥያቄው እንዲመለስ ሞዴል ከተደረገው የአርጎባ ልዩ ወረዳ ጋር ተቀራራቢነት የሌለው፤ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የሌለው በመሆኑና ኩታ ገጠም አሰፋፈር ስላልነበረው ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል ህገ መንግሥታዊ አካሄድ እንዳልነበር አቶ መርሃጽድቅ ያስረዳሉ።

በምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ይህ ውሳኔም 174 የምክር ቤት አባላት የብሔረሰብ አስተዳደሩን መቋቋም ሲቃወሙ፣ ሰባት ደግፈውና 21 የምክር ቤቱ አባላት በድምፀ ተአቅቦ ነው ውድቅ የተደረገው ይላሉ።

“‘ይህ አካባቢ ያንተ ነው ራስህን አስተዳድር ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። የራስ አሰተዳደሩን ለመወሰን የሚያስችል ህገ መንግሥታዊ መስፈርቶች አልተሟሉም በማለት የራስ አስተዳደር ጥያቄው በክልሉ ምክር ቤት ውድቅ ተደርጓል” ይላሉ አቶ መርሃጽድቅ።

ከአማርኛ ጋር እየተቀላቀለና በተወሰኑ አዛውንቶች ብቻ የሚነገረውን የቅማንት ቋንቋ እንዳይጠፋ የማበልፀግም ጥረት እንደተደረገም አቶ መርሃጽድቅ ያስረዳሉ።

አቶ ይርሳው በበኩላቸው ህገ መንግሥቱ የሚጠይቀውን መስፈርት ማሟላታቸውን ይገልፃሉ።

መግባቢያቸው አማርኛ ቋንቋ ቢሆንም የቅማንትኛ ቋንቋ ያልሞተ መሆኑን፤ ወጥ የሆነ የሕዝብ አሰፋፈር ፤ በስነ ልቦና ቅማንት ነኝ ብሎ የሚያምን ህዝብ መኖሩንና ከአማራው ጋር የተቀላቀለ ቢሆንም የራሳቸው ባህል እንዳላቸውም ይገልጻሉ።

በዚህም መሰረት ውሳኔው የማንነት ጥያቄ ያነሱትን የኮሚቴ አባላት ያስደሰተ አልነበረም። ውሳኔውን ባለመቀበልም ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ጉዳዩን የክልሉ መንግሥት ድጋሜ እንዲያየው መልሶ የላከው ሲሆን ከሁለት አመታት በኋላ ግን በ2007 ዓ.ም የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር መፈቀዱን አቶ ይርሳው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እንዴት ተመለሰ?

ክልሉ በ2005 ባደረገው ጥናት የቅማንት ማህበረሰብ የማንነትና የራሱን አስተዳደር ለመመስረት ህገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን ካላሟላ ከሁለት አመት በኋላ ጥያቄው እንዴት ተቀባይነት አገኘ?

በምን መስፈርት የራስ አስተዳደሩ ተመለሰ ለአቶ መርሃጽድቅ የቀረበ ጥያቄ ነው።

እንደ አቶ መርሃጽድቅ ከሆነ በተለይ በአካባቢው ግጭቶች እየተበራከቱና ተቋማት እየተዘጉ በመምጣታቸው፤ በ2007 ዓ.ም የክልሉ የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት “ጉዳዩ እንደገና ይታይልኝ” በማለቱ ጥናቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን ይገልፃሉ።

ምክር ቤቱ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ለማየት እንደተገደደ የሚያስረዱት አቶ መርሃጽድቅ “ይህም ፖለቲካዊ ጫና ነበረበት” ይላሉ።

አቶ መርሃጽድቅ ፖለቲካዊ ጫና የሚሉትም የ2005 ዓ.ም የምክር ቤት ውሳኔ በቅማንት ማንነት ኮሚቴ ቁጣን ከመቀስቀሱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ውሳኔው በኮሚቴው ዘንድ ቁጣን ስለቀሰቀሰ እና የሰው ህይወትም እየጠፋ ሲመጣ ፖለቲከኞቹ (በተለይ በፌደራል ደረጃ የነበሩ የብአዴን ካድሬዎች ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው) እጃቸውን አስረዝመው ቅማንት ይኖርባቸዋል የሚባሉትን አካባቢዎች አገናኝታችሁ ወስኑላቸው ፤ ህዝባችን እስከሆኑ ድረስ የትም አይሄዱም” የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠ አቶ መርሃጽድቅ ይናገራሉ።

