የሲዳማውን ግጭት አስነስተዋል ተብለው ለተከሰሱት የተፈቀደው ዋስትና ታገደ

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ሁከቶችን አስተባብረዋል ለተባሉ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በተፈቀደው የዋስትና መብት ላይ የእግድ ትዕዛዝ ሰጠ ።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በአነ ታሪኩ ለማ መዝገብ በተጠረጠሩ ዘጠኝ ሰዎች ላይ የእግድ ትዕዛዙን የሰጠው መርማሪ ፖሊስ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነሐሴ 10፣2011 ዓም ለተጠርጣሪዎቹ የፈቀደውን የዋስትና መብት በመቃወም ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ በመቀበል ነው።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብትን የሚፈቅድ ወይም የሚከለክል መሆኑን ለማከራከርና ለፖሊስ የተሰጠው የምርመራ ጊዜም በቂ ነው ወይስ በቂ አይደለም የሚለውን በመመርመር ብይን ለመስጠት ለነሀሴ 24 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ይዞል ።

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነሐሴ አሥሩ ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የዋስትና መብት በመቀበል እያንዳንዳቸው የሃምሳ ሺህ ብር ዋስትና በማቅረብ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኖ ነበር ።በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን ተከስተው ከነበሩ ሁከቶች ጋር በተያያዘ የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ስራ አስኪያጆች እና የቦርድ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።