ለ14 ዓመታት ወደ ሥራ ያልገባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መፍትሔ እንቆቅልሽ ሆኗል።

[addtoany]

“ውል ሰጪም ተቀባይም እነማን እንደሆኑ አልታወቁም”፤ ትምህርት ቤቱም ከ14 ዓመታት በኋላም ሥራ አልተጀመረበትም፡፡

ለ14 ዓመታት ወደ ሥራ ያልገባው ዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መፍትሔ እንዲሰጠው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ሰቆጣ ከተማ የሚገኘው ዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተገነባ 14 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተማሪዎች ቅበላ እየጨመረ በመምጣቱ ትምህርት ቤቱ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ለጊዜያዊ መፍትሔነት ሁለት ባለ 10 ክፍል ቆርቆሮ ቤቶችን አስገንብቶ ነበር፡፡ ይህም በቂ ባለመሆኑ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት እንዲሠራ ኅብረተሰቡ በ1998 ዓ.ም ገንዘብ ማዋጣቱን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት መረጃ ደርሶታል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አያልነሽ እንደተናገሩት ዝቅተኛ የከተማዋ ነዋሪዎችም ከዕለት ጉርሳቸው ይልቅ ለልጆቻቸው የነገ ሕይወት አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለው ላሰቡት ት.ቤት ግንባታ መቀነታቸውን ፈትተው ሰጥተዋል፡፡ በኅብረተሰቡ መዋጮ ብቻ የተሠሩ ባለ አንድ ፎቅ 16 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በጥራት መጓደል የተነሳ ‹‹እንደ ሽቦ አልጋ ያረገርጋል›› ያሉት ወይዘሮ አያልነሽ ግንባታው ፈርሶ እንደ አዲስ እንዲሠራ ቢጠይቁም ለ14 ዓመታት ውሳኔ ሰጭ አጥቶ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ደርበው ታረቀ ትምህርት ቤቱ ሲመሠረት ጀምሮ ከ66 ዓመታት በፊት ያገለገሉ ክፍሎች ሳይፈርሱ በቅርቡ በኅብረተሰብ ተሳትፎ መንግሥት እንዲያስገነባ የተሰጡ ክፍሎች ጥቅም አለመስጠት እንዳሳዘናቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን የፈጠረው አካል በህግ አለመጠየቁም ተገቢ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የሰቆጣ ከተማ አስተዳድር ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀግኔ ገበያው ኮንትራቱን የወሰደውን ግለሰብም ሆነ ውሉን የሰጠው የመንግሥት ተቋም ለመጠየቅ መረጃዎችን ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሕግ ለመጠየቅ ኮንትራቱን የወሰደውን ባለሃብት፣ ምን ያህል ወጭ እንደወጣ እና ምን ስምምነት እንደነበረው ማወቅ አለመቻሉንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ሕንፃው እያረገረገ በመሆኑ ማፍረስም ሆነ ማሻሻያ ማድረግ አለመቻሉን በመገንዘብ ኮሚቴ በማዋቀር የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ጀግኔ ፋይናንስ ፅህፈት ቤቱ ያሉ መረጃዎችን እንዲያቀርብ ተጠይቆ እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የሕዝቡ ሀብት ተበልቶ አይቀርም፤ ለመማር ማስተማሩ ለ14 ዓመታት እንቅፋት የሆነው ሕንፃ እልባት ያገኛል›› ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ ከንቲባ በኃይሉ መኮንን ናቸው፡፡ ኮንትራቱን አሸንፎ የሠራው ባለሃብቱ እንዲያስረክብ ወይም መሬቱን መንግሥት ስለሚፈልገው የፍትህ ስርዓቱ በሚፈቅደው ልክ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆኑ ነው አቶ በኃይሉ ለአብመድ የተናገሩት ፡፡

አብመድም በተከታታይ ሁለት ዓመታት በቦታው በመገኘት ችግሩን አረጋግጦ መፍትሔ እንዲሰጠው ቢያመላክትም ዛሬም የ14 ዓመታትን እንቆቅልሽ ለመፍታት ሌላ ዓመታትን ፈልጓል፡፡ በርካታ ተማሪዎች በዳስ መማሪያ ክፍሎች እየተማሩ በሚገኙበት የብሔረሰብ አስተዳደሩ በአሰራር ችግር እና በውሳኔዎች መዘግየት የተነሳ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግና ግንባታውን ማስተካከል አልተቻለም፡፡ ይህም ተማሪዎች ከቆርቆሮ ክፍል እንዳይወጡ ማድረጉንም ታዝበናል፡፡ የመንግሥት ተቋማት የመረጃ አያያዝ ደካማ መሆን ችግሩ እንዳይፈታ እንዳደረገም ኃላፊዎቹ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