የመብራት መቆራረጥ ነዋሪዎችን ጦም እያሳደረ ፋብሪካዎችንም እያዘጋ ነው ተባለ።

መብራት በአማራ ክልል፡- ነዋሪዎችን ጦም እያሳደረ፤ ፋብሪካዎችንም እያዘጋ ነው::

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙት አገሮች መካከል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ በመቀጠል ሁለተኛዋ ግዙፍ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያላት አገር ናት:: ይህንን የተፈጥሮ ፀጋ ወደተግባር በመቀየር ስምንት ያህል ግዙፍ የውሀና የነፋስ ሀይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ሁለት ሺህ 268 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል እያመነጨች ጥቅም ላይ አውላለች::

ሌሎች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌከትሪክ ማመንጫ፣ ጊቤ ሦስት ፣ ገናሌ ዳዋ ሦስት የውሀ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን እንዲሁም የአዳማ ሁለት የነፋስ የሀይል ማመንጫ ጣቢያ እየገነባች ትገኛለች:: ስራዎቹ ሲጠናቀቁም አገሪቱ በጠቅላላው 10 ሺህ ሜጋ ዋት ሀይል እንድታመነጭ ያስችላታል ይላል የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ አገልግሎት በድረ ገጹ::

በርካቶችን ጦም ያሳደረው መብራት
ወጣት ነብዩ ስዩም በምዕራብ ጐንደር ዞን የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ ነው:: ወጣቱ እንደገለጸልን የ10ኛ ክፍልን አጠናቋል:: ይሁንና ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስገባ ነጥብ አላመጣም:: ታዲያ በወላጆቹ ድጋፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቱን በጐንደር ከተማ ተምሮ በማጠናቀቅ በትውልድ ቀየው መተማ ዮሐንስ ከተማ ሁለት የፀጉር ማስተካከያ ቤቶችን ከፍቷል:: ለአራት ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር ችሏል:: በየቀኑም በአራቱ የፀጉር ማስተካከያ ወንበሮች በአማካይ 50 ደንበኞችን ያስተናግዳል:: በሒሳብ ስሌት መሠረት ዋጋው ደንበኞች እንደሚሉት የፀጉር ቅርጽና ቁርጥ አይነት የሚለያይ ቢሆንም በግምት ከአንድ ሺህ ብር ያላነሰ ገቢ ያገኛል::

“ይሁን እንጅ” አለ ነብዩ” በመተማ ዮሐንስ ከተማ ኤሌክትሪክ ከሚኖርበት ቀን የማይኖርበት ይበልጣልና በስራችን ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል:: በሳምንት አራትና አምስት ቀናት መብራት ስለሚጠፋ የፀጉር ቤቱም ይዘጋል:: በመጨረሻም በደንበኞቼ ምክርና ጉትጎታ አነስተኛ በነዳጅ ሀይል የምትሰራ ጀኔሬተር በመግዛት መብራት ሲጠፋ እንጠቀማለን:: ታዲያ የጀኔሬተሯ የነዳጅ ፍጆታ የምንሰራውን ገንዘብ አሟጣ ትጠቀማለች:: ስለዚህ ይህም ቢሆን የሚያዋጣ ሆኖ አላገኘነውም:: እስካሁንም የዘለቅነው በደንበኞች ድጋፍና ድጐማ ነው” ብሏል::

ነብዩ በመጨረሻም የመንግስት ምክረ ሀሳብ ስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ነበር:: ይህንን ዘርፍም እንደሚያበረታታ ይወተውታል:: በሌላ በኩል የሀይል አቅርቦት የለም:: ታዲያ ነገሩ ̋ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ˝ ሆኖባቸዋል::

