የተካደ ሕዝብ – (ፍትሕ መጽሔት)

የተካደ ሕዝብ – በፍትሕ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሁፍ

ኦዴፓ-መራሹ ስብስብ አራት ኪሎን በረገጠ ማግስት፣ በርካታ ሥርዓት-ወለድ ችግሮች እንደሚለውጡ፣ አፋኝ አዋጆች እንደሚሻሽሉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደሚሰፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚቀሩ፣ ስቅየት-መሩ ፖሊሳያዊ ‹ምርመራ›፣ ሳይንሳዊ እንደሚደረግ፣ በየትኛውም ወንጀል የተጠረጠረ ሰው ያለ በቂ ማስረጃ እንደማይታሰር… ቃል-መግባቱ ይታወሳል።
ይሁንና ያሳለፍናቸው 12 ወራት የሚነግሩን ጥሬ ሐቅ፣ በተቃራኒው ስለመሆኑ ማስረጃዎችን ቆጥረን እንመለከታለን።

ድኀረ-ቡራዩ

በመስከረም ወር በቡራዩ ከተማ ኦሮምኛ ተናጋሪ ባልሆኑ ዜጎች ላይ በተቀነባበረ መንገድ ጭፍጭፋና መፈናቀል ተፈጽሟል። ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ከክስተቱ አራት ወር በኋላ በሰጠው መግለጫ፣ ከመንግሥት አካላትና የፀጥታ መዋቅር አባላት ውስጥ በሰይጣናዊው ድርጊት እጃቸውን የነከሩ እንደነበረ ጠቅሶ ክስ መመስረቱን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ዘግናኝ እልቂትና መከራ የተቆጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ መንግሥት በአጥፊዎቹ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሲሞክሩ ከሦስት ያለነሱ ወጣቶች በ‹ፀጥታ አስከባሪ› ጥይት ሲገደሉ፣ በሺ የሚቆጠሩት ደግሞ በጅምላ ታፍሰው እስር ቤት ገብተዋል። ይህ ሲሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሥልጣን ከጨበጡ መንፈቅ እንኳ በቅጡ አልሞላቸውም።
ለእስር የተዳረጉት አብዛኛው የከተማዋ ወጣቶች ከመኖሪያ ቤታቸው በኃይል ተጎትተው፣ ከመንገድ ላይ በጠመንጃ ታግተውና ከመዝናኛ ቦታዎች ታንቀው ሲሆን፤ ከእነዚህ መሀል ሥራ ያላቸው ተለይተው በከፊል ሲለቀቁ፣ የተቀሩት ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ተግዘው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ስቅየት ተፈፅሞባቸዋል። ይህ አይነቱ የግፍ ብትር ባለፉት ሩብ ክፍል ዘመን አሮጌው ኢሕአዴግ ሲተገብረው የሰነበተና ለዛሬ የተላለፈ ‹ክፉ ውርስ› እንደሆነ ይታወቃል። ግፉአኑ በ‹ተጠረጠሩበት ወንጀል› ምንም አይነት የፖሊስ ምርመራ ሳይካሄድባቸውና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በ‹አንጎል አጠባ› ስም የወረደባቸው መከራ የሥርዓቱን እብሪትና ማንአህሎኝነት አሳይቷል። ‹ወንጀል ተፈጽሟል› በሚል ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ ማጎሪያ ካምፕ ማሰቃየት የፋሽስታዊ ባህሪ ማቆጥቆጥ ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድም ይታወቃል።

በኦሮሚያ

በኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ወታደራዊ አዛዥነት የሚመራውና በተወሰኑ የወለጋ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ‹ኦነግ-ሸኔ› የፈፅመውን የሽብር ተግባርም አገዛዙ እንደ መልካም አጋጣሚ የቆጠረው ይመስላል። በተለይም የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን ተገን አድርጎ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በገፍ ወደ እስር ቤት ማጋዙ ለወራት የተዘገበ ዜና ነው። ምዕራብ ኦሮሚያ፡- ነቀምት፣ ደንቢዶሎ፣ ጀልዱ፣ ግንደ-በረት፣ ጥቁር እንጪኒ፣ ጉደር፣ ሙገር፣ አደዓ በርጋ፣ ሜታ ሮቢ፣ አምቦ… እስሩ በስፋት የተንፀባረቀባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን የፍትሕ ምንጮች አረጋግጠዋል።