በዚሁ መሰረትም ከላይ አርማጭሆ ወረዳ 25 እና ከጭልጋ ወረዳ 17 በድምሩ 42 ቀበሌዎችን በቅማንት የራስ አስተዳደር፤ በልዩ ወረዳ እንዲዋቀሩ ተወስኗል። ይህም ከህገ መንግሥቱ መስፈርት ውጭ ብዙ ርቀት ተሂዶ የተወሰነ መሆኑን አቶ መርሃጽድቅ ይናገራሉ። ነገር ግን ውሳኔው ግጭቱን አላስቆመውም።

የቅማንት የማንነት ጥያቄና አስተዳደር ቅሬታ

ክልሉ የቅማንትን አስተዳደር አርባሁለት ቀበሌዎች በልዩ ወረዳ እንዲዋቀር መወሰኑ በማንነት ኮሚቴው ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

ህዝቡን ባላሳተፈ መልኩ፤ 42 ቀበሌዎችን ሰጥቻችኋለሁ ነው የተባልነው” ይላሉ።

አርባ ሁለት ቀበሌዎች ለቅማንት የራስ አስተዳደር መወሰኑንም በመቃወምና በቂ አይደለም በሚልም በጭልጋ በ2007ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።

“እነዚህ 42 ቀበሌዎች በውይይትና በፖለቲካዊ ውሳኔ የተካለሉ እንጅ ህዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው አልነበሩም።” ብለውም አቶ ይርሳው ያምናሉ።

የአቶ ቹቹ ፅሁፍም እንደሚያስረዳው በወቅቱ በቅማንት ወረዳዎች የመንግስት ሥራ ቆሞ ስለነበር፤ ሥራ ለማስጀመር፤ እንዲሁም ውሳኔውን ለማስፈጸም፤ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሮቢት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት፤ ማውራት ከተባለ አካባቢ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ከህዝብ ጋር ግጭት ተደርጎ የሰው ህይወት ማለፉን ነው። ግጭቱም በህዳር 2008 ዓ.ም በሽንፋ አካባቢ ቀጠለ ።

ውሳኔውንም ባለመቀበል የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎቹ በድጋሜ ቅሬታቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡ መልሱ ተመሳሳይ ነበር። ‘የክልሉ መንግሥት በጀመረ ይጨርሰው’ የሚል እንደሆነ አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

ለሦስት አመታት ጉዳዩ በውዝግብ ከቀጠለ በኋላ 2010 ዓ.ም ላይ ጥያቄው እንዴት መፈታት አለበት በሚል ከክልሉ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት ከቅማንት የማንነት ጥያቄና ከአማራ ክልል መንግሥት የተውጣጣ ጥምር ኮሚቴ ተዘጋጅቶ ጥናት ካካሄደ በኋላ ተጨማሪ 21 ቀበሌዎች ወደ ቅማንት ይካለሉ ተብለው ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር መካለላቸውንም ይናገራሉ።

በተመሳሳይም እነዚህ ቀበሌዎች ሲካለሉ ህዝበ ውሳኔ አለመካሄዱንና እንዲሁ “በውይይትና በፖለቲካ ውሳኔ” የተካለሉ መሆናቸውንም አቶ መርሃጽድቅ እንዲሁም አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

ቀበሌዎቹን ወደ ቅማንት ራስ አስተዳደር የማካለል ውሳኔ

ጥምር ኮሚቴው በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር በመዘዋወር የተለያዩ ቀበሌ ነዋሪዎችን አወያይቷል። ከቀደሙት ውሳኔዎችም በተለየ መልኩ በ2010 ዓ.ም 12 ቀበሌዎች በህዝበ ውሳኔ እንወስናለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም አቶ ይርሳው ይናገረራሉ።

ምንም እንኳን ቀበሌዎቹ የራሳቸውን አስተዳደር በራሳቸው ድምፅ ለመወሰን ቢያስቡም አራት የጭልጋ ቀበሌዎች ላይ ሁከት በመፈጠሩ ምርጫ ሳይካሄድ መቅረቱን አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