ሌላው አለሙ በቀለ ይባላሉ:: በምዕራብ ጐንደር አስተዳደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ ናቸው:: ግለሰቡ እንደገለፁት በከተማው ተገንብቶ ሥራ በጀመረው ‘ካልሚ’ የጥጥ ማዳመጫ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀምረው ነበር:: ይሁን እንጂ ፋብሪካው በመብራት ሀይል መቆራረጥና አለመኖር ብዙውን ጊዜ አይሰራም:: በቅጥራቸው ውል መሰረትም ደመወዝ የሚከፈላቸው የሰሩበት ቀን፣ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም መንግስት በካላንደር የሚዘጋቸው ቀናት ተቆጥረው ነው:: ከዚህ ውጭ ግን ስራ ከመጀመራቸው በፊት መብራት ከሌለ፣ ከተቋረጠ ወይም የሀይል ማነስ የፋብሪካውን ሞተር የማያሰራው ከሆነ ስራ አይኖርም፤ ክፍያም የለም:: ስለዚህ እነ አቶ አለሙ የመብራት አለመኖር ገቢያቸውን ስላሳጣቸው የስራ መስክ ለመቀየር ተገደዋል::እናም “መንግስት የሀይል አለመመጣጠኑን ለምን አይፈታውም?” ሲሉም ይጠይቃሉ::

መክሊት እጅጉ በ2011 የትምህርት ዘመን በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ አመት ተማሪ ነበረች:: እሷ እንደምትገልፀው በ14 አመታት የተማሪነት ህይወቷ አይታው የማታውቅ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሞት ሽረት ፈተና ገጥሟታል:: “እኮ እንዴት?” ቢሉ ዩኒቨርሲቲው የሙሉ ሰዓት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አይለምና:: በመሆኑም ኮምፒዩተር በተፈለገው ቀንና ሰዓት መጠቀም አይቻልም:: በእጅ ስልካቸው ላይም መረጃ ለመለዋወጥ አዳጋች ነው::

መክሊት እንደተናገረችው ዩኒቨርሲቲው እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ብቻ በጄኔሬተር የመብራት አገልግሎት ይሰጣል:: ታዲያ የተማሪው የአጠናን ባህሪ ደግሞ እንደ መልኩ የተለያየ ነው:: አንዳንዱ በውድቅት ሌሊት ሲጠና ይመቸዋል:: ሌላው ንጋት አካባቢ ቢሰራ ይገባዋል:: አልፎ-አልፎ መረጃ ሲያገላብጥ፣ ሲያጠና፣ ሲመራመር፣ ፕሮጀክት ሲሰራ፣… የሚያድር ብርቱ ተማሪ ቢኖርም ከምኞት የዘለለ አልሆነም፤መብራት የለማ! በዩኒቨርሲቲው የመብራት አለመኖር በተማሪዎች ውጤት፣ ህይዎትና ሥነ ልቦና ላይም ከፍተኛ ችግር አሳድሯል::

መክሊት አክላም “ወደ ፊት እንደ ነገሩ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች እንዴት ትምህርታቸውን በቤተ -ሙከራ፣ በቤተ- መጽሐፍት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአይ.ሲ.ቲ፣ በኤሌከትሮኒክስ ቤተ- መጽሀፍትና ምርምር ታግዘው ከወጡ አቻ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ሊወዳደሩ ይችላሉ?” በማለት መክሊት የሚመለከታቸውን የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሁሉ ትማፀናለች::

አቶ እርቅይሁን ሀብታሙ በበየዳ ወረዳ የድል ይብዛ ከተማ ነዋሪ ናቸው:: እሳቸው እንደተናገሩት የከተማዋ ነዋሪ መብራት የሚያገኘው ከአንድ ጄኔሬተር ነው:: ይህም ቢሆን ከምሽቱ 1፡00 እስከ 4፡00 ብቻ:: በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይ የገጠሩ ነዋሪ እህል በባህላዊ መንገድ በድንጋይ ወፍጮ ይፈጫል:: ቤተሰቡ ከኩራዝ ጭስ አልተላቀቀም:: በየትምህርት ቤቶች የፕላዝማ ትምህርት አይሰጥም:: የጤና ተቋማት ከፍተኛ ምርመራና የምርመራ ውጤትን የሚያሰሩት ደባርቅና ጐንደር ከተማ በመላላክ ዘዴ ነው::

እንደ አቶ እርቅይሁን ገለፃ ከበየዳ ርእሰ ከተማ ድል ይብዛ የተከዜ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ የሚርቀው 70 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው:: በአንፃሩ የትግራይ ክልል ከዚህ ግድብ 150 ኪሎ ሜትር ቢርቅም፤ መንገዱና መልከአምድሩ አስቸጋሪ ቢሆንም የመብራት ተጠቃሚ ግን ሆኗል:: “ታዲያ እኛ የበይ ተመልካች የሆነው ለምን ይሆን?” ሲሉ በቁጭት ጠይቀዋል::