በቅርቡ የ‹ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)›ም ባወጣው መግለጫ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ አባሎቹን ጨምሮ፣ ከተፈጠረው ችግር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎችም ለእስር መዳረጋቸውን ይፋ አድርጓል። ኦፌኮ ከመደበኛ እስር ቤቶች በተጨማሪ፣ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ፣ አዳማ እና ሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛዎች በጊዜያዊ እስር ቤትነት እያገለገሉ መሆኑንም በመግለጫው አካትቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአሰላ ከተማ ከሃይማኖት እና ከኢዜማ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በግፍ የታሰሩት በዚሁ ዐመት እንደነበረ ይታወሳል።

ድሬደዋ

ድሬደዋ፣ ከደቡብ አፍሪካው የ‹አፓርታይድ ሥርዓት› በተገለበጠ የ40፣ 40፣ 20 አስተዳደር እንድትመራ ተፈርዶባት፣ ከኦሮምኛና ሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ውጪ ያለው ነዋሪ በጥልቅ ጭቆና ሥር መውደቁ ይታወቃል። ከተዛነፈው የፌደራል ሥርዓትም የሚከፋው ይህ አሰራር፣ በቁጥር ብልጫ ያለውን ውህድ-ማኀበረሰብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ሆነ ከውክልና ሥልጣን አግልሎታል።
በወርሃ ጥር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በድሬደዋ ተቀስቅሶ የነበረው አለመግባባት፣ ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የተለወጠበት ገፊ-ምክንያት የአግላዩ አስተዳደር-ዘዬ ነው። ‹አፈቴስ› ተብሎ በሚታወቀው አከባቢ የተሰባሰቡ ወጣቶች ከተማዋ ለዐመታት የተዘፈቀችበት ብልሹ አሰራር መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቃቸው የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተለያዩ ሰፈሮች ሊዛመት ችሏል።
በወቅቱ ለዐመታት የተከማቸ ብሶት የወለዳቸው የድሬደዋ ነዋሪዎች ቁጣቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ በመጋላ ጨብጡ፣ ፖሊስ መሬት፣ ገንደገራድ አከባቢዎች ከ14 የማያንሱ ዜጎች ተገድለዋል። በሥርዓቱ የጭካኔ ጭፍጨፋ የተበሳጩ ከ300 በላይ ወጣቶች ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ ከተማ በሚገኘው ‹ተስፋዬ ሜዳ› ከተሰባሰቡ በኋላ፣ ‹ከንቲባውን እናነጋግራለን› በሚል ወደ ቢሯቸው ለማምራት መንገድ ጀምረው ሳለ፣ ዐድማ በታኝ ፖሊሶች ድንገት ደርሰው ጉዞውን ለመግታት የወሰዱት የኃይል እርምጃ ቁጣውን አንሮት፣ ከዚራ፣ ደቻሳ፣ ቀፊራ፣ ቶነል፣ አሸዋ፣ አዲስ ከተማ፣ ሳቢያን፣ ገንደቆሬ፣ ገንደቦዬ አካባቢዎችን ያዳረሰ የአደባባይ ተቃውሞ ቀስቅሷል። በምላሹ የከተማ አስተዳደሩም ከሁለቱ ብሔር ውጪ ያሉ አያሌ ወጣቶችን ከየቤታቸው አፍሶ ማሰሩ አይዘነጋም። ዕድሜያቸው ከ16 ዐመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ሳይቀር የግፍ እመቃው ሰለባ ነበሩ። ‹ልጆቻቸው እንዲፈቱ› የጠየቁ እናቶች ብቻ የተሳተፉበት ሰልፍ መደረጉም አይዘነጋም።
ድሬደዋ ዛሬም በኦዴፓ-ሶሕዴፓ ጥምረት በሚመራው የአፓርታይድ አስተዳደር እየማቀቀች እንደምትገኝ ይታወቃል።