ከአስራ ሁለቱ በበስምንቱ ቀበሌዎች ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ሰባቱ ወደ ነባሩ አስተዳደር እንዲካለሉ ሲወስኑ አንዷ ቀበሌ ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር ለመካለል መወሰኗን ይናገራሉ።

በቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሂደት ይህች አንዲት ቀበሌ የራስ አስተዳደሩን በሕዝበ ውሳኔ የተቀላቀለች ብቸኛዋ ቀበሌ ነች።

በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ህዝበ ውሳኔ ያልተካሄደባቸው አራቱ ቀበሌዎች በጥምር ኮሚቴው አማካኝነት ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ሁለት ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር ሁለቱ ደግሞ ወደ ነባሩ አስተዳደር እንዲካለሉ መደረጋቸውን አቶ ይርሳው ይገልጻሉ።

በዚህ ሁኔታ በውይይት፤ በፖለቲካዊ ውሳኔና በህዝበ ውሳኔ የተካተቱት የቅማንት የራስ አስተዳደር ቀበሌዎች ቁጥር ከ60 በላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ይርሳው ቀጣዩ ሥራ የራስ አስተዳደሩን መመስረት ነበር።

የቅማንት የራስ አስተዳደርና የሶስት ቀበሌዎች ጥያቄ

ቀበሌዎቹ ከተካለሉ በኋላ የራስ አስተዳደሩን ለመመስረት የሚያስችል መነሻ መዋቅር (proposal) ኮሚቴው እንዲያዘጋጅ በክልሉ መንግሥት በተጠየቁት መሰረት ሌሎች ሦስት የመተማ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ቅማንት ናቸው በሚል እሳቤ ሶስቱን ቀበሌች በማካተት 72 ቀበሌዎች፤ በስድስት ወረዳ ለማድረግ ወስነው ለክልሉ መንግሥት ፕሮፖዛል እንዳቀረቡ አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

የኮሚቴውን ፕሮፖዛል በ2010ዓ.ም የተመለከተው የክልሉ ምክር ቤት “በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ የማንነት ጥያቄው በ69 ቀበሌዎች እንዲዋቀርና ከልዩ ወረዳነት ወደ ብሔረሰብ አስተዳደር እንዲያድግ መወሰኑን” አቶ መርሃጽድቅ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ኮሚቴው ጥያቄያቸው ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንዳላገኘና በቅማንት አስተዳደር ስር መካተት የሚገባቸው፣ 3 ቀበሌዎች (መቃ፤ጉባኤ ጀጀቢት፤እና ሌንጫ) በቅማንት ራስ አስተዳደር ስላልተካተቱ ቀበሌዎቹ በቅማንት ራስ አስተዳደር ካልተካለሉ ውሳኔውን እንደማይቀበለው ይፋ ማድረጉን የአቶ ቹቹ ጽሑፍ ያስረዳል።

አቶ ይርሳውም በበኩላቸው በአቶ ቹቹ ፅሁፍ ይስማማሉ “አራቱን ወረዳ ብንቀበለውም ሶስቱ ቀበሌዎች ወደ እኛ መካተት አለባቸው ብለን ስላሰብን በህግ ሊፈቱ ይገባል ብለን ቅሬታችንን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ላክን” ይላሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ምላሽ

ቅሬታው የደረሰው የፌደሬሽን ምክር ቤትም ጥናት አድርጎ ምላሽ እንደሰጠ የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ወርቁ አዳሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ሦስት ባለሞያዎች ከፌደሬሽን ምክር ቤት ወደ ስፍራው ተልከው፤ የተነሳውን ቅሬታ በአካል ቦታው ድረስ በመጓዝ ጥናት ማካሄዳቸውን ያስረዳሉ።

“ህገ መንግሥቱ ጋር ስለማይጣጣምና ቅሬታ የቀረበባቸው ቀበሌዎች ኩታ ገጠም ስላልሆኑ፤ የክልሉ መንግሥት የሰጠው ውሳኔ ትክክል ነው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ይናገራሉ።

እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት አሰራር ደግሞ እንደዚህ አይነት ቅሬታዎች ሲፈጠሩ በተለይ ቀበሌን ከቀበሌ፤ ወረዳን ከወረዳና ዞንን ከዞን ማዋቀር ያለበትና ውሳኔ መስጠት ያለበት ቅሬታ የተነሳበት ክልል ራሱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ወርቁ፤ “ቅሬታው አስተዳደራዊ ጉዳይ በመሆኑ መመለስ ያለበት አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ነው” ይላሉ።

