በሀረማያ አካባቢ የሚገኘው የከርሰ ምድረ ውኃ ሐብት ትልቅ ስጋት ተጋርጦበታል

DW : ከዓመታት በፊት የአካባቢው ገፀ በረከት የነበረው የሀረማያ ሐይቅ እንደ ዋዛ አንድ ቀን እብስ ብሎ ይጠፋል ያለ ብዙም አልነበረም ፡፡ ከዓመታት በፊት ግን ወደ ላይ ይትነን ወደ ውስጥ ይስረግ ብዙዎች ባልገባቸው መንገድ የሀረማያ ሐይቅ ደረቀ፡፡ ሀረማያ ሐይቅ ታሪክ ሆነ፡፡ የሀይድሮ ጂኦሎጂስት ባለሙያው ኃይሌ አረፋይኔ በአካባቢው የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ላይ ያደረጉትን ጥናት በሚመለከት ለ«DW» በስልክ እንደገለፁት ካለፈው ታሪክ መማር ያልተቻለ እንደሆን በሀረማያ አካባቢ የሚገኘው የከርሰ ምድረ ውኃ ሐብትም ትልቅ ስጋት ተጋርጦበታል፡፡

በዘርፉ ዓለም አቀፍ የጥናት ማድረጊያ መሳርያዎችንና መስፈርቶችን ተከትሎ ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተካሄደ ነው ባሉት ጥናት የተገኘው ውጤት ካመለከተው ግዜ ባነሰም ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ነዋሪነታቸውን በአውስትራልያ ያደረጉት እኝህ ባለሞያ ከአመታት በፊት እንደዋዛ ሙሉ በሙሉ በመድረቅ  ከገፀምድር የጠፋው የሀረማያ ሐይቅ  የጠፋበትን ምክንያት ምንነት በጥናት ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሀይድሮጊኦሎጂስት ባለሞያው አሁን ስጋት የተጋረጠበትን የሀረማያ አካባቢ የከርሰ ምድር ውኃ ሐብት ከጥፋት ለመታደግ በጥናቱ የተመለከቱ መፍትሄዎችን አብራርተዋል ፡፡አጥኚው የዚሁ ሀብት ተጠቃሚ የሆነው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱ እንዲጠና ማድረጉ አንድ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው ለመፍትሄው ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል፤ በተለይ ውኃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂን በስራ ላይ ማዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡ የገፀ ምድሩን ሐብት ያጣው የሀረማያ አካባቢ ዛሬ ላይ የከርሰ ምድር ውሀ ሐብቱን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ የሚያስችለው መፍትሄ በእጁ ስለመሆኑ ጠቁመዋል ፡፡