ድኀረ-ሰኔ 15

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በባሕር ዳር እና አዲስ አበባ የተከሰተውን ግድያ ተከትሎ፣ ኦዴፓ-መራሹ መንግሥት የአካሄደው የጅምላ እስር፣ የዶ/ር ዐቢይ አህመድን ‹አዳሽ-ነኝ› ባይነት በአጭር አስቀርቷል።
ከላይ በተጠቀሰው የተረገመ ቀን በዐማራ ክልል ርዕሰ- መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና ጓዶቻቸው ላይ በባሕር ዳር፤ እንዲሁም በኤታ-ማዦር ሹሙ ጄነራል ሰዓረ መኮንን በአዲስ አበባ ላይ የተፈፀመውን ጭካኔያዊ ግድያ፣ የፌዴራሉ አስተዳደር ‹መፈንቅለ-መንግሥት› የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። ይህን ተከትሎም በክልሉ የፀጥታ መዋቅር በኃላፊነት እያገለገሉ የነበሩት ብ/ጄ ተፈራ ማሞና ኮሎኔል አለበል አማረን ጨምሮ፣ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ከባሕር ዳርና አካባቢው በዘፈቀደ አፈሳ ወህኒ ወርደዋል።
የጅምላ እስሩ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም ቀጥሎ፣ ቁጥሩ በትክክል ያልታወቀ ሕዝብ በገፍ ተግዞ ዛሬ ድረስ እስር ቤት ይገኛል። አፈናው የ‹ዐማራ ብሔርተኝነት ንቅናቄ (አብን)› ከፍተኛ አመራርና አባላትን፤ እንዲሁም የ‹አዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ)› አመራርና አባላትንም አካትቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ጉዳዩን አለቅጥ- ለጥጦ የግፍ እርምጃ ከመውሰዱ በዘለለ፤ እስረኞቹ ላይ የ‹ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ› አንቀጾችን መጥቀሱ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ሳይቀር ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል። ሕወሓት-መራሹ ኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የደነገገውን ይህንን አዋጅ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እንደሚያሻሽሉት ቃል ገብተው እንደነበረ ይታወሳል። ይሁንና የሰኔ 15ቱን አሳዛኝ አጋጣሚ ተንተርሰው፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን በዚሁ ሕግ ማጥቃታቸው መጪውን ጊዜ አስፈሪ አድርጎታል። በ‹ለውጡ› የጫጉላ ሰሞን የበዛ ተስፋ አሳድረው የነበሩ ዜጎች፣ አብዝተው የሰበኩለት የዴሞክራሲ ሽግግር ‹ተቀልብሷል› በሚል፣ በማኀበራዊ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞቸውን እያሰሙ ነው።
‹መፈንቅለ መንግሥት› የሚል ስም በተሰጠው የፖለቲካ መሪዎች እና ወታደራዊ አዛዥ ግድያ ላይ ‹እጃችሁ አለበት› ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎች፣ የምርመራ ሂደቱም ሆነ ፍርድ ቤቱ ጊዜ ቀጠሮ እየሰጠ እስር ቤት እንዲሰቃዩ የተባበረበት መንገድ የክሱን ስሁት-ገጽታ ግላጭ አውጥቶታል።

መደምደሚያ

ሕወሓት ከመንበረ ሥልጣኑ እንደ ቡሽ የተፈነጠረበትን ሕዝባዊ እምቢተኝት ተመርኩዘው፣ አራት ኪሎን የረገጡት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለጥምርም ሆነ ለሽግግር መንግሥት ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ዜና ነው። እኒህን ሁለት አማራጮች ውድቅ ካደረጉ በኋላ፣ ለፖለቲካ ማሻሻያ ቅድሚያ ሰጥተው አገሪቱ የተበጀችበትን አምባ-ገነናዊ ሥርዓት መቃብር ከትተው ከዴሞክራሲ እንደሚያዛምዷት የገቡት-ቃል አማናዊ ተደርጎ መወሰዱ ይታወሳል።
ሊሰናበት አራት ቀናት ብቻ በቀረው 2011 ዓ.ም በተለይም በዋናነት በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ የተፈፀመው ጅምላ እስር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ዛሬም ሥልጣን ላይ ያለው አመራር ከነባሩ ኢሕአዴግ አለመለየቱን ለማስረገጥ የሚጣደፍ አስመስሎታል። በአደባባይ የተዘፈነለት፣ ቅኔ መወድስ የቀረበለት ‹ለውጥ›ም የጉልቻ እንደሆነ መስክሮ አልፏል።
ይሁንና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት እየረፈደበት ቢሆንም፣ በተመናመኑት ቀሪ ጊዜያት ለገባው-ቃል ከታመነ፣ አገርና ሕዝብን ከጥፋት መታደግ አይሳነውም። ለሕግ የበላይነትና ለተቋማዊ ነፃነት ራሱን ማስገዛት ከቻለ፣ ከአሰቃቂ ውድቀት የሚተርፍበት መንገድ ጨርሶ አልተዘጋም። የቀደሙ ገዥዎቻችን የተቸነፉበትን የሥልጣን-መግነጢስ ድል አድርጎ ደማቅ ታሪክ የሚጽፍበት የዕድል ካርታም ገና ከእጁ አልወደቀም።