“ፖሊስ ደበደበኝ ፤ አንገላታኝ የሚል አቤቱታ ቀርቦልን አያውቅም” የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር

ከትናንት በስቲያ አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረባ እጁ በካቴና የታሰረ ግለሰብን ሲደበድብ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ብዙዎች በፖሊስ ስለደረሰባቸው ድብደባና እንግልት ገጠመኛቸውን እያጋሩ ነው። ቢቢሲ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዘላለም መንግስቴ ቀጣዮቹን ጥያቄዎች አንስቷል።

ቢቢሲ፡ ፖሊሶች የሕዝብ አገልጋይ ስለመሆናቸው ምን ዓይነት ስልጠና ነው የሚሰጣቸው?

አቶ ዘላለም፡ በዋናነት የስልጠና ችግር አይደለም። በዚህ ዓመት አዲስ ለውጡን ተከትሎ ለሁሉም ፖሊስ የአገልጋይነት ስልጠና ሰጥተናል። አገልጋይ የሆነ የፖሊስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ አገልግሎታችንም የፖሊስ ስምሪታችንም ሕዝብን የሚያገለግል፣ የሚያከብር፣ ፖሊስ የሚፈራ ሳይሆን የሚከበር እንዲሆን የሚያስችል ሰነድ ቀርጸን ያለንን ፖሊስ በሙሉ አሰልጥነናል። ከአንድም ሁለቴ፣ ሦስቴ። ይህንን ስልጠና እታች ኮሚኒቲ ፖሊስ ድረስ ጭምር አውርደነዋል።

ቢቢሲ፡ ስልጠናው የተሰጠው ለቀደሙት ፖሊሶች ጭምር ነው ለአዲሶች ብቻ?

አቶ ዘላለም፡ ለሁሉም ነው። አሁን ያለውን አመለካከት የሰው ፖሊስ የመፈራት፣ ፖሊስ ሲያይ ከመሸማቀቅ ስሜት እንዲወጣና ዜጎችን የምናገለግል፤ ለዚህም ቃለ መሀላ ፈጽመን፣ ይሄንን ዩኒፎርም ለብሰን የወጣን መሆናችንን እንዲገነዘቡት የሚያደርግ ስልጠና አዘጋጅተን እየሰጠን ነው። ነገር ግን በሽግግር ጊዜ ላይ መሆናችን ልብ ሊባል ይገባል። ትናንት የታየው ያልተገባ ተግባር ከአንዳንድ ፖሊሶች የግል ባህሪ የሚመነጭ ፤ ተቀባይነት የሌለው የግለሰቦች ችግር ነው። ልጆቹ አዲስ በመሆናቸው የአገልጋይነት ስሜት ገና ወደ ውስጣቸው ያልገባና ያልተቀበሉት ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ወስደን የማጣራት ሥራ ጀምረናል። ይሄ እንጂ የፖሊስ የመዋቅሩ፣ የአስተሳሰብም፣ አጠቃላይ የአገልጋይነት ስሜትን ያለመቀበል ነገር አይደለም።

ቢቢሲ፡ ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ያለው እውነታ ሰው ፖሊስ እኔን ሊጠብቀኝ፣ ሊያገለግለኝ ነው የተሰማራው ብሎ ሳይሆን ፖሊስ የመፍራት ነገር ነው ያለው። በፖሊሶች በኩልም አለቃህ ነኝ የምልህን ታደርጋለህ የሚል አመለካከት ነው ያለው። ይህን አመለካከት ለመቀየር ስልጠናው ምን ያህል ረድቷል ይላሉ?

አቶ ዘላለም፡ ሽግግሩ ገና አንድ ዓመት አልሞላውም። ያ አስተሳሰብ ረዥም ጊዜ የቆየ ነው። ከዛ አስተሳሰብ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ጨርሶ ሁሉም ትክክለኛውን አመለካከት ይዞ ይወጣል ማለት በጣም ይከብዳል። ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው ቢሆንም ግን ረዥምም ጊዜ ሳንወስድ በአጭር ጊዜ የምንቀይረው ነው የሚሆነው።

ቢቢሲ፡ ለእንደዚህ አይነት ተግባር ምን አይነት የሥነ ምግባር (ማረሚያ) ቅጣት ነው የሚወሰደው?