የጉና የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካ በደቡብ ጐንደር አስተዳደር ዞን ይገኛል:: ሥራውን በ2003 ዓ.ም እንደጀመረ የፋብሪካው ሰራተኛ የነበሩት አቶ ገዳሙ ሉሌ ተናግረዋል::
እንደ አቶ ገዳሙ ገለፃ ፋብሪካው 95 ሠራተኞች ነበሩት:: ላለፉት ስምንት አመታትም ክልሉን የጠቀመ ፋብሪካ ነበር:: ከታህሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ግን ፋብሪካው በመብራት እጦት ምክንያት በመዘጋቱ ሰራተኞች ተሰናብተዋል፤ ማሽኑም ያለ ስራ በመቀመጡ ለዝገት ተዳርጓል::

የግዮን ውሃ ማምረቻ ፋብሪካም በዚሁ ዞን ይገኛል:: 155 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበት ፋብሪካም ነው:: የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንደገለፁት ይህ ፋብሪካ ወደ ስራ እንዳይገባ የመብራት አለመኖር ሳንካ ሆኖበታል:: ለእነሱም ምላሽ ለመስጠት ከአቅም በላይ ነው::
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሲሳይ አክለው እንደገለፁት በዞኑ የኢንዱስትሪ መንደር ተገንብቷል:: ባለሀብቶችም ልዩ ልዩ ፋብሪካዎችን ገንብተው ማሽን አሟልተዋል::
በጠቅላላው በዞኑ 50 ፕሮጀክቶች አሉ:: ነገር ግን ወደ ስራ የገቡት ስምንቱ ብቻ ናቸው:: “ለምን?” ከተባለ መብራት የለማ!

እንደ አቶ ሲሳይ ገለፃ የመብራት እጦቱ ለኢንቨስትመንቱ ብቻ ሳይሆን የደብረታቦርና አካባቢው ነዋሪም የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ዋነኛ ችግር ሆኗል፤ ለደብረታቦር ዩኒቨርሲቲንም የመማር ማስተማር ሂደት ተፈታትኖታል::
አቶ እንየው ዋሴ በምዕራብ ጐጃም አስተዳደር ዞን በቡሬ ከተማ የተገነባው የፊቬላ ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ ናቸው:: እሳቸው እንደገለፁትም የፊቬላ ኢንዱስትሪ በዋናነት የምግብ ዘይት ይጨምቃል:: የእንስሳት መኖ ያቀነባብራል:: የተለያዩ እቃዎችን መያዣ ካርቶን ይሰራል::

ይህ ኢንዱስትሪ 650 ሚሊዮን ብር ፈሰስ ሆኖበታል:: ለሁለት ሺህ የሰው ሀይል የስራ እድል የመፍጠር አቅምም አለው:: በቀን 450 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት መጭመቅ ይችላል:: የአገሪቱንም የምግብ ዘይት ፍላጎት 60 በመቶ ይሸፍናል:: ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን የሚያንቀሳቅስ መብራት ባለመኖሩ እየሰራ አይደለም::
ሌላው በቡሬ ከተማ የሚገኘው የሪች ላንድ ባዮ ኬሚካል ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ቴዎድሮስ ካሳ እንደገለፁት ይህ ኢንዱስትሪ በአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል እየተሰራ ነው:: ኢንዱስትሪው ወደ ማምረት ሲገባ የምግብ ዘይት፣ የእንስሳት መኖ፣ “ማልት”፣ አነቃቂ መጠጦች፣ ጉሉኮስ፣ ስታርች፣ … ይፈበርካል:: ኢንዱስትሪው ለአራት ሺህ 500 ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል::

“አሁን ለጊዜው” አሉ አቶ ቴዎድሮስ ” ስራችንን 500 ኪሎ ዋት ሀይል በሚያመነጭ ጄኔሬተር ልንጀምር ነው:: የመንግስትን በጐ ምላሽ በመጠባበቅ! የሆነ ሆኖ ኤሌክትሪክ የማይገኝ ከሆነ በጄኔሬተር መስራት አይቻልም:: ስለዚህ በተሟሟቀው ስራችን ላይ የቀዘቀዘ ውኃ እንዳይደፋበትና ተስፋችን እንዳይጨልም መንግስት የመብራቱን ጉዳይ ሊፈጽምልን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል::

