የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ ሰልፎች በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፎቹ በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በምዕመኗ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በመቃወም ዛሬ በአማራ ክልል ሰልፎች ተካሂደው በሠላም ተጠናቅቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በምዕመኖቿ ላይ የሚፈጸመው ግፍና መከራ እንዲቆም፣ በቤተ ክርስቲያንና ምዕመኖቿ ላይ ግፍ የፈጸሙት አካላትም በሕግ እንዲጠየቁ ነው በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ምዕመናኑ እና የሀይማኖት አባቶች የጠየቁት፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሠጠው፣ በቤተ ክርስቲያኗ እና ምዕምኖቿ ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላትንም ተጠያቂ እንዲያደርግ በሰልፎቹ ተጠይቋል፡፡

ጥቃት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲሰሩ እና ለተጎዱ ወገኖችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈልም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሰልፎቹ በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በብቸና፣ በደጀን፣ በሞጣ፣ በደብረ ብርሃን፣ በማጀቴ፣ በጫጫ፣ በአረርቲ፣ በመሐል ሜዳ፣ በፍኖተ ሠላም፣ በቡሬ፣ በመርዓዊ፣ በእንጅባራ፣ በደባርቅ፣ በዳባት፣ በአዲ አርቃይ፣ በጯሂት፣ በወልድያ፣ በቆቦ፣ በላልይበላ፣ በውጫሌ፣ በወረኢሉ፣ በደላንታ፣ በኮን፣ በዳንግላ፣ በዱር ቤቴ፣ በአዲስ ዘመን እና በሌሎችም ከተሞች ተካሂደዋል፡፡