“የሰለጠነና በሙሉ አቅም የሚዋጋ ኃይል ነው ችግሩን የሚፈጥረው” – የማዕከላዊ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ

BBC – ከእሁድ ዕለት መስከረም 18፣2012 ጀምሮ በጎንደር አካባቢ፣ አዘዞና ማራኪ [ቀበሌ 18] አካባቢ፣ በነበረው አለመረጋጋት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ አካባቢ በተከሰተ ግጭት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን አስከሬን ወደ ጎንደር በሚመጣበት ወቅት፣ ወጣቶች በሁኔታው ተቆጥተው በከተማዋ አንጻራዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጎንደር ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘነበ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከእሁድ ጀምሮ ወጣቱ በአዘዞና ቀበሌ 18 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙ የቅማንት ተወላጆች ላይ ጉዳት የማድረስና ቤታቸውን የማቃጠል እርምጃዎች ተፈፅሟል ይላሉ።

ይህም የሆነው ጭልጋ የሞቱ ሰዎች አስከሬን ጎንደር ሲገባ “በግጭቱ ተሳትፎ በሌላቸው የቅማንት ተወላጆች ላይ ወጣቱ የበቀል እርምጃ በመውሰዱ ነው” በማለት ይከስሳሉ።

ሌላኛው ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው የጎንደር ከተማ ነዋሪ ደግሞ “ወጣቱ በጭልጋ የተገደሉትን ተከትሎ በከተማዋ የሚኖሩ ነገር ግን ይህ ችግር እንዲፈጠር አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሰዎች ይያዙልን በማለት ወደ ቤታቸው ሲያመራ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ተኩስ ከፍተዋል” ይላል።

በዚህም ምክንያት አንድ የልዩ ሃይል አባል እና አንድ ሰላማዊ ግለሰብ ግርግሩን በማረጋጋት ላይ እያሉ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን ይናገራል።

“ሰዎቹም ሙሉቀን ሲተኩሱ ውለዋል፤ በቂ ትጥቅ የነበራቸውና በኋላም ቤታቸው ሲፈተሽ የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎች ተገኝተውባቸዋል” በማለት በቅማንት ተወላጆች ላይ “አንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አልደረሰም” ይላሉ።

አቶ ዘነበ እንደሚሉት ግን በተነሳው ግርግር ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል፤ ንብረት ተዘርፏል፤ ቤቶችም ተቃጥለዋል፤ ይህ ጥቃትም “አንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ ነው” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ “የመንግሥት እጅ አለበት” ባይ ናቸው።

ከጎንደር ከተማ ትንሽ ወጣ ብላ በምትገኘው ቁስቋም አካባቢ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሆነው የተኩሱም ድምፁም ጎንደር ስለሚሰማ ሽብር ለመፍጠር እንጂ የተደራጀ ጥቃት አልተሰነዘረም የሚሉት ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ግለሰብ አሁንም በተለያዩ የጎንደር ከተማና ዙሪያዋ አልፎ አልፎ በየግቢያቸው ሆነው የሚተኩሱ አሉ፤ በተወሰነ መልኩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፣ የትራንስፖርት አገልግሎትም በአንጻሩ ቀንሷል በማለት የዛሬውን የጎንደር ውሎ ይናገራሉ።

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ አሁን ላይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸው በአጠቃላይ በከተማዋ ውስጥ የተቃጠለ ቤት አለመኖሩንና አልፎ አልፎ ግን መስኮታቸው የተሰባበሩ ቤቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር እንየው በአካባቢው (በማዕከላዊ ዞን) አሁን አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን ገልጸዋል።

“በሎጂስቲክስም በአካልም ድጋፍ የሚደረግለት ‘ጽንፈኛው ኮሚቴ’ ግድያዎችን በመፈጸም ግጭቶችን ወደ ጎንደር ከተማ የማስገባት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል” ብለዋል።

ይህንንም ለመከላከል ከተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸው “በተደራጀ፤ በሰለጠነ እና በሙሉ አቅም የሚዋጋ ኃይል ነው ችግሩን የሚፈጥረው” በማለት በህዝብ ላይ ትንኮሳ በመፍጠር ችግሩን በህዝቦች መካከል ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

“የውክልና ጦርነት አለ የምንለው ዝም ብለን አይደለም” የሚሉት ኮማንደሩ ሌሎች ያሰማሯቸው ኃይሎች ናቸው ያሏቸውን በቀጣዮቹ ጊዜያት “አንድ ሁለት ተብለው በሚቆጠሩ ማስረጃዎች ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።