ምሁራንስ ምን ይላሉ?
በኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር ተቋም የምርምር ባልደረባና የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የመብራት መቆራረጥ፣ የሀይል እጥረት፣ መሄድና መምጣት (OFF and ON) መቋረጥ ከነዋሪው ባሻገር በኢንዱስትሪዎችና በፋብሪካዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው:: በውጭ ምንዛሬ እጦት፣ በጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር፣ የማበረታቻ ድጋፍ አለመኖር የፋብሪካዎች ፈርጀ ብዙ ፈተና ነበር:: የሀይል እጦት ሲታከልበት በርካቶችን ከስራ ሊስወጣቸው ይችላል:: እያስወጣቸውም ነው፤ ይህም ኢኮኖሚውን እያጋሸበው ይገኛል::

ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም ባለሀብቶችን በመሳብ ረገድም ሚናው አሉታዊ ይሆናል:: የሀይል እጦቱ ፋብሪካዎች በነዳጅ እንዲጠቀሙ ካደረገ ደግሞ በአገር ውስጥ የእነዚህ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ይንራል:: አሁን እየታየ ላለው የዋጋ መናርም እንደ ምክንያት ይጠቀሳል ብለዋል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማክሮ ኢኮኖሚ መምህርና ተመራማሪ ብሎም በአለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አማካሪ ዶ/ር መሐሪ ሰንደቁ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰተው የሀይል እጥረት ዋናው ምክንያት የማከፋፈያ ጣቢያ – አለመኖር፣ የትራንስፎርመርና የትራንስሚሽን እጥረት አይደለም:: በአገሪቱ የሚመረተው ሀይል በአግባቡና በፍትሃዊነት ለየክልሎቹ በፍላጐታቸውና በህዝብ ቁጥራቸው መጠን ተቀምሮ ስርጭት አለመደረጉ ነው፤ ስለሆነም ያለ አመክንዮ አንዱ ክልል ከፍተኛ መጠን ሀይል ሲለቀቅለት ሌላው በርካታ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ እያለው፣ የህዝብ ቁጥሩ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ አነስተኛ ሀይል ይለቀቅለታል:: በአማራ ክልል የተከሰተው የሀይል እጥረትም ምክንያቱ ይኸው ነው::

እንደ ዶ/ር መሐሪ ገለፃ በ2009 በአገሪቱ የተጀመሩ የግል ኢንቨስትመንቶች ግብአት ባለማግኘታቸው 26 ቢሊዮን ብር ሳይገኝ እንደቀረ የአለም የገንዘብ ድርጅት “መኒ” በተሰኘው ጆርናል ላይ ይፋ አድርጓል:: ከዚህ ውስጥ ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮኑ በመብራት እጦት የደረሰ ኪሳራ ነው:: ሩብ ያህሉ ደግሞ የአማራ ክልል ድርሻ ነው::

ዶ/ር መሐሪ አክለውም በ2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከኢንቨስትመንቶቿ በሰላም መደፍረስና በመብራት መቆራረጥ የተነሳ 30 ቢሊዮን ብር አጥታለች ተብሎ በምጣኔ ሀብት ምሁራን ተሰልቷል:: እንደ የአለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት በ2011 ኢትዮጵያ 38 ቢሊዮን ብር የኢኮኖሚ ኪሳራ ደርሶባታል:: ከዚህ የሂሳብ ቀመር ውስጥ ከሩብ የሚልቀው የአማራ ክልል ድርሻ ነው:: ታዲያ የገንዘቡ ስሌት ከስራ ውጭ የሆነውን የሰው ጉልበትና የማሽን ሂሳብ ከመብራት አለመኖር ጋር ታሳቢ ያደረገ ነው::