አቶ ዘላለም፡ የነገርኩሽ ‘ጄነራል’ [ጠቅለል ባለ መልኩ] ነው። በዚህ ዓመት ያጋጠመን ይህ ነው።

ቢቢሲ፡ እናንተ ወደ አመራር ከመጣችሁ በኋላ በአንድ አመት ውስጥ አጋጥሞ አያውቅም?

አቶ ዘላለም፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ያልወጡ፣ እኛ እርምጃ የወሰድንባቸው የተለያዩ የዲሲፒሊን [የሥነ ምግባር] ግድፈቶች አሉ።

ቢቢሲ፡ ምን እርምጃ ተወሰደ?

አቶ ዘላለም፡ የተለያየ ነው። በወንጀል የሚሳተፍም ካለ እንደ ወንጀል መጠኑ በሕግ እንዲጠየቅ፣ የስነምግባር ችግር ያለበት እንዲሁም ሃላፊነቱን ያልተወጣም እንዲጠየቅ አድርገናል። ችግሮች ያየንባቸውን በየደረጃው ከላይ እስከታች የማስተካከያ እርምጃ ወስደናል።

ቢቢሲ፡ ተደብድቦ ወይም በፖሊስ በደል ደርሶበት ወደናንተ ለአቤቱታ መጥቶ የሚያውቅ ሰው አለ?

አቶ ዘላለም ፡ በፍጹም። ሪፖርት ካላችሁ ቢሯችን 24 ሰዓት ክፍት ነው። በተለይም ከፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የምንታገሰው ነገር የለም።

ቢቢሲ፡ በትላንቱ ድርጊት ላይ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ጉዳያቸው እየታየ መሆኑ ተሰምቷል። እውነት ነው?

አቶ ዘላለም፡ እርምጃ ወስደናል።

ቢቢሲ፡ የተወሰደው እርምጃ ምንድን ነው?

አቶ ዘላለም፡ የተለያየ እርምጃ አለ። ፖሊስ የውስጥ አሠራር አለው። አንድ የፖሊስ አባል ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽም [የሚቀጣበት ደንብ] ሥርዐት አለው። የትኛውም መሥሪያ ቤት እንዳለው ማለት ነው። [ፖሊሶቹን] ከሥራ ውጪ አድርገን፣ ጉዳዩን በሕግ ጥላ ሥር እንዲያዝ አድርጎ የማጣራት ሥራ እየሠራን ነው።

ቢቢሲ፡ ስለዚህ ሁለቱ የፖሊስ ባልደረቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ናቸው ማለት ነው?

አቶ ዘላለም፡ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ፣ እንዲጣራና እንዲመረመር ውሳኔ ተሰጥቷል። ይህን የሚከታተሉ ከታች ያሉ የሥራ ኃላፊዎች አሉ። እነሱ የደረሱበትን ነገር በእኛ ፖሊስ ኮምኒኬሽን በኩል አቅርበናል። ይሄ ነው የተወሰደው እርምጃ።

ቢቢሲ፡ የፖሊስ ባልደረቦቹ ምን ዓይነት ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል?

አቶ ዘላለም፡ ጥፋቱ እኮ ገና ይታያል የሚጣራ ነው። በፖሊስ ባልደረቦቹ ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ለምሳሌ አንደኛው ፖሊስ ተመቷል አብጧል የሚል ነገር አለ። ስለዚህ ፖሊሶቹ ወደዚህ የገቡት በስነምግባር ችግር ነው? የግለሰብ ችግር ነው ወይስ በእነሱ ላይ የተፈፀመ ጥቃት አለ? የሚሉት ነገሮች ሁሉ ታይቶ ነው ውሳኔ ላይ የሚደረሰው።

ቢቢሲ