ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮችና በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።- የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን

ኢዜአ – በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም ለማስጠበቅ የህግን የበላይነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ የሲቪክ ማህበራት እና መላው ህዝብ በጽናትና በጋራ እንዲቆሙ የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዛሬ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮችና በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።

እነዚህን ችግሮችና ግጭቶች በአፋጣኝ ለማስወገድ፣ የዜጎች ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር ነው። ለዚህም መላው ህዝብ፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ፀንተው በጋራ ሊቆሙ ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣውን የሰላም እጦት ለማርገብና ለህዘቦች የአርምሞ ፋታ ለመስጠት እንዲቻል መላው ህዝብ ለእርቅና ሰላም እንዲቆም ጥሪ ያቀረበው ኮሚሽኑ፤ ችግሮቹ በዘላቂነት እንዲፈቱ የእርቅና ሰላም መንፈስ በኢትዮጵያ የመስፈን አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥቶታል።

ህዝቡ “በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል” በማለት ያመነበትን ወቅታዊ የለውጥ ሂደት ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በነቂስ በመውጣት የተሰማውን ደስታና ድጋፍ የገለጸበት በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩት አስታውሶ፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማስተዋል እድል ማግኘቱንም አመልክቷል።

በዚህ አንድ ዓመት ውስጥም የታዩትን የተስፋ ወጋገን የሚያጨልሙ ተግባራት መስተዋላቸውን መግለጫው ጠቁሞ፤ ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑትን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በአብነት ጠቅሷል።

ዛሬ የሲዳማን የክልል ጥያቄ ተከትሎ የታየው አሳዛኝ ክስተትም ሆነ በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያለው የዜጎች የእርስ በእርስ ግጭትና መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።

የሃይማኖት መሪዎች ፡ የሀገር ሽማግሌ የሆኑ ጭሜሳዎች እና አባገዳዎች በየአካባቢዎቻቸው ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት ህዝቡን በተለይም ወጣቱን ከማረጋጋት አኳያ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አጽንኦት የሰጠው ኮሚሽኑ፤ የፍቼ ጨንበላላ ታላቅ የመቻቻል ባህል በሰረፀባት ምድር እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች፣ መፈናቀሎች መከሰታቸው አሳዛኝ መሆኑንም አመልክቷል።

በሌሎች የክልልነት ጥያቄ እየተነሳ ባለባቸውና መሰል ችግሮች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ህዝቡን ሆነ ወጣቱን ለማረጋጋት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስቧል።

መንግስት የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሆነ ሌሎች ህዝቦች የሚያነሷቸውን መሰል ጉዳዮች በህጋዊ መንገድ በወቅቱ ለመመለስ እንዲችል የእያንዳንዱን አካባቢ ህዝብ በማሳተፍ በከፍተኛ አቅም እንዲረባረብም ኮሚሽኑ  ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው የሆኑ ወጣቶች አሁን የሚስተዋለውን የግጭት አዙሪት በአግባቡ በመረዳት ከጸብ አጫሪነት መታቀብ እንዳለባቸው አመልክቷል። በተለይም ከወንጀል እና ከመጠላለፍ አካሄድ በመራቅ ኢትዮጵያን ሆነ ህዝቦቿን የመታደግ ሃላፊነት እንዳለባቸው በአንክሮ አሳስቧል።

የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች እና የማህበራዊ ድረ ገፆች በኢትዮጵያ እየታየ ያለ የግጭት አዙሪት ሊያስከትል የሚችለውን ውድመት በመረዳት ልዩነትን እና አለመግባባትን ከሚያቀነቅኑ ድርጊቶች እንዲታቀቡ የጠየቀው ኮሚሽኑ፤ “የሀሰት መረጃዎችን ከማሰራጨት ተቆጥበው በሚያስተሳስሩ እና በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው ይሰሩ ዘንድ አደራ እንላለን” በማለት ገልጿል።

እነዚህን ችግሮች “መላው የሀገራችን ህዝቦች በሚገባና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይወጡታል” ሲል እንደሚያምን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በውይይት እና በንግግር ብቻ እንዲፈቱ ፣ ፍትህ እንዲያገኙም ሆነ እርቅና ሰላም በመሀላቸው እንዲወርድ የሚያደርገውን አጋዥ እንቅስቃሴ በቅርቡ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል።

በቅርቡ በአዋጅ የተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ቀደም የተከሰቱና ያለፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በህዝቦች መካከል ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን መሰረታዊ መንስኤዎቻቸውን በመመርመር፤ ካለፉ የተበላሹ ታሪኮች በመማር ዘላቂ ሰላምና እርቅ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ቀዳሚ ዓላማው በማድረግ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው።