ኢሕአዴግ ስሙን ከመቀየሩ በፊት ከስሕተቱ ይማር !!!

ከስም ለውጥ በፊት ስር ነቀል የመዋቅርና የፖሊሲ ለውጥ ሊጀመር ይገባል። ( ምንሊክ ሳልሳዊ)

ኢሕአዴግ ስሙን ከመቀየሩ በፊት ከስሕተቱ ይማር !!!

ከስም ለውጥ በፊት ስር ነቀል የመዋቅርና የፖሊሲ ለውጥ ሊጀመር ይገባል።ካሁን ቀደም እንዳልነው ኮማ ውስጥ ያለው አሮጌው ኢሕአዴግ ተቀብሮ አዲስ ኢሕአዴግ መወለድ አለበት። በየክልሉ የምናያቸው ችግሮች አባታቸው ኢሕአዴግ ነው ፤ ከየቦታው እየፈለቁ በሕዝብ መሓል ግጭት የሚፈጥሩት አባታቸው ኢሕአዴግ ነው ፣ በየሚዲያው የፖለቲካ ተላላፊ ወረርሽኝ የሚያሰራጩት አባታቸው ኢሕአዴግ ነው ፣ ሐገራችንን ለእርስ በርስ ጦርነት ለሃይማኖትና ለጎሳ ግጭት የሚዳርጉ ከባባድ አደጋዎችን እየፈጠሩ ያሉት በመንግስት ጉያ የተወሸቁት ሁከት ፈጣሪዎች፣ መዋቅሮችና ፖሊሲዎች አባታቸው ኢሕአዴግ ነው። ወዘተ …….

ያደፈው በሕዝብ ደምና ለቅሶ የጨቀየው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ባለፉት አመታቶች በርካታ መንግስታዊ ወንጀሎችን ሰርቷል፤ አሁንም በተዝረከረከው መዋቅር የከፋ ሽብር በሕዝብ ላይ እያካሔደ ነው።ኢሕአዴግም ተዋኻደም አልተዋኻደም ፤ ኢሕአዴግ ኢሕአዴግ ነው። የስም ውሕደት ብቻውን ዋጋም የለውም ፤ በነብስም በስጋም ካልተቀየረ ለውጥም አያመጣም። ኦሕዴድም ብአዴንም ስማቸውን ቀይረዋል ግብራቸውን ግን አልቀየሩም።ሕወሓት ስሟንም ግብሯንም አልቀየረችም።ጥቂት አመራሮች ካልሆኑ በስተቀር ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ካለፉት ስሕተቶቹ ተምሮ አዲስ ነገር ለመፍጠር እየሰራ አይደለም።ባለህበት እርገጥ ሆኗል።

ኢሕአዴግ በተከፋፈሉ ኃይሎች ተከቧል።ለስልጣን ከቋመጡ ኋይሎች ጀምሮ እስከ ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ድረስ እየተራወጡ ድርጅቱን ኮማ ውስጥ አስገብተውታል። አጋር ድርጅቶችም ቢሆኑ ወደ አሸናፊው ኃይል ለመቀላቀል እንደፔንዱለም እየተወዛወዙ ነው።እነዚህን ኃይሎች ለመለየት ከፍተኛ ፍጭት ቢኖርም የደፈረሰው እንዲጠራ ያበጠው መፈንዳት አለበት ።

ኢሕአዴግን ለማመን ቢከብድም የመንግስት መራሹ አካል ገኖ በወጣበት መንገድ አዲስ ድርጅታዊ ኃይሉን አምቆ የያዘው አካል ወደፊት መግፋቱ የማይቀር ሀቅ ነው። ኢሕአዴግ ራሱን የብልጽግና ፓርቲ ቢለውም ባይለውም ስር ነቀል የርእዮተዐለም ፖሊሲና የመዋቅር ለውጥ እስካላደረገ ድረስ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ከማለት ውጪ ምንም ለውጥ የለውም።

ኢሕአዴግ ስሙን ከመቀየሩ በፊት ከስሕተቱ ይማር በዋነኛነት ከኢሕአዴግ የሚጠበቀው የሚከተለውን የጸረ ሕዝብ የዘረኝነት ፖሊሲውን በመቀየር ከላይ እስከታች ያለውን መዋቅሩን በአዲስ አሰራር ሲለውጥ ብቻ ነው። ካሁን ቀደም እንዳልነው አሮጌው ኢሕአዴግ ተቀብሮ አዲስ ኢሕአዴግ መወለድ አለበት። የስም መለወጥ ለወሬ ካልሆነ በቀር ፋይዳ ቢስ ነው። ከስሕተቱ የማይማር አንድም የሐገር ጠላት ሲልም ድንጋይ ብቻ ነው። – ምንሊክ ሳልሳዊ