በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነው ሲል ትዴት አማረረ

DW : ባለፈው ዓመት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ( TAND) የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ በመሆኑ በትግራይ ክልል ለመንቀሳቀስ እየተቸገረ መሆኑን አመለከተ።የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይለ በትግራይ አማራጭ ሐሳቦች በማስተናገዱ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በማክበሩ ረገድ ውስንነት አለ ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ግዜ በክልሎች መካከል እያታየ ነው ላሉት ችግር ለመፍታት የትግራይ ዴሞክራስያዊ ትብብር የበኩሉን ሚና ለመጫወት ጥረት እያደረገ መሆኑ ጠቅሰዋል። «ቀጣይ ትውልድ» በሚል መሪ ሐሳብ የአማራና ትግራይ ክልል ወጣቶች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ ለማሰናዳት የፖለቲካ ድርጅቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ቃል አቀባዩ አቶ ሙሉብርሐን ሃይለ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል መንግሥት ግን የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነው የሚለው ወቀሳ አይቀበልም። የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በቅርቡ ከትግራይ ተወላጅ ዳያስፓራዎች ጋር ሲወያዩ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳቦቻቸው እያቀረቡ እንዲንቀሳቀሱ ድጋፍ ይደረጋል ብለው ነበር።