በመማር ማስተማር ስራዎች ወቅት የፖለቲካ አመለካከትን ማንጸባረቅ አይገባም – ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ

በመማር ማስተማር ስራዎች ወቅት የፖለቲካ አመለካከትን ማንጸባረቅ አይገባም – ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውሳኔ ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውጭ በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚሳተፉ አካላት የፖለቲካ አመለካከታቸውን በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ማንጸባረቅ እንደሌለባቸው የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታም ምሁራን ከፖለቲካ አመለካከታቸው ወጥተው በሳይንሱና በምርምር ባገኙት ውጤት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ያስገድዳል።

የትምህርት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ ስርዓተ ትምህርቱ፣ ደረጃውን የጠበቀ መማሪያ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የግብዓት እጥረት፣ የዘርፉ ተዋንያን የአቅምና ፍላጎት ውስንነት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከዚህ ባለፈም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ አመራሮች በፖለቲካ ተጽዕኖ ስር መውደቅና ያንን ወደ ተማሪዎቻቸው ማስረጻቸው ችግሩን አባብሶታል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለኢዜአ እንዳሉት “በየትኛውም ዓለም ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ሊሆን አይችልም”።

ለአብነትም “የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በግዴታ እሰጣለሁ፤ ትምህርት ለዜጎቼ በነጻ እሰጣለሁ፤” የሚሉት ሃሳቦች ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስርዓተ ትምህርት ጉዳይ ላይም ፖለቲካዊ ውሳኔ ካልተሰጠበት መርሃ ግብሩ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ ትምህርት ነጻነትን ስለሚሻ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎችም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን በሙያ ብቃታቸው ብቻ መመደብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የሀገር በቀል እውቀት እናስተምራለን ሲባልም የአንድን እምነት ወይም የፖለቲካ ድርጅት አመለካከትና ርዕዮተ ዓለም መጫን አለመሆኑን ይገልጻሉ።

በሃገራችን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን መገንቢያ ማዕከል እንጅ የእርስ በርስ ግጭት መፍጠሪያ መሆን እንደሌለባቸውም አንስተዋል።

ምሁራን የትኛውም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም ሳይንሱንና የምርምር ግኝታቸውን ብቻ ማስተማር እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።