አክለውም “ዋናው ነገር ማንነትን እውቅና መስጠት ነው፤ ይህም ምላሽ አግኝቷል” ያሉት አቶ ወርቁ በክልሉ ውስጥ የሚፈጠርን የአስተዳደር ወሰን በተመለከተ ጉዳዩ ግን አስተዳደራዊ በመሆኑ ክልሉ ራሱ እንዲፈታ ነው ህጉ የሚያዘው” ብለዋል።

ኮሚቴው ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን አለመቀበሉን የሚገልፁት አቶ ይርሳው ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት “ጥናቱን ለማከናውን የተላኩት ሰዎች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ስላልነበሩ ገና ከመመለሳቸው በፊት ምን ይዘው እንደሚመለሱ ስለምናውቅ እነዚህ ሰዎች ይዘውት የሚመለሱትን ውጤት ምንም ይሁን ምንም አንቀበልም ብለን ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ጽፈናል” ይላሉ።

ኮሜቴው ጥናቱን ለማከናወን የተላኩት ግለሰቦች ገለልተኛ አይደሉም የሚል ጥያቄ ቢያነሱም አቶ ወርቁ በበኩላቸው “የሚዛናዊነት ጥርጣሬ ካለ ብሔር ብሔረሰብ ቢሆን የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ካልሆነ ግን መታየት ያለባቸው ሰዎቹ ሳይሆኑ ይዘውት የሚመጡት መረጃ ነው፤ ከዚህም አንጻር የመጣው መረጃ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ነው” ይላሉ።

የማንነት ጥያቄና መፍትሔ ያላገኘው የቅማንት ራስ አስተዳደር ጥያቄ

የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ በዋናነት ልማትን ለማፋጠን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ይርሳው “ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር እኩል ተጠቃሚነት፣ ባህልንና እሴትን ለማሳደግ እንዲሁም የራስን አካባቢ ህዝቡ ራሱ በሚመርጣቸው ሰዎች እንዲተዳደርና በዚህም ከፍተኛ የልማት ጉዳይ ለማምጣት ነው።”ይላሉ

የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄና የክልሉ ውዝግቡ መፍትሔ ሳያገኝ በዚህ ከቀጠለ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት፤ ኮሚቴውንና የክልሉን መንግሥት ተወካዮች ባካተተ መልኩ ውይይት ተደርጎ ጉዳዩ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

እንደ አቶ ይርሳው ገለጻ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ምክረ ሃሳብ በኋላ ኮሚቴው ነሐሴ 2010 ዓ.ም ጎንደር ለስብሰባ ተቀምጧል።

“ስብሰባ ላይ እያለን በክልሉ የፀጥታ ኃይል የእገታ ሙከራ ተካሂዶብናል፤ ከዚያም በኋላ ከክልሉ መንግስት ጋር ያለን ግንኙነት ተቋረጠ” ይላሉ።

ውዝግቡ እንዳይቋጭ ምክንያቱ ይህ መሆኑንም ይገልጻሉ።

አቶ መርሃ ጽድቅ በዚህ አይስማሙም፤ እሳቸው እንደሚሉት በተለይ የጸጥታው መደፍረስና የነገሮች መበላሽት የጀመሩት ክልሉ በ2005 ባጠናው መሰረት የመጀመሪያውና ትክክለኛው ውሳኔ በመቀልበሱ እንደሆነ አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ።

“ክልሉ ሰለባ ሆኗል፤ በተለይ ከ2005 ዓ.ም ውሳኔ በኋላ ክልሉ ከሚገባው በላይ ባልተገባ መንገድ hijack ተደርጓል(ተጠልፏል)። በማንም አይደለም ሃይጃክ የተደረገው። በራሱ ሰዎች ነው፤ በተለይ በፌደራል ደረጃ ላይ በነበሩት ትልልቅ የብአዴን ሰዎች የክልሉን ምክር ቤት ወደ እዚህ ችግር አስገብተውት አካባቢው እንዳይረጋጋ ተደርጓል” የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።

