የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦችና የሚወከሉበት ምልክቶች ይፋ ሆኑ

ለሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦችና የሚወከሉበት ምልክቶች ይፋ ሆኑ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦችና የሚወከሉበት ምልክቶችን ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ፥ ለማካሄድ ላቀደው ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ከዚህ በፊት ቦርዱ ይፋ ባደረገው የድርጊት መርሀ ግብር ላይ ቦርዱ ሁለቱ የህዝበ ውሳኔው አማራጭ ሃሳቦች የሚወከሉበትን አማራጭ ምልክቶች ይፋ እንደሚያደርግ በገለጸው መሰረት ይህንኑ አስመልክቶ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ከሲዳማ ዞን ምክር ቤት ጋር ምክክር ያደረገ መሆኑን ነው ያመለከተው።

በዚህም መሰረት፡-
1. “ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጎጆ ቤት ምልክት፣

2. “ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫነት እንዲያገለግል የተወሰነ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

EBC