ዶ/ር መሐሪ ጨምረው እንደገለፁት በ2010 ዓ.ም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የስራ ቦታዎች በመዘጋታቸው በአማራ ክልል ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሰው ሀይል ከስራ ውጭ ሆኗል:: ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ከስራ ገበታው የተፈናቀለው ወይም ሥራ ይፈጠርለት የነበረ ሲሆን መብራት ባለመኖሩ ግን እድሉን እንዳጣ ይገመታል::
ዶ/ር አበጀ ታፈረ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው:: እንደሳቸው ገለጻ በዩኒቨርሲቲው የ24 ሰአት የመብራት አገልግሎት ባለመኖሩ በ2011 የትምህርት ዘመን ሶስት ሺህ መደበኛ ተማሪዎች በአግባቡ እንዳይማሩ ተጽእኖው ከፍተኛ ነበር:: በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ሶስት ጄኔሬተሮችን ገዝቶ መብራት እስከ ሌሊቱ 6፡00 ብቻ ቢያቀርብም የነዳጁ ፍጆታ መጨመርና ዋጋ መናር የሚቀመስ አልነበረም::ዩኒቨርሲቲውንም ለኪሳራ ዳርጓታል::

በፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ዶ/ር አሰፋ መኮንን እንደገለፁት ከአገሪቱ ከሚመረተው የኤሌክትሪክ ሀይል ውስጥ የአማራ ክልል በፍትሃዊነት ተጠቃሚ አልተደረገም:: ስለሆነም የሀይል እጥረቱ በተለይ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል:: ትምህርት ቤቶችም ትምህርትን በቤተ ሙከራ አስደግፈው እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል:: አ.ይ ሲ.ቲ የለም፤ በፕላዝማና ቤተ- መፃህፍት የተደገፈ ትምህርት አይሰጥም::

በመሆኑም ለአብነት፦ በአንድ ወቅት የህዝብ ብዛቱ ከአማራ ክልል በሶስት እጅ የሚያነስ ክልል ካስፈተናቸው ተማሪዎች ዘጠኝ ሺህ ወደ ዩኒቨርሲቱ ሲያስገባ የአማራ ክልል ግን አራት ሺህ ብቻ አስገብቷል፤ ለዚህ ዋናው ምክንያትም በመብራት አለመኖር ትምህርቱ በመርጃ መሳሪያዎች ተደግፎ እንዳይሰጥ ማድረጉ ነው::
የአመራሩ ምላሽስ ምን ይሆን?

የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው በ2012 በጀት አመት የነበሩ ችግሮች ስለተለዩ የሀይል ብክነትን በመቀነስ እንደየ ጥያቄው ክብደት እየተጠና ጊዜያዊና ዘለቄታዊ ምላሽ ይሰጣል:: ለተግባራዊነቱ ደግሞ የክልሉ መንግስት ከጐናችን ቁሞ በምክር፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ድጋፍ ሊያግዘን ቃል ስለገባ ችግሮች ደርጃ በደረጃ ይፈታሉ ብለዋል::

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ እንደገለፁት በአማራ ክልል የተከሰተውን የሀይል እጥረት ለማስወገድ፣ ደረጃ የማሳደግና አዳዲስ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ ቁልፉ መፍትሄ በየከተሞች ሰብስቴሽን መገንባትን ግድ ይላል:: ለዚህም በተመረጡ የክልሉ ከተሞች ማለትም፦ በደብረታቦር፣ በቡሬ፣ በደባርቅና አካባቢው፣ በአረርቲ፣ በወልዲያ፣ በባህር ዳር፣…. ሰብስቴሽን ለመገንባት ከቻይናው ሲ.ቲ.ኢ ኩባንያ ጋር ውል ታስሯልና ችግሮቹ ከ2012 መጨረሻ እስከ 2014 ድረስ ሙሉ በሙሉ ይፈታል::

የአማራ ከልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በ2012 በጀት አመት የክልሉ መንግስት በክልሉ የኤሌክትሪክ አሰጣጥ እንዲሻሻልና አዳዲስ የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በአብሮነትና በቅንጅት ይሰራል:: የክልሉ መንግስትም ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል:: የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል አገልግሎትም ቃል የገባውን ይፈጽም ዘንድ በቅርብ እየተከታተሉና እየደገፉ እንደሚሰሩ ጭምር ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጠቁመዋል።

Source AMMA