ግጭትና መፈናቀል በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር

በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች እየተነሱ የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም በስፋት ተስተውሏል።

በተለይ ባለፈው ዓመት የተነሳው ግጭት የክልሉን አጠቃላይ ተፈናቃይ ወደ 90 ሺህ ያሳደገና በግጭቱም ቢያንስ 560 ቤቶች መቃጠላቸውን በወቅቱ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

ለተወሰኑ ወራት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ቢቆይም ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት ደግሞ ሰዎች ተገድለዋል፤ ንብረት ወድሟል። ንጹሃን ዜጎችን ከተሽከርካሪ አስወርደው ማንነታቸውን መሰረት በማድረግ ቢያንስ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉና ይህም “በጽንፈኛው ኮሚቴ” የሚመራና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያለው መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

ለዚህ ክሥ ምላሽ የሰጡት አቶ ይርሳው “እኛ የማንም ተላላኪ አይደለንም፤ እንደዚያም ሆነን ከሆነ የክልሉ መንግሥት ምን ይሰራ ነበር?” በማለት ይጠይቃሉ።

ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ግጭት በተመለከተ ደግሞ “የቅማንት ህዝብ የትም አልሄደም፤ ሲመጡበት ግን ራሱን ተከላክሏል” ያሉት አቶ ይርሳው “መኪና ላይ ሰዎችን አስወርዶ በማንነታቸው ምክንያት መግደል ነውር ነው፤ ማን እንደፈጸመው ግን መረጃ የለኝም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አሁን የክልሉ መንግሥትና ኮሚቴው አንዱ ሌላውን በመክሰስ ላይ ይገኛሉ። በአካባቢው ግጭቶች እየተፈጠሩ በየጊዜው የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም የቀጠናው መገለጫ እንደሆነ ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

መፍትሄው ምን ይሆን?

አቶ መርሃጽድቅ ለጉዳዩ ሁለት የመፍትሔ ሃሳቦች መኖራቸውን ይገልጻሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ “የራስ አስተዳደሩ ህገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን ሳያሟላ የተወሰነ በመሆኑ ህጋዊ መሰረት የለውም በማለት ውሳኔውን ውድቅ ማድረግ ይቻላል” የሚለው አንደኛው አማራጭ ነው፤ ነገር ግን ይህ አማራጭ ተግባራዊ ቢደረግ “ሰላም ሊሰፍን ይችላል ወይ?” የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ይገልጻሉ።

“ህዝቡ በዚህ ደረጃ ከተነሳሳ በኋላ፤ ብዙ ተስፋዎችን ካሳየኸው በኋላ የራስ አስተዳደርህን አጥፌብሃለሁ ቢባል ውጤቱ መረጋጋትን የሚያሰፍን አይሆንም” ባይ ናቸው።

ሌላኛው ደግሞ እንደ አማራጭ የሚያቀርቡት የተፈቀደውን የራስ አስተዳደር መመስረትና ይህንን ህጋዊ አካሄድ በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ደግሞ ህጋዊ ርምጃ መውሰድ እንደሆነ አቶ መርሃጽድቅ ይናገራሉ።

“ሂደቱ የራሱ ችግር እንዳለበት ሆኖ 69 ቀበሌዎችን ያቀፈው የራስ አስተዳደር ይደራጃል” ያሉት አቶ መርሃጽድቅ ይካተቱልኝ የሚባሉት ሦስት ቀበሌዎች አስፈላጊ ከሆነ ባሉበት በልዩ ቀበሌ ሊደራጁ ይችላሉ ብለዋል።

አቶ ይርሳው በበኩላቸው ሁለት የመፍትሄ አማራጮችን ያቀርባሉ። አንደኛው የብሔረሰብ አስተዳደሩ እንዲቋቋምና ነገር ግን ባለፈው የፌዴሬሽን ሰዎች የሰጡት ውሳኔ ተሽሮ ሌላ አካል በተለይ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ አካል የሶስቱን ቀበሌዎች ጉዳይ እንዲያጠና ጠይቀዋል።

ሁለተኛው ደግሞ “ብሔረሰብ አስተዳደሩ ሲመሰረት ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አያስፈልገንም ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ከኮሚቴው ጋር የነበሩ ነገር ግን አሁን አብረውን ያልሆኑ ሰዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ ስለሆነ ነው” ይላሉ።